U-20 | አዲስ አበባ ከተማ እና አዳማ ሲያሸንፉ መሪው ሆሳዕና ከ ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርቷል

የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ ምድብ ለ በአዳማ ከተማ ቀጥሎ በኮቪድ ምርመራ መዘግየት ምክንያት ያልተካሄዱት የአራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከትናንት እስከ ዛሬ ጠዋት ተከናውነዋል። በዚህም አዲስ አበባ ከተማ እና አዳማ ከተማ ሲያሸንፉ ሀድያ ሆሳዕና ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርተዋል፡፡

3፡00 ላይ ይጀመራል ተብሎ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ ጨዋታ የኮቪድ ውጤት በጊዜ ባለመድረሱ ከሰዓት 7፡15 ላይ ተጀምሯል፡፡ ጠንካራ እንቅሴቃሴን ባየንበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከዳኝነት ውሳኔዎች ውጪ ተጫዋቾች በሜዳ ላይ የነበራቸው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ግን አስገራሚ ነበር፡፡ አራት ጎሎችን ባየንበት የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኳስን መሰረት ካደረገ ጨዋታ እስከ ረጃጅም እና በመስመር ተሻጋሪ የሆኑ ድንቅ እንቅስቃሴን ማድረግ የቻሉበት ነበር፡፡ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ረጃጅም ኳሶች ላይ ትኩረትን ሲያደርጉ የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች በዚሁ የአጨዋወት መንገድ ጎል አስቆጥረዋል፡፡ 23ደቂቃ ላይ አቡበከር መሀመድ የግል አቅሙን ተጠቅሞ ኳስን እና መረብን አገናኝቶ ክለቡን ቀዳሚ አድርጓል፡፡


በኳስ ቅብብል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ሲታትሩ የሚታዩት ወልቂጤዎች ለማጥቃት ጥረት በሚያደርጉት ጊዜ በቁጥር አንሰው መታየታቸው በቀላሉ ለአዲስ አበባ ከተማ ተከላካዮች ሲሳይ ሲሆን መመልከት ችለናል፡፡32ኛው ደቂቃ ቧይ ኩዊት በድጋሚ አዲስ አበባ ከተማን ወደ 2ለ0 ከፍ አድርጓል፡፡ አጋማሹ ሊጋማስ አራት ደቂቃ ሲቀሩት ከሰሞኑ የትጥቅ ድጋፍን ያገኙት ወልቂጤ ከተማዎች አከታትለው ባስቆጠሩት ጎል አቻ ሆነዋል፡፡ 42ኛው ደቂቃ የአዲስ አበባ ተከላካዮች ኳስ በእጅ በመንካታቸው የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ዮሴፍ ብርሀኑ ሲመታ በግብ ጠባቂ ቢመለስበትም ራሱ በድጋሚ አስቆጥሮ ክለቡን አነቃቅቷል፡፡ ከሁለት ደቂቃ በኃላ ምንተስኖት ዮሴፍ ወልቂጤዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ከመረብ አዋህዶ ወደ መልበሻ ክፍል 2ለ2 በሆነ ውጤት አቅንተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ አዲስ አበባ ከተማዎች በሁሉም ረገድ የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም በመከላከሉ ላይ የጥንቃቄ ጉድለት ስለሚታይ በቀላሉ በወልቂጤ ተጫዋቾች ላይ ስህተት ሲሰሩ ተመልክተናል፡፡የወልቂጤ ከተማ ተከላካዮች በሰሩት የአቋቋም ስህተት ከግራ አቅጣጫ እየገፋ ወደ ሳጥን ገብቶ ቴዎድሮስ ናስር ግሩም ጎል አስቆጥሮ አዲስ አበባ ከተማን 3 ለ 1 አድርጓል፡፡ 60ኛው ደቂቃ የአዲስ አበባ ተከላካይ በዮሴፍ ብርሀኑ ላይ በሳጥን ውስጥ የሰራበትን ጥፋት ተከትሎ ዳግም ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ሀይደር ሸሪፍ በቀላሉ አስቆጥሮ 3ለ3 ቡድኑን አድርጓል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው ቴዎድሮስ ናስር በሚገርም መልኩ ከቀኝ አቅጣጫ የሰጠውን ኳስ አቡበከር መሀመድ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ 4ኛው ጎል በማስቆጠር ጨዋታው 4 ለ3 በአዲስ አበባ አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

9፡22 ሲል የጀመረው የአዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን የምድቡ ሁለተኛ መርሀ ግብር ተካሂዷል፡፡ አዳማ ከተማዎች ማራኪ እንቅስቃሴን ባደረጉበት እና ብልጫን ወስደው በታዩበት በዚህ ጨዋታ ገና ጅምሩ ወደ መድን የግብ ክልል በቶሎ ደርሰው የታዩ ቢሆንም መድኖች በመልሶ ማጥቃት መሪ የሆኑበትን ጎል ግን አግኝተዋል፡፡ በሚያደርጋቸው አስፈሪ እንቅስቃሴዎቹ ስናስተውለው የነበረው አሸብር ደረጀ 7ኛው ደቂቃ ለክለቡ ግሩም ጎል አስቆጥሮ ክለቡን መሪ ቢያደርግም የኃላ ኃላ እጃቸውን ለአዳማ ከተማ አሳልፈው ለመስጠት ተገደዋል፡፡

26ኛው ደቂቃ ላይ መረጋጋት የማይታይበት የመድን የተከላካይ መስመር በሰሩት ጥፋት አዳማዎች ያገኙትን የፍጹም ቅጣት ምት ቢኒያም አይተን ቡድኑን አስቆጥሮ 1ለ1 ማድረግ ችሏል፡፡ 40ኛው ደቂቃ ከርቀት አብዲ ዋበላ ግሩም ጎል በማስቆጠር አዳማን 2ለ1 ወደ ሆነ ውጤት አሸጋግሯል፡፡

ከእረፍት መልስ በቀጠለው እና አሁንም የአዳማ ከተማ የበላይነት በታየበት ጨዋታ ብዙም የጎል ዕድሎችን ባንመለከትም ከእንቅስቃሴ አንፃር ግን ጥሩ እና ተስፋ የሚሰጡ ተጫዋቾችን በይበልጥ የተመለከትንበት ነበረ፡፡ ተስፈኛው አጥቂ ቢኒያም አይተን ከቀኝ በኩል በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ አክርሮ መቶ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሶስተኛ ጎል ከመረብ በማሳረፍ አዳማ ከተማን 3ለ1 አሸናፊ አድርጓል፡፡

ትናንት 11፡22 ሲል የጀመረው የሀድያ ሆሳዕና እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ እስከ 75ኛው ደቂቃ ድረስ ተደርጎ ተቋርጧል። የተቋረጠበትም ምክንያት የቀደሙ ጨዋታዎች በመዘግየታቸው ከተያዘለት ሰዓት ዘግይቶ በመጀመሩ እና በመምሸቱ ምክንያት ነበር። ዛሬ ረፋድ 3፡30 የቀረው 15 ደቂቃ ተከናውኖም ያለ ጎል ተጠናቋል፡፡

የኢትዮ ኤሌክትሪኮች ያማረ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ከሀድያ ሆሳዕናዎች በተሻለ ባየንበት ጨዋታ ረጃጅም ኳስ ላይ ያተኩሩ የነበሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች ኳስን ይዘው በሚጫወቱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች አንፃራዊ ብልጫ ተወስዶባቸዋል፡፡ የእንቅስቃሴውን ያህል ብዙም የጎል ዕድሎችን መመልከት ያልቻልንበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በትላንትናውም ሆነ በዛሬው ቀሪ ደቂቃዎችም ጎሎች ሳይቆጠሩ 0ለ0 ተጠናቋል፡፡



© ሶከር ኢትዮጵያ