ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

የ13ኛው የጨዋታ ሳምንት አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች እና ዐበይት አስተያየቶችን እነሆ!

👉 ዘማርያም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ተመልሰዋል

ከጥቂት ቀናት በፊት ፍሰሀ ጥዑመልሳንን በመተካት የድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝነት ወንበሩን የተረከቡት አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ አዲሱን ቡድናቸውን እየመሩ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታቸውን ሀዋሳ ከተማን በመግጠም ጀምረዋል። ያለ ግብ በተጠናቀቀው ጨዋታ አሰልጣኙ ለአንድ ዓመት ከሚጠጋ ጊዜ በኋላ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በፕሪምየር ሊጉ አድርገዋል።

ከዚህ ቀደም ባሰለጠኗቸው ቡድኖች እንዳስመለከቱን አሰልጣኙ ኳስን ተቆጣጥሮ ማጥቃትን ምርጫው ያደረገን ቡድን ለመገንባት ካላቸው ፅኑ ፍላጎት አንፃር አዲስ የተረከቡት የድሬዳዋ ከተማ ስብስብ ያለው በንፅፅር የተሻለ የተጫዋቾች አማራጭ የቡድን ግንባታ ግንባታቸው ጥሩ መነሻ እንደሚሆን ሲጠበቅ በቀጣይ በዝውውሮች ራሱን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀርብ ይጠበቃል። በአሰልጣኙ አገላለፅ ‘የተጨዋቾቹ ብቃት እና ያለበት ደረጃ የተለያየ የሆነው’ ድሬዳዋ ከተማ በአሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ስር በቀጣይ በምን መልኩ ሊሻሻል ይችላል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

👉 አስቻለው ኃይለሚካኤል እና የአዳማ መጨረሻ

እንደ ተራራ የገዘፈ የሚመስለውን ከቀድሞው አዳማ ከተማ ስያሜን ብቻ የወረሰውን አዲሱ ቡድኑን የማዋቃር ከፍተኛ ኃላፊነት ወስደው ስራ የጀመሩት አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል አዳማ በዝውውሩ ካሰባሰባቸው ተጫዋቾች የጥራት ደረጃ እና ከነበረው የዝግጅት ጊዜ ማነስ አንፃር አጣብቂኝ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ፍንጭ የሚሰጡ ሀሳቦችን መስጠት ከጀመሩ እጅግ ሰንብተዋል። ታድያ የሆነውም የዚሁ ነፀብራቅ ነው። ቡድኑ የመጀመሪያው ዙር ሲጠናቀቅ ካደረጋቸው 12 ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፎ እንዲሁም በአንድ ጨዋታ አቻ ተለያይቶ ሰባት ነጥቦች ብቻ በመሰብሰብ የሊጉ ግርጌ በመሆን አጠናቋል።

ይህንን ተከትሎ ከአዳማ ጋር በስምምነት የተለያዩት አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤልን ስንብት ለየት የሚያደርገው ግን ቡድኑ የመጨረሻ የሊግ ጨዋታውን ከማድረጉ አስቀድሞ አሰልጣኙ ከኃላፊነታቸው ራሳቸውን ቢያነሱም በክለቡ አመራሮች ርብርብ አሰልጣኙ በኢትዮጵያ ቡና 4-1 የተረታውን ስብስብ እየመሩ ወደ ሜዳ መግባታቸው ነው። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ግን ሲጠበቅ የነበረው የአሰልጣኙ እና የአዳማ መለያየት ይፋ ሆኗል። እንደ ቡድን በርካታ ክፍተቶች ያሉበት አዳማ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን መሾሙ ሲሰማ በአሰልጣኝ ለውጥ ብቻ ከተጋረጠበት አደጋ ይወጣል ወይ የሚለውን ጥያቄ በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታዎች የምንመለከተው ይሆናል።

👉 የሰከኑት ካሳዬ አራጌ

አሰልጣኞች እንደ ማንኛውም ሰው በህይወት ጉዟቸው የስሜት ከፍታ እና ዝቅታ ማስተናገዳቸው ብሎም እነዚሁን ስሜቶች የሚያፀባሩቁባቸው ተለዋዋጭ ግብረ መልሶችን በስራቸው ላይ ማሳየታቸው የሰውነታቸው መገለጫ ተደርገው ይወሰዳሉ። ታዲያ ይህን የህይወታችን አንዱ አካል የሆነውን የስሜት መለዋወጥ ግን በኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ላይ መመልከት እጅግ አዳጋች ይመስላል።

አሰልጣኙ ብዙዎቻችን በምናውቀው ከካሜራ ፊት እና በሜዳው ጠርዝ ቡድኑን ሲመሩ የሚታይባቸው የስሜት ወጥነት እጅግ አስደናቂ ነው። ቡድኑ ቢመራም አልያም ብልጫ ቢወሰድበት አሰልጣኝ ካሳዬ ግን እንደተለመደው እጅጉን ተረጋግተው በሜዳው ጠርዝ ላይ ይታያሉ እንጂ ሲቅበጠበጡ እና በስሜት መዋዥቅ ውስጥ ሆነው አናያቸውም።

እንደ አብዛኞቹ የሊጉ አሰልጣኞች ከቡድኑ በተቃራኒ የሚወሰኑ የዳኝነት ውሳኔዎችን ተከትሎ እንኳን ተቃውሞዎችን ስያሰሙ አይስተዋልም። ታድያ ይህ የሰከነ ስብዕና አያስገርምም ትላላችሁ ?

ዓበይት አስተያየቶች

👉ካሳዬ አራጌ ስለ አቡበከር ናስር ብቃት

“የቡድኑ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተጫዋች አቡበከር ነው ማለት ይቻላል። ግን ደግሞ እሱንም የቡድኑ እንቅስቃሴ ጠቅሞታል። እንደ ቡድን በምናጠቃበት ጊዜ በቁጥር ብዙ ሆነን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ስለምንደርስ ተጫዋቾች ማንን መያዝ እንዳለባቸው ይቸገራሉ። ይህ ደግሞ አቡበከርን አግዞታል። ግን ደግሞ ብዙ ትኩረት እየተደረገበት ይህንን ሁሉ ግቦች ማስቆጠር መቻሉ ደግሞ የእርሱን ብቃት ያሳያል።”

👉ተሰናባቹ አስቻለው ኃይለሚካኤል ስለ አንደኛ ዙር የአዳማ አጠቃላይ እንቅስቃሴ

“ከነበረን የዝግጅት ሁኔታ አኳያ የሚታሰቡ ነገሮች አሉ። ኳሊቲም ቡድንህ ውስጥ ሊኖር ይገባል። በተጨማሪም ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ቢኖሩ መልካም ነው። እንደሚታወቀው ሌሎቹ ቡድኖች ብዙ ገንዘብ አውጥተው ነው የተሰሩት። የእኛ ግን እንደምታቁት ነው። ባለን አቅም ነበር ስንዘጋጅ የቆየነው። ይሄ ነገርም እንደሚደርስብን ቀድመን አስበን ነበር። ነገርግን እንስራ በሚል ሀሳብ ነበር የገባንበት። አሁን የክለቡ የበላይ አመራሮች ዘግይተው ነው ለክለቡ የደረሱት። ቀድመው ቢሆን ኖሮ ጥሩ ነበር። ብዙ ሮሮ አሰምተን ነው የተሰማነው። እኔም አዳማ በሁለተኛ ዙሩ ጥሩ ውጤት እንዲገጥመው እመኛለሁ።”

👉 አሸናፊ በቀለ ለቡድኑ ግብ የማስቆጠር ችግር

“ከጅማ ጀምሮ ብዙ መሰናክሎች ነበሩብን። የነገሮች አለመስተካከል ፣ የተጨዋቾች ጤና መጓደል እና ተሟልቶ አለመግባት ፤ ምክንያት ይሆንብኛል እንጂ ዛሬም አምስት ያህል ቋሚ ተሰላፊዎች አልነበሩም። እነዚህን ነገሮች ለማስተካከል አንደኛ ክፍተቶችን መድፈን ይፈልጋል። ተጠባባቂ ላይ ያገኘናቸው ተጫዋቾችም ሁለት ቢሆኑ ነው። ሌሎቹ ምን ያህል ጠቃሚ ነበሩ የሚለውም አጠያያቂ ነው። ቡድኑን ወደ ተሻለ ሁኔታ ለመውሰድ የሰው ኃይል አስፈላጊ ነው። ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ቢስተካከል መልካም ነው ብዬ አስባለሁ።”

👉ፀጋዬ ኪዳነማርያም ስለ ዝውውር መስኮት

“ተጫዋቾችን ማምጣት የግድ ነው። ክፍተቶች ባሉበት ቦታ ላይ ተጨማሪ ተጫዋቾች ለማግኘት እንሞክራለን። በእርግጥ ያናገርናቸው ተጫዋቾች ከእጃችን እያመለጡ ነው ያሉት። ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ አላወቅኩም። ዞሮ ዞሮ ስር ነቀል ሳይሆን ቡድኑን ለማጠናከር ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን።”

👉ዘላለም ሽፈራው በሁለተኛው ዙር ቡድኑ መጠናከር ስላለበት ቦታ?

“እንደሚታወቀው መጀመሪያ አካባቢ የነበረው ውጤት ትንሽ ደከም ያለ ነበር። ነገርግን ቡድኑን እየጠጋገንን ውጤት ለመያዝ ጥረናል። ይህም ተሳክቶልናል። በሁለተኛው ዙር ግን ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነን መቅረብ ይኖርብናል። በተለይ ከግብ ጠባቂው ጀምሮ በሚገኘው ቀጥታ የሜዳ ክፍል ትንሽ ክፍተት አለብን። በእነዚህ የሜዳ ክፍል ላይም የሚያስፈልጉንን ተጫዋቾች አዘዋውረን ጨርሰናል።”

👉ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ቡድኑ መሻሻሎችን ማድረግ ስላለበት ቦታ?

ኳስ ስንይዝ መስተካከል ያለበት ነገር አለ። ስለዚህም መሐል ሜዳ ላይ የምናስተካክለው ነገር ይኖረናል። በአጥቂ መስመር ላይ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች አሉን። በእነሱ ላይ ሰርተን ስል ለመሆን እንሞክራለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ