ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

የመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ሳምንት በነበረው 13ኛው ሳምንት ላይ ያተኮሩ ዐበይት ነጥቦችን እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።

👉 ፋሲል ከነማ የአሸናፊነት ጉዞ ተገቷል

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ከሰንጠረዡ አናት ሆኖ የሚመራው ፋሲል ከነማ ለመጨረሻ ጊዜ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከባህር ዳር ከተማ ጋር አቻ ከተለያየ ወዲህ ተከታታይ ስድስት ጨዋታዎችን በአሸናፊነት በመዝለቅ አስደናቂ ጉዞን ማድረግ ቢችልም በ13ኛው የጨዋታ ሳምንት ከሰበታ ከተማ ጋር 1-1 በመለያየቱ የአሸናፊነት ጉዞው ሊገታ ችሏል።

አዝናኝ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ ማራኪ የሆነ ፉክክርን አስመልክቶናል። ገና በ4ኛው ደቂቃ ፋሲል ከነማዎች ከተከላካይ ጀርባ በተጣለ ኳስ ያገኙትን አጋጣሚ ሽመክት ጉግሳ አስደናቂ ፍጥነቱን ተጠቅሞ መሪ ማድረግ ችሏል። ፋሲል ተከታታይ አሸናፊነቱን ለማስቀጠል እስከ 77ኛው ደቂቃ ድረስ በመሪነት ቢቀጥልም ከቅጣት ምት የተሻማን ኳስ ተጠቅሞ ቡልቻ ሹራ ሰበታን አቻ በማድረጉ ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤር እንዲጠናቀቅ ሆኗል።

በመጀመሪያ አጋማሽ ከፍ ባለ ፍላጎት በቀጥተኛ እና በመስመር ተጫዋቾቻቸው ፍጥነት ላይ የተመሰረተ ጥቃትን መሰንዘር ጀምረው የነበሩት ፋሲል ከተማዎች ይህን ሒደት በሁለተኛው አጋማሽ ማስቀጠል ባለመቻላቸው በእጃቸው የገባውን መሪነት በስተመጨረሻ አጥተው በአቻ ውጤት ጨዋታውን ለማጠናቀቅ ተገደዋል።

ተከታዮቻቸው በሙሉ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ማሸነፋቸውን ተከትሎ ነጥብ መጋራታቸው ከተከታዮቻቸው የነበረውን የሰባት ነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ቢጠብም ለአስር ጨዋታዎች ሳይሸነፉ መጓዝ የቻሉት ፋሲሎች አሁንም በ29 ነጥብ ሊጉን እየመሩ የመጀመሪያውን ዙር ማጠናቀቅ ችለዋል። በቀጣይ ከተከታዮቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት ጨዋታ በቀጣይ የውድድር ዘመን ጉዟቸው ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ እጅግ ወሳኝ ነው።

👉 ኢትዮጵያ ቡና አጋማሹን በአስደናቂ ብቃት ደምድሟል

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ያለግብ አቻ የተለያዩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አዳማ ከተማን ከፍፁም የጨዋታ የበላይነት ጋር 4-1 በመርታት የውድድር ዘመኑን አጋማሽ በድል ደምድመዋል።

በጨዋታ ሳምንቱ መክፈቻ ኢትዮጵያ ቡና በመጀመሪያው አጋማሽ በ69% አማካይ የኳስ ቁጥጥር አምስት አደገኛ የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም በተጫዋቾች ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች ፍፁም ማጥቃት ላይ ትኩረት አድርገው ይንቀሳቀሱ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ የተነጠቁትን ኳስ ዳግም መልሶ ለማግኘት ባደረጉት ደካማ ተነሳሽነት መነሻነት በተገኘችው እና በአጋማሹ ያደረጓትን ብቸኛ ኢላማውን የጠበቀችውን ሙከራ አብዲሳ ጀማል አስቆጥሮ ሁለቱ ቡድኖች ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተው ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመሪያው ሁሉ ኢትዮጵያ ቡና ለአዳማ ከተማ የሚቀመሱ አልሆኑም ፤ በዚህኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡና ከመጀመሪያው በተሻለ የተገኙ የግብ አጋጣሚዎችን ወደ ግብነት በመቀየር የጨዋታውን ውጤት መቀልበስ ችለዋል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች አራት ግቦችን ማስቆጠር በቻሉበት አጋማሽ አስደናቂው አጥቂ አቡበከር ናስር ሐት-ትሪክ ሲሰራ ቀሪዋን ደግሞ ታፈሰ ሰለሞን አስቆጥሮ ከጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው በመውጣት ነጥባቸውን ወደ 24 በማሳደግ የመጀመሪያውን ዙር በሁለተኝነት ማጠናቀቅ ችለዋል።

👉ቀሪ ሥራዎች የሚጠብቁት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዳግም አሸንፏል

የሊጉ ውድድር ወደ ባህርዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም ካመራ ወዲህ ሁለተኛ ጨዋታውን ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልቂጤ ከተማ ብርቱ ፈተና ቢገጥመውም በእጁ የገባውን መሪነት እንደምንም አስጠብቆ በመውጣት ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል።

4-3 በሆነ ውጤት በቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነት በተጠናቀቀው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ኳስን ተቆጣጥረው ወደ ግራ መስመር ባጋደለ መልኩ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። ገና በ8ኛው ደቂቃ ግብ ያስተናገዱት ፈረሰኞቹ ግብ ካስተናገዱ ወዲህ በከፍተኛ ተነሳሽነት ሲንቀሳቀሱ ተስተውለዋል በተለይም የአምበሉ ጌታነህ ከበደ ትጋት የተለየ ነበር።

ጌታነህ ከበደ ከቅጣት ምት እና በግንባሩ በመግጨት ሁለት ግቦችን ባስቆጠረበት በዚሁ ጨዋታ ቀሪዎቹን ግቦች አቤል እንዳለ እና አብዱልከሪም መሐመድ አስቆጥረዋል። አራት ግቦች አስቆጥረው መምራት የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጨዋታው የመጨረሻ 30 ደቂቃዎች ከተጋጣሚያቸው ወልቂጤ ከነማ ከፍ ያለ ጫናን አስተናግደዋል። በዚህም 4-1 እየተመሩ የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች በቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ለዓለም ብርሃኑ ስህተቶች ታግዘው የኋላ ኋላ ተጨማሪ ሁለት ግቦችን አስቆጥረው ጨዋታው 4-3 ሊጠናቀቅ ችሏል።

እንደባለፈው የጨዋታ ሳምንት ሁሉ በማጥቃት ወቅት የተሻለ ቅንጅት ያለው ቡድኑ በሁለት ጨዋታዎች ብቻ ስምንት ግቦችን ቢያስቆጥርም ሲከላከል ግን ቡድኑ አሁንም በግልፅ የሚታዩ የአደረጃጀት ክፍተቶች እንዳሉበት ይስተዋላል። ይህም ጉዳይ ቡድኑ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ በተጫዋቾቹ ላይ ከሚታየው መዘናጋት ጋር ተዳምሮ በሁለት ጨዋታዎች ብቻ አምስት ግቦችን እንዲያስተናግድ ሆኗል።

በመከላከሉ ረገድ ያሉበትን ክፍተቶች በሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽ ቀርፎ መቅረብ የሚገባው ጊዮርጊስ የመጀመሪያውን ዙር በሁለተኛ ደረጃ ከሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና እኩል 24 ነጥብ አስመዝግቦ በሦስተኛ ደረጃ ማጠናቀቅ ችሏል።

👉 ሀዲያ ሆሳዕና በመጨረሻ ደቂቃ ጎል ወደ ድል ተመልሷል

ከአስደናቂ አጀማመሩ ማግስት የነበረውን አስደናቂ የሜዳ ላይ ግስጋሴ መድገም የተሳነው ሀዲያ ሆሳዕና በዚህ ሳምንት በኮቪድ እና በጉዳት ሳቢያ ሦስት የሜዳ ላይ ተጨዋቾችን ብቻ በተጠባባቂነት ይዞ ተቸግሮም ቢሆን ጅማ አባ ጅፋርን ማሸነፍ ችሏል።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ከእስከዛሬው በተሻለ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም አጋጣሚዎቹ ኢላማቸውን መጠበቅ ባለመቻላቸው እንጂ የጨዋታው ውጤት ማሳያ ላይ በመጀመሪያው አጋማሽ ለውጥ በተመለከትን ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማ አባ ጅፋሮች ፍፁም የሚያስቆጩ አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም እድሎቹን መጠቀም ሳይችሉ በመቅረታቸው 0-0 ሊጠናቀቅ ጨዋታው ቢቃረብም ጋናዊው አማካይ አልሀሰን ካሉሻ በ90ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ሆሳዕናዎች ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ አሸንፈው ለመውጣት በቀተዋል።

በተሰረዘው የውድድር ዘመን በውድድሩ አጋማሽ በሊጉ ግርጌ ይዳክር የነበረው ሀዲያ ሆሳዕና ዘንድሮ ፍፁም የሆነ መሻሻልን በማሳየት በ23 ነጥብ በአራተኛ ደረጃ ዙርን ማጠናቀቅ ችሏል።

👉ወላይታ ድቻ ማንሰራራቱን ቀጥሏል

የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረገ ወዲህ አስገራሚ ማንሰራራትን እያሳየ የሚገኘው ወላይታ ድቻ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ሲዳማ ቡናን በአናጋው ባደግ ብቸኛ ግብ በማሸነፍ የመጀመሪያውን ዙር በስምንተኛ ደረጃ ማጠናቀቅ ችሏል።

ወደ ኋላ ጠቅጠቅ ብለው በመከላከል እንዲሁም በመስመሮች በኩል በሚሰነዘሩ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ኳሶች ሲዳማ ቡናን ጫና ውስጥ መክተት የቻሉት ድቻዎች በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ያገኟትን ብቸኛ ግብ ለማስጠበቅ በቀሩት ደቂቃዎች እጅግ በጥንቃቄ ተጫውተው መሪነታቸውን በማስጠበቅ ወሳኙን ሦስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት በቅተዋል።

ከጨዋታ ጨዋታ ደረጃቸውን ማሻሻል ላይ የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች ከወራጅ ቀጠናው ተላቀው ነጥባቸውን ወደ 14 በማሳደግ የመጀመሪያውን ዙር በ8ኛ ደረጃ ማጠናቀቅ ችለዋል።

👉 መሻሻል የከበደው ሲዳማ ቡና

የወትሮው የዋንጫ ተፎካካሪ ቡድን ሲዳማ ቡና ዘንድሮ ተቃራኒ መንገድን ይዞ ቀጥሏል። በጅማ ከነበረው የውድድሮ ቆይታ መልስም ክለቡ ለውጦችን አድርጎ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ምትክ ሾሟል። ሆኖም ያለፉት ሁለት ጨዋታዎች አቋሙ የመሻሻል ምልክትን የሰጠ አልነበረም። በ12ኛው ሳምንት ያለድል በቆየው ጅማ አባ ጅፋር ሲረታ አሁን ደግሞ በወላይታ ድቻ ሽንፈት ደርሶበታል።

ቡድኖች አዲስ አሰልጣኝ በሾሙ ማግስት የሚታይባቸው መነቃቃት እና የውጤት መስተካከል በሲዳማም ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም ቡድኑ በእንቅስቃሴም ሆነ በውጤት ወርዶ ታይቷል። ይህንን ተከትሎም በሰንጠረዡ አጋማሽ ወረድ ብሎ የነበረው ቡድኑ ወደ ወራጅ ቀጠናው ገብቷል። በተለይም ከወገብ በላይ ያለው የቡድኑ ክፍል ሁነኛ የማጥቃት ዕቅድ ኖሮት ያልታየ ሲሆን የኳስ ቅብብል ስኬቱም የወረደ ሆናል። በተጨማሪም ግብ ከማስቆጠር የራቁት የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ የተጋጣሚን ተከላካይ ክፍል የመረበሽ አቅማቸው እንዲሁ ደካማ ሆኖ ታይቷል። ረዣዥም ኳሶችን በመጣል ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረትም ስኬታማ ሳይሆን በድቻ ዳግም ሽንፈት አግኝቷቸዋል። አሁን ላይ የሲዳማ ተስፋ የሚሆነው አዲስ ያስፈረማቸውን ተጨዋቾቹን ከቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት ጀምሮ የመጠቀም ዕድል ያለው መሆኑ ነው። አሰልጣኝ ገብረመድህንም ከዚህ በኋላ በሚኖሩት ጨዋታዎች የቡድኑን ክፍተቶች በአዲስ ፈራሚዎቹ በመሸፈን ምን ዓይነት ለዉጥ ያስመለክቱናል የሚለውን የምንመለከት ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ