ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የምርቃት ፈለቀ ሁለት ጎሎች አዳማን ባለድል አድርገዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የ13ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ በአዳማ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ መካከል ተደርጎ፡፡ ምርቃት ፈለቀ ያስቆጠረቻቸው ሁለት ጎሎች አዳማን ሙሉ ሦስት ነጥብ አስጨብጧል፡፡

ጠንካራ ሙከራዎችን ማየት ባልቻንበት እና አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች መሀል ሜዳ ላይ ብቻ በተገደበ እንቅስቃሴ አመዝኖ በታየበት ጨዋታ በአንፃራዊነት አዳማ ከተማዎች ወደ አርባምንጭ የግብ ክልል በመድረሱ ስኬታማ የነበሩ ሲሆን በእንቅስቃሴ ግን ተመሳሳይ ይዘትን ማስተዋል ችለናል፡፡ ጨዋታው እንደተጀመረ አርባምንጮች በመልሶ ማጥቃት ሽግግር በፍጥነት ወደ አዳማ የግብ ክልል በመድረስ ቀዳሚ የነበሩ ቢሆንም ሒደታቸው ወጥነት የጎደለው ነበር።

በሒደት በሰርካለም ጉታ እና ምርቃት ፈለቀ ድንቅ ጥምረት ወደ የአርባምንጭን የተከላካይ ክፍል ሲፈትኑ የታዩት አዳማዎች ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር የተሻሻለ የማጥቃት አቀራረብን ለማሳየት ጥረዋል፡፡ ምርቃት ፈለቀ 35ኛው ደቂቃ ከሰርካዲስ ጉታ ያገኘችውን ኳስ አስቆጥራ ከጨዋታ ውጪ ከተባለባት አምስት ደቂቃዎች ከተቆጠሩ በኃላ የአርባምንጯ ግብ ጠባቂ ነህሚያ አብዲ በምርቃት ላይ በሰራችባት ጥፋት የዕለቱ ዋና ዳኛ ምስጋና ጥላሁን የፍፁም ቅጣት ምት በመስጠቷ ራሷ ምርቃት ወደ ጎልነት የተገኘውን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም አዳማን መሪ አድርጋለች፡፡ ቤተል ጢባ ካደረገችው የርቀት ሙከራ ውጪ ሁነኛ አጥቂ በማጣታቸው ያገኙትን ጥቂት አጋጣሚዎች መጠቀም ያልቻሉት አርባምንጮች በአዳማ ከተማ እየተመሩ አጋማሹ 1ለ0 ተገባዷል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ አቀራረባቸውን በሚገባ አሻሽለው የተመለሱት አርባምንጮች ከመጀመሪያው አጋማሽ በላቀ ደረጃ አዳማ ከተማን መፈተን ችለዋል፡፡ ሆኖም የተከላካይ አደራደር ስህተት ጎልቶ የሚታይባቸው አርባምንጮች በአዳማ አጥቂዎች ለመፈተን ተገደዋል፡፡ የምስራች ላቀው በረጅሙ አሻምታ ናርዶስ ጌትነት ባዶ ጎል የሳተችበት አስቆጪ የአዳማ ሙከራ ነበር፡፡ 70ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የሜዳ ላይ ቆይታ የነበራት ሰርካዲስ ጉታ ጣጣውን የጨረሰ ኳስ የግል አቅሟን በመመገባ አሟጣ ወደ ሳጥን ገፍታ በመግባት መሬት ለመሬት የላከችሁን ኳስ ምርቃት ፈለቀ ለራሷ እና ለክለቧ ሁለተኛ ጎል ከመረብ አሳርፋለች፡፡

በእንቅስቃሴ ከአዳማ ጋር ቢመጣጠኑምም የአጥቂ ክፍላቸው ደካማ የነበረባቸው አርባምንጮች በሰናይት ባሩዳ ተደጋጋሚ ጥረቶች በኃላ ከመሸነፍ ያልዳኑበት ጎል አግኝተዋል፡፡80ኛው ደቂቃ ላይ በግምት 30 ሜትር ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት በአርባምንጭ በኩል በግሏ ስትታትር የነበረችው አንጋፋዋ ተጫዋች ሰናይት ባሩዳ ግሩም ጎል አክርራ በመምታት ከመረብ በማዋሃድ አርባምንጭ ከተማ በመጨረሻም ያለ ጎል ከመውጣት ተርፎ ጨዋታው በመጨረሻም በአዳማ ከተማ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት ምርቃት ፈለቀን የጨዋታው ምርጥ ብሎ ሸልሟታል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ