ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ ከአራት ተከታታይ የአቻ ውጤት በኋላ ድል አድርገዋል

125ኛውን የአድዋ የድል በዐል በማሰብ የተጀመረው የአስራ አራተኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ መርሐ-ግብር በባህር ዳር ከተማ አሸናፊነት ተገባዷል።

ከሦስት ጨዋታዎች ሽንፈት በኋላ የመጡት ሲዳማ ቡናዎች በድቻው ጨዋታ በቀይ ካርድ ያጡት ፈቱዲን ጀማልን ጨምሮ አማኑኤል እንዳለ፣ ዮሴፍ ዮሐንስ፣ አዲሱ አቱላ እና ግሩም አሠፋን አዲስ ባስፈረሟቸው ሽመልስ ተገኝ፣ መሐሪ መና፣ ዮናስ ገረመው እንዲሁም ከጉዳት በተመለሰው ይገዙ ቦጋለ እና ሰንደይ ሙቱኩ ተክተው ለጨዋታው ቀርበዋል። ከአራት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት ባህር ዳር ከተማዎች ደግሞ በ12ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ቋሚ 11 ሁለት ተጫዋቾችን ለውጠዋል። በዚህም ሳለአምላክ ተገኘን እና ምንይሉ ወንድሙን በግርማ ዲሳሳ እና ባዬ ገዛኸኝ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ከጨዋታው መጀመር በፊት የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ የሆኑት ዶ/ር ሳህሉ ድረስን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ግለሰቦች ከሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች ጋር በመሆን በዛሬው ዕለት እየተከበረ የሚገኘውን 125ኛውን የአድዋ የድል በዓልን የሚያስታውስ የጉንጉን አበባ የማስቀመጥ መርሐ-ግብር አከናውነዋል።

የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ ላይ በኳስ ቅብብሉ ተሽለው የታዩት ባህር ዳር ከተማዎች በ6ኛው ደቂቃ በአንድ ሁለት ቅብብል የተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሰው በአፈወርቅ አማካኝነት ጥቃት መሰንዘር ጀምረዋል። በተቃራኒው በባህር ዳር የግብ ክልል ሁለት የቅጣት ምት በስምንት ደቂቃዎች ውስጥ ያገኙት ሲዳማ ቡናዎች ያገኙትን አጋጣሚ በግንባር ወደ ግብነት ለመቀየር ጥረው መክኖባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ረጃጅም ኳሶችን ከተከላካይ ጀርባ ለመላክ በመሞከር ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። በዚህ እንቅስቃሴም ይገዙ ቦጋለ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ለመጠቀም በሚሮጥበት ሰዓት የባህር ዳሩ የግብ ዘብ ሀሪሰን ሄሱ ጥፋት ሰርቶበት ቡድኑ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝቷል። የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምትንም ዳዊት ተፈራ በ15ኛው ደቂቃ ወደ ግብነት ቀይሮት ሲዳማ መሪ ሆኗል።

ጨዋታው ገና ሩብ ሰዓት ሳያስቆጥር ግብ ያስተናገዱት ባህር ዳር ከተማዎች ኳስን ተቆጣጥረው መጫወት ቢቀጥሉም በሰንደይ ሙቱኩ እና ጊት ጋትኩት የሚመራውን የሲዳማን የተከላካይ መስመር ሰብሮ መግባት ተስኗቸዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ስድስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ግን በቀኝ መስመር በኩል የተገኘውን የመዓዘን ምት በመጠቀም ወሰኑ ዓሊ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር። ሲዳማ ቡናዎች በበኩላቸው ያገኙትን የመሪነት ዕድል አሳልፎ ላለመስጠት በመታተር ተጫውተዋል። የመጀመሪያው አጋማሽም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት በሲዳማ ቡና አንድ ለምንም መሪነት ተጠናቋል።

የአማካይ መስመራቸውን ለማጠናከር የተጫዋች ለውጥ አድርገው አጋማሹን የጀመሩት ባህር ዳር ከተማዎች በ50ኛው ደቂቃ ወሰኑ ከባዬ ተቀብሎ ወደ ግብ በመታው ኳስ አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪም በ57ኛው ደቂቃ ባዬ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን ያሻገረውን ጥሩ ኳስ የመሐል ተከላካዩ መናፍ ለመጠቀም ጥሮ መክኖበታል።

አጋማሹን በተሻለ የተነሳሽነት ስሜት የጀመሩት ባህር ዳር ከተማዎች የሲዳማ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረሳቸው በ60ኛው ደቂቃ ዋጋ ከፍሏቸዋል። በዚህ ደቂቃም ፍፁም ዓለሙ ከሚኪያስ ግርማ የተቀበለው ኳስ በመጠቀም ግብ አስቆጥሮ አቻ ሆነዋል። አቻ ከሆኑ ከአንድ ደቂቃ በኋላ የመዓዘን ምት ያገኙት ባህር ዳሮች ወደ ሳጥን ያሻሙትን ኳስ የሲዳማው የግብ ዘብ መሳይ አያኖ በሚገባ ሳይቆጣጠረው ቀርቶ የተገኘውን ኳስ ወሰኑ ዓሊ በጥሩ ቅልጥፍና ወደ ግብነት ቀይሮት መሪ ሆነዋል።

በእጃቸው የገባው ሦስት ነጥብ ያመለጣቸው ሲዳማ ቡናዎች ዳግም ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ማድረግ ጀምረዋል። በዚህም በ63ኛው ደቂቃ ቡድኑን በፍፁም ቅጣት ምት መሪ አድርጎ የነበረው ዳዊት ከቅጣት ምት ጥሩ ጥቃት ሰንዝሯል። በተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ የባህር ዳርን የግብ ክልል መጎብኘት ያልቻሉት ሲዳማዎች በ79ኛው ደቂቃ በተገኘ ሌላ የቅጣት ምት ጎል ለማስቆጠር ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። 

ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመሩት ደቂቃዎች መባቻ ላይም ቀድሞ በ65ኛው ደቂቃ የማስጠንቀቂያ የቢጫ ካርድ ያየው ሀብታሙ ገዛኸኝ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሳምሶን ጥላሁን ላይ ጥፋት ሰርቶ በሁለት የቢጫ ካርድ ከጨዋታው እንዲወጣ ሆኗል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክት በባህር ዳር ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ከአራት የአቻ ውጤቶች በኋላ ድል የተቀዳጁት ባህር ዳር ከተማዎች ነጥባቸውን ወደ 20 በማሳደግ ያሉበት 5 ደረጃ ላይ ፀንተው ተቀምጠዋል። በተቃራኒው በዛሬው ዕለት አራተኛ ተከታታይ ሽንፈታቸውን ያስተናገዱት ሲዳማ ቡናዎች በ13 ጨዋታ በሰበሰቡት 11 ነጥብ የወራጅ ቀጠናው ላይ ሆነው ቀጥለዋል።




© ሶከር ኢትዮጵያ