ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ንግድ ባንክ በጎል ተንበሽብሾ ወደ ድል ተመልሷል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የ13ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ ዛሬ ረፋድ 4፡00 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አቃቂ ቃሊቲን አገናኝቶ በንግድ ባንክ 5ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ የለመደውን አሸናፊነት አጥቶ የሰነበተው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊነቱን ዳግም ለማግኘት አቃቂ ቃሊቲዎች የራቀቸውን ድል ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡ የጎል ቀበኛዋን ሎዛ አበራን በጉዳት ለሁለተኛ ጊዜ ሳያሰልፍ ጨዋታውን ለመጀመር የተገደደው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጀማመሩ ፍፁም መረጋጋት የተሳነው ነበር፡፡ በተለይ የኃላ መስመር ተሰላፊዎቻቸው ይሰሩት የነበረው ስህተት ጎል እንዲቆጠርባቸው ምክንያት ሆኗል፡፡

የቤዛዊት ንጉሤን የግል ጥረቶች በመጠቀም ገና ከጅምሩ ከቀኝ መስመር በኩል ቶሎ ቶሎ መድረስ የቻሉት አቃቂዎች የመጀመሪያው አጋማሽ ሀያ ደቂቃዎች ከንግድ ባንክ በተቃራኒ ለነሱ ያማረ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ፌቨን መርከቡ በ4ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል የተገኘችን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ ሆና ካገኘችው በኃላ ወደ ግብ ስትሞክር በተከላካዩ ተደርባ ኳሷ ስትመለስ ቤዛዊት ንጉሴ አግኝታ ከጀርባዋ ቆማ የነበርችው ገነሜ ወርቁ ተጫዋቿን በሳጥን ውስጥ በመጎተቷ የዕለቱ ዋና ዳኛ ማርታ መለሰ የሰጠችውን የፍፁም ቅጣት ምት አምበሏ እና የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አማካይ አስናቀች ትቤሶ አስቆጥራው አቃቂን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡

ጎል ካስቆጠሩ በኃላ ጨዋታው ያለቀ መስሎ የታያቸው አቃቂዎች የኃላ ኃላ እጃቸውን ለንግድ ባንክ ሰጥተዋል፡፡ ንግድ ባንኮችም የነበረባቸውን ስህተቶች በሚገባ ያዩ በሚመስል መልኩ ተከላካይዋ ትዕግስት አበራን አስወጥተው አጥቂዋ ፎዚያ መሐመድን ማስገባታቸው ቡድኑ በሚገባ ለመነቃቃቱ ዋነኛ ቅያሪ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

በመስመር አጨዋወት ወደ አቃቂ የግብ ክልል ከአማካዩዋ ሰናይት ቦጋለ መነሻነት ወደ አረጋሽ ካልሳ የቀኝ መስመር ቦታ በማሻገር አልያም ወደ ረሂማ ዘርጋው ከግራና ቀኝ በኩል በረጅሙ በሚጣሉ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ ከቆመ ኳስ በዓለምነሽ ገረመው እና እመቤት አዲሱ የቅጣት ምቶች ወደ አቃቂ የግብ ክልል ቀስ በቀስ መጠጋት የጀመሩት ንግድ ባንኮች ከእነኚህም ሙከራዎች በኃላ በአረጋሽ ካልሳ አማካኝነት ተጨማሪ ሙከራን ማድረግ ችለዋል፡፡

34ኛው ደቂቃ ላይ የማጥቃት ኃይላቸውን በይበልጥ ለመጠቀም ሲታትሩ የተስተዋሉት ንግድ ባንኮች ተሳክቶላቸው ጎል አግኝተዋል፡፡አረጋሽ ካልሳ ከግራ በኩል ያሳለፈችውን ኳስ ረሂማ ዘርጋው በግንባር ገጭታ በማስቆጠር ክለቧን ወደ ጨዋታ መልሳለች፡፡ የአቃቂዎችን መዳከም በአግባቡ ወደመጠቀሙ የተሸጋገሩት ባንኮች 40ኛው ደቂቃ ላይ ገነሜ ወርቁ ከመሐል ሜዳው አሾልካ ስታሳልፍ ረሂማ ዘርጋው ለራሷ እና ለክለቧ ሁለተኛ ጎል ከመረብ አሳርፋ ወደ መልበሻ ክፍል ክለቦቹ አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ክለብ በሁሉም የሜዳ ክፍል ላይ ተሽለው የታዩ ሲሆን አሁንም የመስመሩን ኮሪደር በመታተር ሲፈነጩበት ተስተውሏል፡፡ በተለይ የአረጋሽ ካልሳ፣ ሰናይት ቦጋለ፣ ፎዚያ መሐመድ ሲያደርጉት የነበረው ድንቅ የሜዳ ላይ አጨዋወት ተጨማሪ ጎሎች በተዳከሙት አቃቂዎች ላይ ሊቆጠር ችሏል፡፡ 52ኛው ደቂቃ ረሂማ ዘርጋው የሰጣችን አረጋሽ ካልሳ ወደ ጎልነት ለውጣው የክለቧን የጎል መጠን ወደ ሶስት አሳድጋለች፡፡

56ኛው ደቂቃ ላይ ዳግም ከመስመር አረጋሽ ስታሻግር በቀኝ የግቡ አቅጣጫ የነበረችሁ ፎዚያ መሀመድ በአግባቡ ተቆጣጥራው አራተኛ ግብ ከመረብ ጋር አገናኝታለች፡፡ ትደግ ፍሰሀ ካደረገችው ሙከራ ውጪ በሁለተኛው አጋማሽ ብዙም ሜዳ የነበሩ የማይመስሉት አቃቂዎች 72ኛው ደቂቃ ሰናይት ቦጋለ በአስደናቂ መልኩ መሀል ለመሐል ስትሰጣት የአካዳሚ ፍሬ የሆነችሁ ፎዚያ መሐመድ ለራሷ ሁለተኛ ለንግድ ባንክ አምስተኛ ጎል አስቆጥራ ጨዋታው 5ለ1 በሆነ ውጤት ተደምድሟል፡፡ ንግድ ባንክ ዳግም ከሁለት ጨዋታዎች በኃላ ወደለመደው ያሸናፊነት መንገድ መመለስ ችሏል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ አረጋሽ ካልሳ በልሳን የሴቶች ስፖርት የጨዋታው ምርጥ በመባል ተመርጣለች፡፡

የ13ኛ ሳምንት ጨዋታ ከሰዓት ሲቀጥል መከላከያን ከ አዲስ አበባ 10፡00 ሲል ያገናኛል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ