ወልቂጤ ከተማን በአዲስ መልክ ለማዋቀር ተወስኗል

የወልቂጤ ከተማ የቦርድ አመራሮች ዛሬ ጠዋት ክለቡን ከመንግሥት ጥገኝነት በማውጣት በአዲስ መልኩ ለማዋቅር ከውሳኔ መድረሳቸው ታውቋል።

ዐምና ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወደ ዋናው የሀገሪቱ የሊግ እርከን አድገው በሊጉ ጥሩ ፉክክር እያደረጉ የሚገኙት ሠራተኞቹ የክለባቸውን ቁመና በአስተማማኝ መሠረት ላይ ለማሳረፍ ምክክር ሲያደርጉ ከርመዋል። ቡድኑን ወደፊት ለማራመድ ከመንግስት ጥገኝነት በማውጣት ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ መዋቅር በመዘርጋት ወደ አክሲዮን ማኅበርነት የሚቀየርበትን መንገድ ሲመረምር ቆይቶ የክለቡ ቦርድም ውሳኔዎችን ማሳለፉን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

በዚህ ጉዳይ ዙርያ ዛሬ ረፋድ ላይ የከተማው ከንቲባ አቶ እንዳለ ገብረመስቀል በበላይነት የመሩት ስብሰባ የተከናወነ ሲሆን 50+1 የሚሆነውን ድርሻ ለአክሲዮን ሽያጭ ገበያ ክፍት እንዲሆን፤ ቀሪው ደግሞ በከተማ መስተዳደሩ ባለቤትነት እንዲቀጥል ተወስኗል። በውሳኔው መሠረትም በ2014 ብዙ ለውጦችን ለማድረግ ያቀደው ክለቡ አክሲዮን ሽያጩን በዘንድሮ ዓመት እንደሚጀምርና ዝርዝር ጉዳዮችን በቀጣይ እንደሚገለፁ ታውቋል።

በተያያዘ ዜና ከክለቡ ኃላፊነታቸው ሊለቁ እንደሆነ ሲነገር የቆየው ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ አበባው ሰለሞን በኃላፊነታቸው እንደሚቆዩ ለማወቅ ተችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ