ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መከላከያ ከ አዲስ አበባ ከተማ ጋር ያለ ጎል ተለያይቷል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የ13ኛ ሳምንት ሦስተኛ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማን ከ መከላከያ አገናኝቶ 0ለ0 በሆነ አቻ ውጤት ፈፅመዋል፡፡

10፡00 ሲል በኢንተርናሽናል ዳኛ ፀሐይነሽ አበበ አማካኝነት የተጀመረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ብዙም ሳቢ ያልሆነ፤ አልፎም የረቡ ሙከራዎችን ሳንመለከት የተጠናቀቀ ነበር ማለት ይቻላል፡፡በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለቱም ክለቦች የተፈራሩ በሚመስል መልኩ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸው የቀረቡ ሲሆን የተለየ የጨዋታ ይዘትን ሲጠቀሙ አለመመልከታችን የጠሩ የጎል አጋጣሚዎችን እንዳንመለከት ዳርጎናል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበሩ ጨዋታዎች ይበልጡኑ በማጥቃቱ የተዋጣላቸው መከላከያዎች በዚህ ጨዋታ እቅዳቸውን ተግባራዊ ለማድረግ የተወሰነ ፍንጭ ማሳየት ቢችሉም የወጥነት እና የአጨራረስ ከፍተኛ ችግር ይስተዋልባቸው ስለነበር ያለሙትን ለመተግበር አላስቻላቸውም። በአንፃሩ በጥብቅ መከላከል በሚያገኙት ውስን ቀዳዳ ለማጥቃት ሲታትሩ የሚታዩት አዲስ አበባ ከተማዎች በቤተልሄም ሰማን ብቸኛ አጥቂነት ወደ ፊት ኳስን ይዘው ለመሄድ ቢሞክሩም ብዙም ስኬታማ ሊሆንላቸው ግን አልቻለም። 31ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሄም ሰማን በአዲስ አበባ ከተማዎች በኩል ያደረገቻት ሙከራ የመጀመሪያው አጋማሽ ልትጠቀስ የምትችል ሙከራ የነበረች ሲሆን ሌላ የተለየ ነገርን ሳንመለከት አጋማሹ ተገባዷል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ አሁንም የተለየ አቀራረብን ይዘው ሁለቱም ክለቦች ያልታዩ ሲሆን በተወሰነ ረገድ ግን ዋና አሰልጣኙ ስለሺ ብሩ እና ሌሎች አካላትን በቅጣት በማጣቱ በጊዜያዊ አሰልጣኝ እየተመራ መከላከያ የተሻለ ለመሆን ሞክሯል፡፡ምንም እንኳን ቡድኑ ተሽሎ የቀረበ ቢመስልም ደካማው የአጥቂ ክፍሉ የተገኙትን ጥቂት አጋጣሚዎች መጠቀም አልቻሉም። 55ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ በኩል በረጅሙ ህይወት ረጉ ያሻገረችውን ኳስ ሴናፍ ዋቁማ በግንባር ገጭታ የግቡ ቋሚ የግራ ብረት የመለሰባት ከሌሎች ሙከራዎች ሁሉ ቀዳማዊውን ቦታ ትይዛለች፡፡ ሌላኛው ሙከራ ህይወት ረጉ ከርቀት ሞክራ ግብ ጠባቂዋ ቤተልሄም ዮሀንስ የያዘችባት የቡድኑ ተጨማሪ ሙከራ ነበረች፡፡

ከመጀመሪያው አጋማሽ እንቅስቃሴያቸው መቀዛቀዝ ቢታይባቸውም በመከላከሉ ጠንካራ የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች 79ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት በተገኘ ኳስ ቤተልሄም ሰማን አግኝታ አምበሏ ትርሲት መገርሳ በቀጥታ ስትመታ ታሪኳ በርገና የያዘችባት ብቸኛ የጠራ ሙከራቸው ነበር፡፡ ጨዋታውም ብዙም ሳቢነት ሳይኖረው በዚህ መልኩ 0ለ0 ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የአዲስ አበባ ከተማዋ ተከላካይ አብነት ለገሰ የጨዋታው ምርጥ በመባል ተመርጣለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ