ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ ከተማ በግቦች ታጅቦ ድሬዳዋን ረቷል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የ13ኛ ሳምንት የሦስተኛ ቀኝ አራተኛ መርሃግብር ሀዋሳ ከተማን ከ ድሬዳዋ አገናኝቶ ሀዋሳ ከተማ 4ለ0 ድል አድርጓል።

ጨዋታው የተጠበቀውን ያህል በእንቅስቃሴ የጎሉ ነገሮችን ባያሳየንም ሀዋሳ ከተማዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት በድሬዳዋ ላይ የበላይነት ያሳዩበት ጨዋታ ነበር ማለት ይቻላል፡፡በተለይ የተረጋጋው የአማካይ ክፍል ኳሶችን ለመልሶ ማጥቃት በማደራጀት ምቹ እንዲሆኑ በማድረጉ የተዋጣላቸው ሆነው ታይተዋል፡፡13ኛው ደቂቃ በዚህ የጨዋታ መንገድ የተገኘን ኳስ የድሬዳዋ ከተማዋ ተከላካይ ሀሳቤ ሙሶ በአግባቡ መከላከል ባለመቻሏ መሳይ ተመስገን ከጀርባ አፈትልካ ወጥታ ከፊቷ ለነበረችው ዙፋን ደፈርሻ ሰጥታት አማካዩዋ ኳሷን ሁለቴ ብቻ ገፋ በማድረግ በድንቅ አጨራረስ አስቆጥራ ሀዋሳን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡

የድሬዳዋ ከተማ የጨዋታ መንገድ ብዙም ለተጋጣሚ ፈታኝ መስሎ ባይታይም ከቆሙ ኳሶች በሚገኙ አማራጮች የማግባት አጋጣሚን ለመጠቀም ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡ በተለይ አጥቂዋ ፀጋነሽ ወራና ከቅጣት ምት እና ከማዕዘን ምት በቀጥታ ወደ ጎል ስትመታቸው የነበሩ ኳሶች አደገኛ ቢሆኑም የሀዋሳ ግብ ጠባቂ ዓባይነሽ ኤርቄሎ በቀላሉ ስታወጣቸው ተስተውሏል፡፡በተቃራኒው በሙከራ ረገድ ሻል ብለው ሲታዩ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች በተደጋጋሚ በቀላሉ ለስህተት ተጋላጭ የነበረውን የድሬዳዋን የተከላካይ ክፍል ሲረብሹ ተመልክተናል፡፡ መሳይ ተመስገን ተከላካዮችን አታላ በማለፍ በተደጋጋሚ አክርራ ሂሩት ደሴን ስትፈትን ያስተዋል ሲሆን በተለይ ደግሞ 41ኛው ደቂቃ መቅደስ ማሞ መሀል ለመሀል አሾልካ ሰጥታ መሳይ ተመስገን ወደ ሳጥን ገፍታ ገብታ ወደ ጎል የመታቻትን ኳስ ከግቁ ጠርዝ ሀሳቤ ሙሶ ሁለተኛ ጎል የምትህነዋን አጋጣሚ እንድምንም አትርፋታለች፡፡

ከእረፍት መልስ ሀዋሳ ከተማዎች በርካታ አጋጣሚዎችን አግኝተው በአግባቡ መጠቀም የቻሉበት ነበር፡፡ በተለይ በመስመር አጨዋወት ወደ ፊት በመሄድ በኃላም ወደ አጥቂዎች በማሻገር ጎል ለማስቆጠር የመረጡት የጨዋታ መንገድ ነበር፡፡ ከወትሮው ፈጣን የሽግግር አጨዋወታቸው የተቀዛቀዙት ድሬዳዋዎች ከፀጋነሽ ወራና የቅጣት ምት አልያም ከርቀት በሚገኙ ጥቂት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ካልሆነ የተደራጀ የጨዋታ ሲስተም ሲጠቀም አልተመለከትንም፡፡ ይሁን እንጂ በሚገባ የመልሶ ማጥቃትን ተግባር ላይ ያዋሉት ሀዋሳዎች 60ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረዋል፡፡ ከግራ የድሬዳዋ የግብ ክልል ወደ መስመር በኩል ካደላ ቦታ ላይ የተገኘን የቅጣት ምት መሳይ ተመስገን ስታሻማ የድሬዳዋ ግብ ጠባቂ ሂሩት ደሴ በአግባቡ መቆጣጠር ባለመቻሏ አጠገቧ የነበረችሁ ፀሀይነሽ ጁላ ከመረብ አሳርፋ የጎል መጠኑን ወደ ሁለት አሳድጋለች፡፡

በመሳይ ተመስገን አስደናቂ ብቃት በመታገዝ በቀሩት ደቂቃዎች አሁንም በሙከራ ረገድ ብልጫን ወስደው የተንቀሳቀሱት ሀዋሳዎች 70ኛው ደቂቃ ሌላ ግብ አክለዋል፡፡ መሳይ ተመስገን በተመሳሳይ ሁለተኛው ጎል ሲቆጠር የቅጣት ምት በተሰጠበት ቦታ ላይ በግምት 40 ሜትር ርቀት ላይ አክርራ መታ እጅግ አስገራሚ ጎል ከመረብ አሳርፋለች፡፡ 86ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው ዓይናለም አሳምነው ከቀኝ የድሬደዋ ግብ ክልል ካሰች ፍሰት የሰጠቻትን ኳስ አንድ ጊዜ ብቻ ካቆመች በኃላ በቀጥታ በቅጽበት መታው አራተኛ ጎል ለሀዋሳ አግብታለች፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ በጭማሪ ሰአት መሳይ ተመስገን ያለቀላት ኳስ አግኝታ መጠቀም ሳትችል በመቅረቷ ጨዋታው 4ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ መሳይ ተመስገን የጨዋታው ምርጥ ተብላ ተመርጣለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ