ቅድመ ዳሰሳ | ሰበታ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

የአስራ አምስተኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ መርሐ-ግብርን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በአስራ አራተኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ሁለት አቻ ተለያይተው ለዚህኛው የጨዋታ ሳምንት እየተዘጋጁ የሚገኙት ሰበታ ከተማዎች ከሁለት የአቻ ውጤቶች በፊት ወልቂጤ ከተማ ላይ የተቀዳጁትን ድል ለመድገም እና በደረጃ ሠንጠረዡ ከበላያቸው ከሚገኘው የነገው ተጋጣሚያቸው በልጦ ለመቀመጥ ወደ ሜዳ ይገባሉ። በተቃራኒው በአስራ አራተኛ ሳምንት አራፊ ቡድን የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች ከተከታታይ የአቻ እና የሽንፈት ውጤቶች ለመላቀቅ ድልን አስበው ለነገው ጨዋታ ይቀርባሉ።

በአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሚመሩት ሰበታ ከተማዎች ኳስን ለመቆጣጠር የተለየ ፍላጎት ካላቸው ቡድኖች መካከል አንዱ ናቸው። በተለይም ኳስ መጫወት የሚያስችል ብቃት ያላቸው የአማካይ መስመር ተጫዋቾቹ የጨዋታው የኳስ ቁጥጥር የሀይል ሚዛን ወደ እነርሱ እንዲሆን ጥረትን ሲያደርጉ ይታያል። እርግጥ ቡድኑ ኳስን በሚቆጣጠርበት ደረጃ ጎሎችን በክፍት ጨዋታ ለማስቆጠር የሚቸገር ቢሆንም ተጋጣሚው ኳስን የሚያገኝበትን ጊዜ ቀንሶ ግብ ክልሉ ቶሎ ቶሎ እንዳይጎበኝ ይጥራል። ከዚህ ውጪ አብዛኛው የቡድኑ የግብ ማስቆጠሪያ አማራጮች የቆሙ እና ተሻጋሪ ኳሶች ሲሆኑ ይስተዋላል። ከዚህ መነሻነትም በነገውም ጨዋታ ቡድኑ ባለፉት ጨዋታዎች ጥሩ የሆነበትን የቆመ ኳስ አጠቃቀም ተጠቅሞ ተጋጣሚው ላይ ጫና ለመፍጠር ይሞክራል ተብሎ ይታሰባል።

በሊጉ ብዙ የአቻ ውጤቶችን (6) በማስመዝገብ ቀዳሚ የሆነው ሰበታ በነገው ጨዋታ ከጉዳት የተመለሰውን አብዱልሀቪዝ ቶፊቅ ማግኘቱ ለቡድኑ መልካም ዜና ነው። በተለይም ተጫዋቹ የአማካይ መስመሩን ከአጥቂ መስመሩ ለማገናኘት የሚጥርበት መንገድ ቡድኑን ተጠቃሚ ሊያደርግ ይችላል። በተቃራኒው ግን ካስቆጠራቸው የግብ ብዛቶች የበለጠ ግቦችን ያስተናገደው የቡድኑ የኋላ መስመር በነገው ጨዋታ እንዳይፈተን ያሰጋል። በተለይም ወደ መሀል ሜዳው ተጠግተው ከሚከላከሉት ተጫዋቾች ጀርባ ያለውን ሰፊ ቦታ ሀዋሳዎች ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ይገመታል።

ሰበታ አብዱልሀፊዝ ቶፊቅን ከጉዳት መልስ ሲያገኝ ፋዑድ ፈረጃን እና ታደለ መንገሻን ግን በጉዳት ነገ መጠቀም አይችልም።

ከእረፍት የተመለሱት ሀዋሳ ከተማዎች በሊጉ ላይ ወጥ ብቃት ማሳየት ከከበዳቸው ክለቦች መካከል ይጠቀሳሉ። እርግጥ ቡድኑ በደረጃ ሠንጠረዡ ከፍ ብለው ከሚገኙ ክለቦች ጋር ሲጫወት ጥሩ እንቅስቃሴ ቢያሳይም በአንዳንድ ጨዋታዎች ግን በወረደ አቀራረብ ወደ ሜዳ ይገባል።

ሀዋሳ ከተማ ከእረፍቱ በፊት በነበረው የድሬዳዋው ጨዋታም “አግባብነት” የሌለው ጥንቃቄ አዘል አጨዋወት በመከተል ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። በነገው ጨዋታም ግን እንደ ድሬዳዋው ጨዋታ ሁለት የተከላካይ አማካዮችን በመጠቀም የተጋጣሚውን የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ለመቆጠቀጠር እንደሚጥር ይገመታል። ከምንም በላይ ደግሞ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ሜዳ ተመልሶ የተጎዳው ነገርግን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ በሆነው አለልኝ አዘነ የአማካይ መስመራቸውን አጠናክረው የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው ለማድረግ ይሞክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በፈጣኖቹ አጥቂዎች የሚመራው የቡድኑ የፊት መስመር በነገው ጨዋታ ለሰበታዎች ከባድ ጊዜን እንደሚሰጥ ይታሰባል። ከምንም በላይ በሽግግሮች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የማያቅተው ቡድኑ የሰበታን ተጫዋቾች የኳስ ቅብብል እያቋረጠ ተጋጣሚ ላይ ፍጥነት የታከለበት ጥቃት ሊሰነዝር ይችላል። በተጨማሪም በድሬዳዋው ጨዋታ ከጉዳት ተመልሶ ደካማ ብቃት ያሳየው ደስታ በነገው ጨዋታ ጥሩ የሚሆን ከሆነ ለቡድኑ ጥሩ የማጥቂያ አማራጭ በግራ መስመር በኩል የሚሰጥ ይሆናል። ምንም ቢሆን ምንም ግን በአንዳንድ ጨዋታዎች የሚታየው የመዘናጋት እና የትኩረት ማጣት ችግር ነገ የማይቀረፍ ከሆነ ቡድኑ አደጋ ውስጥ ሊገባ ይችላል።

ሀዋሳ አለልኝ አዘነ እና ዳንኤል ደርቤ ከጉዴት ሲመለሱለት ወንድምአገኝ ማዕረግ እና ኤፍሬም ዘካሪያስ ግን አሁንም ባለማገገማቸው ከነገው ፍልሚያ ውጪ ናቸው ተብሏል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ ለሰባት ያክል ጊዜያት ተገናኝተው ሰበታ 4 በማሸነፍ ቀዳሚ ነው። ሀዋሳ ደግሞ 1 ጊዜ ብቻ ድል አስመዝግቧል። በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ግን ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል።

– በስድስቱ ጨዋታዎች ሰበታ 8 ሲያስቆጥር ሀዋሳ 5 አስቆጥሯል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሰበታ ከተማ (4-3-3)

ምንተስኖት ዓሎ

ጌቱ ኃይለማርያም – መሳይ ጻውሎስ – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

ዳዊት እስጢፋኖስ – መስዑድ መሀመድ – አብዱልሀቪዝ ቶፊቅ

ያሬድ ሀሰን – ፍፁም ገብረማርያም – ቡልቻ ሹራ

ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)

ሶሆሆ ሜንሳህ

ዳንኤል ደርቤ– ምኞት ደበበ – ላውረንስ ላርቴ – ደስታ ዮሐንስ

ሄኖክ ድልቢ – ዳዊት ታደሰ – አለልኝ አዘነ

ኤፍሬም አሻሞ – መስፍን ታፈሰ – ብሩክ በየነ


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ