ወላይታ ድቻ ሀዲያ ሆሳዕናን 2-0 በማሸነፍ በመልካም አቋሙ ገፍቶበታል።
ሀዲያ ሆሳዕና ጅማን ከረታበት ጨዋታ አንፃር ሱለይማን ሀሚድ እና ብሩክ ቃልቦሬን በፀጋሰው ደመሙ እና አዲስ ህንፃ ምትክ በመለወጥ ለጨዋታው ሲቀርብ ወላይታ ድቻዎች አዲስ ፈራሚዎቹ አስናቀ ሞገስ እና ነፃነት ገብረመድህንን ወደ አሰላለፍ በማምጣት አበባየሁ ሀጪሶ እና ፀጋዬ ብርሀኑን አሳርፈዋል።
የመጀመሪያው አጋማሽ እንደተጠበቃውም የቡድኖቹ የመከላከል ጥንካሬ በሰፊው የተስተዋለበት ነበር። 10ኛው ደቂቃ ላይ አስናቀ ሞገስን በጉዳት አጥተው ፀጋዬ ብርሀኑን ለመተካት የተገደዱት ድቻዎች በቅብብሎች በሀዲያ ሳጥን አራቢያ የሚደርሱባቸው አጋጣሚዎች ቢታዩም ግልፅ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። አነስ ባለ ቁጥር ጎል ጋር ይደርሱ የነበሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ጥቃትም አቅሙ አንሶ ተመልክተነዋል። በሁለቱም ጎሎች አቅጣጫ በዳዋ ሆቴሳ እና ቢኒያም ፍቅሬ አልፎ አልፎ የተደረጉ ሙከራዎች ኢላማቸውን ሳይጠብቁ ሲቀሩ ቡድኖቹ ከቆሙ ኳሶችም የተለየ ተፅዕኖ ሳይፈጥሩ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ከዕረፍት መልስም የቡድኖቹ እንቅስቃሴዎች በሁለቱ ሳጥኖች መካከል ተገድቦ ከሙከራዎች ርቀው የቆዩ ሲሆን ወላይታ ድቻዎች በሰሞንኛው የቆመ ኳስ አጠቃቀም ጠንካራ ጎናቸው መነሻነት በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ሁለት ጎሎችን በማከታተል አስቆጥረዋል። 64ኛው ደቂቃ ላይ የያሬድ ዳዊትን የቀኝ መስመር ቅጣት ምት ፀጋዬ ብርሀኑ ወደ ግብነት ሲቀይረው 68ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከማዕዘን በተነሳ እና ቢኒያም ፍቅሬ ሞክሮት በሄኔክ አርፌጮ የተጨረፈውን ኳስ አግኝቶ ቸርነት ጉግሳ ሁለተኛ ግብ አክሏል።
በቀሩት ደቂቃዎች ወላይታ ድቻዎች በራሳቸው የግብ ክልል መቆየትን ሲመርጡ ሀዲያ ሆስዕናዎች ተጭነው ተጫውተዋል። ሆኖም ከሦስተኛው የሜዳ ክፍል መግቢያ ላይ የሚጣሉ የነብሮቹ ኳሶችን በማቋረጥ አልፎ አልፎም ኳሱን ለመያዝ በመሞከር ጨዋታውን መጨረስ ችለዋል። ለመልሶ ማጥቃት በእጅጉ ተጋልጠው የነበሩት ሆሳዕናዎች ጥቃታቸው የግብ ልዩነቱን ሊያጠብላቸው ሳይችል ቀርቶ ከሰባተኛው ሳምንት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሸነፍ ተገደዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ