የአሠልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 1-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ

በባከነ ሰዓት በተቆጠረ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ አንድ ለምንም ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ አሠልጣኞች አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

ስለ ጨዋታው?

ዛሬ ትክክለኛው ፋሲል ከነማ ሜዳ ውስጥ ነበር። በደረጃ ሰንጠረዡ ከሚከተሉን ቡድኖች ነጥብ መውሰድ ትልቅ ነገር ነው። በጨዋታው አጀማመራችንም ጥሩ ነበር። የልፋታችን ውጤት ነው በመጨረሻም ውጤት ያስገኘን። የዛሬው ሦስት ነጥብ ለእኛ ወሳኝ ነበር። በጣምም ደስ ብሎኛል። ለመላ ደጋፊዎቻችን እንኳን ደስ አላችሁ ማለትም እፈልጋለሁ።

በጭማሪ ደቂቃ ስለተገኘችው የፍፁም ቅጣት ምት?

አንዳንድ ጊዜ በጨዋታ እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች ሊኖሩ ይችላሉ። እዚህ ደረጃ መድረሳችን እራሱ ትልቅ ነገር ነው። በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ ሙከራ አድርገን ነበር። ነገርግን እነዛን መጠቀም አልቻልንም። በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ጊዮርጊሶችን ለመቆጣጠረ የዘየድነው ዘዴ ጠቅሞናል። ውጤቱም ይገባናል ብዬ ነው የማስበው።

ስለ ዋንጫ ፉክክሩ?

ከተከታያችን ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት አስፍተን መያዛችን ለእኛ ትልቅ ነገር ነው። በራስ መተማመን ይሰጠናል። ነገርግን ገና 11 ጨዋታ አለ። ይሄንን አስጠብቆ ለመሄድ ትልቅ ስራ ይጠብቀናል። በቀጣይ ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነው የምንጫወተው። በዛም ጨዋታ በተሻለ ቅርፅ ለመቅረብ እንሞክራለን። በአጠቃላይ ትልቅ ነጥብ ነው ዛሬ ያገኘነው።

ማሒር ዴቪድስ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለ ቡድኑ እንቅስቃሴ?

ዛሬ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ጥሩ ነበርን። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ጥሩ ዕድሎችን ፈጥረን ነበር። በሁለተኛው አጋማሽም ጥሩ ነበርን። ነገርግን በፍፁም ቅጣት ምት ባስቆጠሩት ጎል አሸነፉን። በአጠቃላይ ምርጡ ቡድን ነው የተሸነፈው።

ስለ ፍፁም ቅጣት ምቱ?

በፍፁም ቅጣት ምቱ ላይ ምንም ሀሳብ መስጠት አልችልም። ምስሉን ማየት አለብኝ።

ከመሪው ጋር ስላላቸው የነጥብ ልዩነት መስፋት?

የዛሬው ጨዋታ የዋንጫውን ባለቤት አይወስንም። ዛሬ እንዴት እንደተጫወትን አይታችኋል። እነሱ ላይ ጫና ማሳደራችንን እንቀጥላለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ