ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ወላይታ ድቻ

የነገውን ሁለተኛ ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን በዳሰሳችን እንደሚከተለው ተመልክተናል።

ጨዋታው ምንም እንኳን በደረጃ ሰንጠረዡ ቢራራቁም በሰሞንኛ አጨዋወታቸው መመሳሰል የሚታይባቸውን ቡድኖች የሚያገናኝ ነው። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች መረባቸውን ያላስደፈሩት እና ባሳለፍነው ሳምንት በውስን ተጠባባቂ ተጨዋቾች ለመጠቀም ተገደው ግን ደግሞ ማሸነፍ የቻሉት ሀዲያ ሆሳዕና እና ወላይታ ድቻ ነገ እርስ በእርስ ይፋለማሉ።

አንድ ግብ ብቻ ካስቆጠሩባቸው የአራት ጨዋታዎች የአቻ ውጤት በኋላ በጅማ አባ ጅፋር ላይ ድል የቀናቸው ሀዲያ ሆሳዕናዎች ነገ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሊያስቀምጣቸው የሚችለውን ድል ፍለጋ ወደ ሜዳ ይገባሉ። አሁንም በመከላከል ጥንካሬያቸው የገፉበት የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ልጆች ከቀደመው ጊዜ በተሻለ በተጋጣሚ ሳጥን አቅራቢያ መታየት ቢጀምሩም የመጀመሪያውን አስፈሪ የፊት መስመር ጉልበታቸውን መልሰው አላገኙም። እርግጥ ነው ቡድኑ በፊት በተለያዩ ምክንያቶች ጠንካራው ስብስቡ ሳስቶ መቅረቡ አማራጮችን ያሳጣው ቢሆንም ነገ ግን ከቴዎድሮስ በቀለ እና ሳሊፉ ፎፋና በቀር ቀሪዎቹ ተጨዋቾቹ የሚመለሱለት መሆኑ መሰማቱ ነገሮችን አስተካክሎ እንዲቀእብ ሊረዳው ይችላል።

በድኑ የሚያደርጋቸው ሙከራዎች በአመዛኙ በፈጣሪ አማካዩ ካሉሻ አልሀሰን ሲደረጉ መታየቱ እና በማጥቃት ወቅት በቂ ቁጥር ያላቸው ተሰላፊዎቹን አደጋ ዞን ላይ አለማድረሱ ነገ የሚደገም ከሆነ ጥሩ የመከላከል ብርታት ላይ ካለው ተፎካካሪው ክፍተቶችን የማግኘት ዕድሉ አናሳ ነው። በንፅፅር ግን የሀዲያ ሆሳዕና የቀኝ ወገን ነገም በተሻለ ሁኔታ ጥሩ የማጥቃት አማራጭ ሆኖ እንደሚቀርብ ይገመታል። የሱለይማን ሀሚድ ከአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት መመለስም ይህንን መስመር ይበልጥ የሚያጠናክረው ይሆናል።

ካለፉት አራት ጨዋታዎች አስር ነጥቦችን የሰበሰቡት ወላይታ ድቻዎች የውድድሩ ምርጥ አቋማቸው ላይ ይገኛሉ። ከወራጅ ቀጠናው በመላቀቅም ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ እያደረጉት ያሉትን ጉዞ ለማሳመር ነገ ሙሉ ነጥቦችን ማሳካት በእጅጉ አስፈላጊያቸው ይሆናል። ካሉበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ለጥንቃቄ ከፍ ያለ ትኩረት የሚሰጡት ድቻዎች በወጣት ተሰላፊዎቻቸው ፍጥነት ላይ የተመሰረተው መልሶ ማጥቃት ዋነኛው የግብ መፍጠሪያ መንገዳቸው መሆኑ ነገም የሚቀጥል ይመስላል። በዚህ ረገድ በተመሳሳይ ድክመት የሚታይበት የተጋጣሚያቸውን የፊት መስመር ለማቆም ላያንሱ ቢችሉም ከግብ ክልሉ እምብዛም ሳይርቅ የሚከላከለውን የሀዲያን የኋላ ክፍል በመልሶ ማጥቃት መረበሽ መቻላቸው ግን አጠራጣሪ ነው።

ድቻዎች በንፅፅር ደካማ የመከላከል ክፍል ካለው ሱዳማ በና ጋርም የማጥቃት ሽግግራቸውን አፍጥነው ሦስተኛው ሜዳ ላይ ከመድረሳቸው በፊት የቅብብል ስህተቶቻቸው እና የማጥቃት መስመር አመራረጣቸው የመልሶ ጥቃታቸውን ጉልበት ሲቀንሰው መታየቱ ለነገም የሚያሰጋቸው ጉዳይ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ግን ቡድኑ በቅርብ ጨዋታ ጎሎች ያስገኘለት እና በሙከራ ረገድም አስፈሪ ሲያደርገው የሚታየው የቆሙ ኳሶች አጠቃቀሙ ሌላ ግብ የማግኛ አጋጣሚን የሚፈጥርለት ሲሆን ይህን ለማሳካትም ከተጋጣሚው የሚገጥመው ፈተና ቀላል አይሆንም። ከዚህ አኳያ የቡድኑ ጥንካሬ መገለጫ የሆነው ደጉ ደበበ ለነገው ጨዋታ መድረስ አጠራጣሪ ሆኗል። ከእርሱ ውጪም በማገገም ላይ የሚገኘው ስንታየሁ መንግሥቱ በጉዳት በረከት ወልዴ ደግሞ በቅጣት ጨዋታው ያልፋቸዋል። በርከት ያሉ አዲስ ፈራሚዎቹም ዝውውራቸው እስከ ነገ ማለዳ ከፀደቀ ብቻ የጨዋታው ተካፋይ ይሆናሉ።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ በድኖች ከዚህ ቀደም ለሦስት ጊዜያት ተገናኝተው አንዴም አቻ ያልተለያዩ ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕና ሁለቴ ወላይታ ድቻ አንዴ ድል አድርገዋል። በጨዋታዎቹ ሀዲያ ሰባት ድቻ ደግሞ አራት ግቦችን ከመረብ አገናኝተዋል።

– በአንደኛው ዙር ባደረጉት ግንኙነት ሀዲያ ሆሳዕና 2-1 አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)

መሐመድ ሙንታሪ

ሱሌይማን ሀሚድ – ኢሴንዴ አይዛክ – ተስፋዬ በቀለ – ሄኖክ አርፌጮ

ካሉሻ አልሀሰን – ተስፋዬ አለባቸው – አማኑኤል ጎበና

ዱላ ሙላቱ – ዳዋ ሆቴሳ – ቢስማርክ አፒያ

ወላይታ ድቻ (4-3-3)

መክብብ ደገፉ

አናጋው ባደግ – አንተነህ ጉግሳ – ደጉ ደበበ – ያሬድ ዳዊት

መሳይ አገኘሁ – አበባየሁ አጪሶ – እንድሪስ ሰዒድ

ፀጋዬ ብርሀኑ – ቢኒያም ፍቅሬ – ቸርነት ጉግሳ


© ሶከር ኢትዮጵያ