“ዓምና የተናገርኩትን ዘንድሮም ለጅማ እደግመዋለሁ” ሳዲቅ ሴቾ

አንዴ ብቅ አንዴ ጥፍት እያለ በሊጉ በጎል አግቢነት ስሙ የሚጠራው ሳዲቅ ሴቾ አሁናዊ ብቃቱን አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

በቀድሞ አጠራሩ ብሔራዊ ሊግ በተሰኘው ውድድር በሼር ኢትዮጵያ ክለብ ባሳየው መልካም እንቅስቃሴ በአሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች ምርጫ ኢትዮጵያ ቡናን ተቀላቅሎ ለሁለት ዓመታት ከቆየ በኋላ ወደ ሀዋሳ ከተማ፣ በማስከተል ለአዲስ አበባ ከተማ በኃላም ለወልቂጤ መጫወት ችሏል። ዘንድሮ ጅማ አባ ጅፋርን የተቀላቀለው ሳዲቅ በኢትዮጵያ ቡና የመጀመርያ ዓመት ያሳየውን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በሌሎች ክለቦች መድገም ባይችልም በወልቂጤ መልካም ጊዜ አሳልፎ አሁን በተለይ ከአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ወደ አባጅፋር መምጣት በኃላ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ በዛሬው ወሳኝ ጨዋታም የቡድኑን የመጀመርያ ጎል በማስቆጠር መነቃቃት አሳይቷል።

ሳዲቅ ስለ ወቅታዊ አቋሙ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

” ብዙ ጊዜ እየታየሁ የምጠፋው የተጫወትኩባቸው ክለቦች የሚከተሉት አጨዋወት ነው። አብዛኛው መከላከልን መሠረት ያደረገ በመሆኑ ጎል የማግባት ዕድል አይገኝም። የማጥቃት አጨዋወት የሚከተል ቡድን ካገኘህ ግን ጎል ታገባለህ። ስለዚህ አሰልጣኙ የሚከተለው አጨዋወት ይወስነዋል። ተከላከል ከተባልክ የመከላከል ሥራህን ትወጣለህ ። ቡና ቤት እያለሁ የበለጠ ወደ ማጥቃቱ ያመዘነ አጨዋወት በመኖሩ ጎል ለማስቆጠር የቀረብኩ ነበርኩ። ከዛ በኃላ ትንሽ አስቸጋሪ ነበር። በጅማ አሁን ነው አሰልጣኝ ፀጋዬ ከመጣ በኃላ ነው ማጥቃት፤ ወደ ጎልም መድረስ የጀመርነው። ለዚህም ነው ወደ ጎል ማስቆጠር የተመለስኩት። በአጠቃላይ የተለያየ ቡድን ስትቀያይር እንደየ ቡድኑ አጨዋወቱ ስለሚቀያየር የኔንም አቅም ገድቦት ቆይቷል። መሐል ላይ አጋጥሞኝ የነበረው ጉዳት እንዳለ ሆኖ።

” የአሰልጣኝ ፀጋዬ ወደ ቡድኑ መምጣት ሙሉ ለሙሉ ራሴን አውጥቼ እንድጫወት ጠቅሞኛል። ጨዋታውን ካያችሁ ማጥቃትን መሠረት ያደረገ አጨዋወት ላይ ትኩረት ማድረጋችን ጠቅሞኛል። እስክንዋሀድ ድረስ ጊዜ ቢፈልግም ወደፊት የእርሱ አጨዋወት ስንረዳው የተሻለ ቡድን ይወጣናል። እኔም ወደ ትክክለኛው አቋም እመለሳለሁ።

” ጎሉ ያስቆጠርኩበት መንገድ በትክክል በምንፈልገው አጨዋወት የመጣ ነው። አንድ አጥቂ በተደጋጋሚ ኳስ ሲያገኝ ጎል የማግባት ዕድሉ ይሰፋል። ወንድማገኝ ኳሷን ክሮስ ሲያደርግልኝ አቋቋሜን በመጠበቅ ጎል ለማስቆጠር ችያለሁ።

” ትዝ ይላችሁ ከሆነ ዓምና በዚህ ሰዓት ወልቂጤ እያለሁ በወራጅ ቀጠናው አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ነበር። ያኔ ከድሬዳዋ ጋር ስንጫወት እኔ ነበርኩ ጎል አስቆጥሬ ቡድኑ ከወራጅ ቀጠና እንዲወጣ ያስቻልኩት። ዛሬም ጅማ የመውረድ ነገር አይኖርበትም። ምክንያቱም የራሳችን አጨዋወት ካለን የመትረፍ ዕድላችን ሰፊ ነው። ዓምና ወልቂጤ እያለው ቡድኑ እንደማይወርድ ለሶከር ኢትዮጵያ ጎል ካገባው በኋላ ተናግሬ ነበር። አሁንም ዓምና የተናገርኩትን ዘንድሮም ለጅማ እደግመዋለው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ