በነገ ረፋዱ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።
በዕኩል ሰባት ነጥቦች በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኙት አዳማ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ከወራጅ ቀጠናው ባያስወጧቸውም ለቀጣይ ጨዋታዎቻቸው መነሳሻ የሚሆኑ ሦስት ነጥቦችን ፍለጋ ወሳኝ የሆነው ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
አዳማ ከተማ ከበርካታ ለውጦች በኋላ የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎቹን ይጀምራል። ክለቡ ከቀናት በፊት አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን በዋና አሰልጣኝነት ሲሾም የዝውውር መስኮቱን መከፈት ተከትሎም እስካሁን ሰባት ተጫዋቾችን በእጁ አገብቷል። አሚኑ ነስሩ ፣ ሚሊዮን ሰለሞን ፣ ኤልያስ አህመድ ፣ ኤልያስ ማሞ ፣ ሰይፈ ዛኪር ፣ ያሬድ ብርሀኑ እና ሀብታሙ ወልዴ አዲሶቹ የአዳማ ከተማ ተጨዋቾች ሆነዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ሱለይማን መሀመድ ፣ ፀጋዬ ባልቻ ፣ ብሩክ ቦጋለ ፣ መጃይድ መሀመድ እና አክሊሉ ተፈራ ከክለቡ ጋር የተለያዩ ተጨዋቾች ሆነዋል። ቀደም ብለው የአሰልጣኝ ለውጥ ያደረጉት ጅማ አባ ጅፋሮች ደግሞ እስካሁን ባለው ሂደት አሌክስ አሙዙ ፣ አማኑኤል ተሾመ እና ራሂም ኡስማኖን ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል።
አዲሱ ክለባቸውን ከያዙ የቀናት ዕድሜ ላይ የሚገኙት አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ከአንድ ቀን የልምምድ ቆይታ በኋላ ብቻ ነው የነገውን ጨዋታ የሚያደርጉት። እስካሁን በነበረው የውድድሩ ሂደት በሁሉም ጨዋታ ላይ የተሳተፉት የቡድኑ ተቀዳሚ ተመራጭ የመሀል ተከላካዮች እና የተከላካይ አማካዩ በሌሉበት የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ማከናወናቸው ደግሞ ጨዋታውን ይበልጥ የሚያከብድባቸው ይሆናል። በተቃራኒው ሲታይ ደግሞ ተጋጣሚያቸውም በአዲስ የቡድን ግንባታ ሂደት ላይ መገኘቱ በመጠኑ መልካም ዜና ሊሆንላቸው ይችላል።
ከአሰልጣኙ ጋር በነበረን ቆይታ እንደተረዳነውም አሁን ካለው ሁኔታ አንፃር የቡድኑን በርካታ ክፍተቶች ለመድፈን አስቸጋሪ በመሆኑ ጥንቃቄ ላይ የተመሰረተ አቀራረብ ሊኖራቸው እንደሚችል ይገመታል። በእርግጥ ከጨዋታው ውጤት አስፈላጊነት አንፃር ቡድኑ በተለይም የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ካገኘ በፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ፍጥነት ላይ ተመስርቶ ለመጠቀም እንደሚሞክር ይጠበቃል። አማራጮቹ እጅግ በጠበቡበት ቦታዎች ላይም አዳዲሶቹ ፈራሚዎቹን የመጠቀም ግዴታ ውስጥ ሊገባ ይችላል።
ከአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም መምጣት በኋላ የመጀመሪያውን ድል ያሳካው ጅማ አባ ጅፋር ሌላ አንድ ነጥብ ለማሳካት በተቃረበበት ጨዋታ በጨረሻ ሰዓት በሀዲያ ሆሳዕና ሽንፈት አስተናግዶ ለነገው ጨዋታ ደርሷል። የቡድን ተነሳሽነቱ ተሻሽሎ የታየው ጅማ አባ ጅፋር ጥብቅ መከላከልን መርጦ እንኳን ስህተት የሚሳረበት አጋጣሚ አሁንም አብሮት እንዳለ ያሳየው የሀዲያው ጨዋታ ነገም ተመሳሳይ ክስተት እንዳይገጥመው ትምህርት የሰጠው ነበር።
በማጥቃቱም ረገድ የመጨረሻ ዕድሎችን የማባከን ችግሩ ዋጋ ሲያስከፍለው ታይቷል። ቡድኑ ነገ አዳማን ሲገጥም በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ እና የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ያለው አቀራረብን ሊከተል እንደሚችል ቢታመንም እነዚህ ደካማ ጎኖቹ ግን ኳስ እና መረብን እንዳያገናኝ ቀድሞ ግብ ከተቆጠረበት ደግሞ መልሶ ማገገም እንዳይከብደው ሊያደርጉት ይችላሉ። ቡድኑ በሲዳማው ጨዋታ የነበረው ተጋጣሚን ከግብ ክልሉ ርቆ እንዲንቀሳቀስ የማድረግ እና በሜዳው ስፋት ክፍተቶችን በንቃት የመዝጋት ብቃቱን በነገው ጨዋታም መልሶ ማግኘት ይጠበቅበታል።
አዳማ ከተማ መሀል ተከላካዮቹ ትዕግስቱ አበራን በጉዳት ደስታ ጊቻሞን ደግሞ በቅጣት ሲያጣ ሌላው ወሳኝ አማካይ ደሳለኝ ደባሽም በአምስት ቢጫ ካርድ ሳቢያ ጨዋታው ያልፈዋል። በጅማ አባ ጅፋር በኩል ብዙአየሁ እንዳሻው ጉዳት ላይ ሲገኝ ከሦስቱ አዲስ ፈራሚዎች አማኑኤል ተሾመን ብቻ የመጠቀም ዕድል ሊኖረው ይችላል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለአምስት ጊዜያት ተገናኝተው ጅማ ሁለት ጊዜ አዳማ ደግሞ አንድ ጊዜ ድል የቀናቸው ሲሆን ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።
– በአራቱ ግንኙነቶች ጅማ 9 ሲያስቆጥር ፤ አዳማ 5 ግቦች አስመዝግቧል።
– በዚህ ዓመት የመጀመርያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ አዳማ ከተማ 4-1 አሸንፏል።
ግምታዊ አሰላለፍ
አዳማ ከተማ (4-2-3-1)
ታሪክ ጌትነት
ታፈሰ ሰርካ – አሚኑ ነስሩ – አካሉ አበራ – እዮብ ማቲዮስ
ኤልያስ አህመድ – ኤልያስ ማሞ
በላይ ዓባይነህ – በቃሉ ገነነ – ፍሰሀ ቶማስ
አብዲሳ ጀማል
ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)
ጃኮ ፔንዜ
ወንድምአገኝ ማርቆስ – መላኩ ወልዴ – ውብሸት ዓለማየሁ – ኤልያስ አታሮ
አብርሀም ታምራት – ንጋቱ ገብረሥላሴ – ሱራፌል ዐወል
ተመስገን ደረሰ – ሳዲቅ ሴቾ – ሮባ ወርቁ
© ሶከር ኢትዮጵያ