በዕንባዋ ክለብ እንዳይፈርስ የታደገች ጠንካራ እንስት – ወ/ሮ ሲሳይ በላይ

በኢትዮጵያ እግርኳስ ብዙ ባልተለመደ ሁኔታ በዕንባ በታጀበ ተማፅኖ ክለብ እንዳይፈርስ ስላደረገች እንስት ልናወጋችሁ ወድድን።

በሀገራችን ኢትዮጵያ ካለው ኃላ ቀር አስተሳሰብ መነሻነት ለወንዶች እና ለሴቶች ተብለው የተተዉ የስራ መስኮች በተለምዶ ይስተዋላሉ። እግርኳሳችን ላይም ይህ ገዳቢ አስተሳሰብ ተንሰራፍቶ ይስተዋላል። የዛሬዋ እንግዳችን ይህን አስተሳሰብ ከሰበሩ ጥቂት ሴቶች መካከል የምትመደብ ሲሆን ለክለቧ ያበረከተችው አስተዋጽኦ በቂ እውቅና ባይሰጠውም በክለቧ ጉዞ ውስጥ በጉልህ የሚፃፍን ታሪክ ግን ፅፋ አልፋለች።

በ2009 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተካፋይ የነበረው ጅማ አባ ቡና በመጣበት ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊግ ከተመለሰ ወዲህ እጅግ ፈታኝ የሆኑ ጊዜያትን እያሳለፈ ይገኛል። በወረደበት ዓመት ሌላኛው የከተማዋ ክለብ የሆነው ጅማ አባጅፋር የምዕራቡን ኢትዮጵያ በመወከል በፕሪምየር ሊግ መካፈሉን ተከትሎ ትኩረት እየተነፈገው የመጣው ቡድኑ በተለይ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት ላለመፍረስ ሲታገል ቆይቷል።

ታድያ ከሁለት ሺዎቹ መጀመሪያ አንስቶ በጅማ አባቡና ስፖርት ክለብ ውስጥ በፋይናንስ ክፍል ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ስትሰራ የነበረችው እና በቅርቡም የክለቡ የቀድሞው የቡድን መሪ የነበረው ግለሰብ ከኃላፊነት መነሳቱን ተከትሎ ከዚህ ቀደም በነበራት የሥራ ክፍል ከተጫዋቾች ጋር በነበራት መልካም ግንኙነት መነሻነት ወ/ሮ ሲሳይ ቡድኑን በቡድን መሪነት እንድታገለግል መመደቧ ይታወሳል።

ወደ አዲሱ ኃላፊነት ከመጣች አንስቶ ሴትነቷ ሳይገድባት ክለቧን በሚገባ እያገለገለች ትገኛለች። ነገርግን የክለቧ ወቅታዊ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ አደጋ ውስጥ መግባት በእጅጉ ያሳሰባት ወ/ሮ ሲሳይ ከዕለታት በአንዱ ስለክለቧ ጉዳይ ለመምከር ወደ ኦሮሚያ ስፖርት ኮሚሽን ታቀናለች። በዚህም ቆይታዋ ሁኔታው ከተቋሙ አመራሮች በላይ መሆኑን የተረዱት እኚሁ ወይዘሮ “የእናት ሆድ” እንዲሉ የክለባቸው ነገር ሆነባቸውና ተንበርክከው በዕንባ እየታጠቡ የክልሉን የስፖርት ኮሚሽን ኃላፊዎች ተማፀኑ። ዕንባቸውም መና አልቀረም፤ በአፋጣኝ የስፖርት ኮሚሽኑ ኃላፊዎች ቀናነት ታክሎበት ክለቡ ለጊዜውም ቢሆን ተንፈስ ያለበትን የፋይናንስ ድጋፍ አግኝቶ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ መወዳደሩን ቀጥሏል። ይህን አስገራሚ ክስተት አስመልክቶ ይህች ጠንካራ እንስት ከሶከር ኢትዮጵያ ሁኔታውን በተመለከተ ቆይታ አድርጋለች።

ወደ እግርኳሱ የገባሽበት መንገድ እንዴት ነው?

ወደ እግርኳሱ የገባሁት በ2009 ክለቡ ባወጣው ማስታወቂያ መሠረት ነው። ተወልጄ ያደኩት ጅማ ኳሰሜዳ በሚባል ሠፈር ነው። ከልጅነቴ ጀምሮ እግርኳስን ሳይ ስመለከት ነው ያደኩት። ከዚህም በኃላ ያው ትዳር ልጅ እያለ መጣ። ግን እስካሁን በእግርኳስ ውስጥ አለው።

በክለቡ የመጀመርያ ቅጥርሽ በቡድን መሪነት ወይስ በሌላ ዘርፍ ነው?

የተቀጠርኩት በፋይናስ ክፍል ነው። በዚህም ኃላፊነት አንድ አራት ዓመት ሰርቻለው። በአጋጣሚ ነው ወደ ቡድን መሪነት የመጣሁት እንጂ በቀጥታ የቡድን መሪ ሆኜ አልተቀጠርኩም።

እንዴት ቡድን መሪ ሆንሽ ታድያ ?

ክለቡን በቡድን መሪነት ያገለግል የነበረው ሰው ዘንድሮ ውድድሩ ወደሚካሄድበት ሀዋሳ ከተማ ከመጣ በኃላ በኮቪድ በመያዙ ምክንያት ወደ ጅማ ሲመለስ የክለቡ ኃላፊዎች እኔ ደርቤ እንድሰራ በመደረጌ ነው ዘንድሮ ወደ ቡድን መሪነቱ የገባሁት።

ወደ ቡድን መሪነትሽ ወደ ኃላ እመለሳለው። አባ ቡና ለመፍረስ ከጫፍ ደርሶ ስለተረፈበት ሒደት አጫውቺኝ

እንዴት ሆነ መሰለህ ውድድሩ ሊጀምር ሁለት ሦስት ቀን ሲቀረው ወደ ቢሮ እሄዳለው። ያው ለሰባት ወር ደሞዝ አልተከፈለኝም። ያም ቢሆን ተስፋ ይኖረዋል አዲስ ነገር ይፈጠራል በሚል ስሜት ሁሌም ዝም ብዬ ወደ ቢሮ እየሄድኩ እመላለስ ነበር። ግን መጨረሻ ላይ ታህሳስ 24 ይጀመራል ሲባል ቡድኑ ምንም ምዝገባ አላደረገም። በውድድሩ ላይ ስለመሳተፉም እርግጠኛ መሆን አልቻልንም። የዚህን ሰዓት ታህሳስ 20 ወደ አዲስ አበባ ሄድኩ። ምን አልባት አመራሮቹ ራርተው ቡድኑን ከመፍረስ ያተርፉታል ብዬ የኦሮምያ ስፖርት ኮሚሽን ቢሮ ገባሁ። መጀመርያ አቶ ፍሮምሳን አገኘሁትና አለቀስኩ። ‘ምድነው? አባቡና ምን አጥፍቶ ነው የሚፈርሰው?’ እያልኩ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ። አቶ ፍሮምሳ በሁኔታው ተደናግጠው ‘ ከዞኑ ስፖርት ቢሮ ጋር ተነጋግረን አባቡና በውድድሩ እንደሚቆይ ነው የማውቀው’ ብለው መለሱልኝ። ‘ኧረ ምንም የተጀመረ ነገር የለም’ አልኳቸው። በኃላ የዞኑ ስፖርት ቢሮ ጋር ደውለው አጣሩ ‘በጀት የለም ቡድኑ ፈርሷል’ የሚል ምላሽ ሰጧቸው። ‘በቃ እንዲህ የሚል ነገር ሰምቼማ አልወጣም። አቶ ናስር እና አቶ ፍስሀን ማናገር እፈልጋለው’ ብዬ አለቀስኩ። ‘ለጊዜው አቶ ናስር የሉም። አቶ ፍስሀ ግን አዳማ ለስራ ሄዷል’ ሲለኝ ‘እጠብቃለሁ’ ብዬ ጠብቄ ከሰዓት አቶ ፍስሀ ሲመጣ ቢሮ ገብቼ ‘የአባቡና መፍረስን ሰምቼ መቋቋም አልቻልኩም’ ብዬ አለቀስኩ። ‘ምክንያቱም ሦስት ሚሊየን ህዝብ ይደገፈዋል። 20 ወረዳ ይረዳዋል። አባቡና በህዝቡ የሚወደድ ቡድን ምን አጥፍቶ ነው። እንዴት ይፈርሳል። በምን ምክንያት ነው። እኔ ሰባት ወር ደሞዝ አልተከፈለኝም። የምትከፈለኝ ደሞዝ አነስተኛ ነው። እኔ ተርፎኝ አይደለም ከኔ ክለቡ ይበልጣል። ለምን ይፈርሳል?’ ብዬ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩኝ። በዚህ ሰዓት አቶ ፍስሀ ‘ለምን? እንዴት? አይፈርስም!። አንቺ ተረጋጊ አታልቅሺ።’ ብለው በድንጋጤ ወድያው ተደዋውለው በጀት ተመድቦላቸው ቡድኑን ከመፍረስ ታድገውት ወደ ውድድር እንዲገባ አድርገውታል። አሁንም እየደወሉ ከምልህ በላይ ምንችግር አለ እያሉ እየረዱን ነው። አቶ ፍሮምሳ ሀዋሳ ድረስ መጥቶ ማበረታቻ ገንዘብ እየሰጠ እንዲሁም ከኪሱ ገንዘብ አውጥቶ መጋጫ የለንም ካርቶን ነበር የምንጠቀመው መጋጫ ገዝቶ በመስጠት ድጋፍ አድርጎልናል። በአጠቃላይ የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ድጋፍ አልተለየንም። አሁን ቡድንናችን ከሽንፈት ወደ አቻ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ወደ ማሸነፍ ተቀይረን አስራ አንድ ነጥብ ይዘን የውድድሩን አጋማሽ አጠናቀናል።

በጥረትሽ ቡድኑን ከመፍረስ ታድገሽ አሁን እየተወዳረ ስታይው ምን ይሰማሻል ?

ስሜቱ በቃላት የሚገለፅ አይደለም። በጣም ነው ደስ የሚለኝ። አባቡና እኔ ብቻ ሳልሆን በጅማ ህዝብ በጣም የሚወደድ ክለብ ነው። ይህ ክለብ ቢፈርስ በጣም አዝን ነበር። አሁን በውድድር ላይ ሆኖ ሳየው በጣም እደሰታለው። አባ ቡና ከልጆቼ የማለየው ቡድን ነው።

ሴት ነሽ፤ የቤተሰብ ኃላፊነት አለብሽ፤ ልጆች አሉ፤ ይሁን ሁሉ አልፈሽ ቡድን መሪ ሆኖ መስራት ቀላል ነው?

አላማ ካለህ ቀላል ነው፤ አይከብድም። ዋናው አላማ እና ሙያውን የመውደድ ፍላጎት ነው። እኔ ደግሞ በተፈጥሮዬ ሽንፈት አልወድም። ለዚህም ነው ችግሮችን ተቋቁሜ ፈተናዎችም ቢኖሩ ይህን ሁሉ ተቋቁሜ በመስራት ማሸነፍ ነው ውስጤ የሚቀበለው። የሁልጊዜ ስሜቴ ይህ ነው። ለማንኛውም ነገር መሸነፍ እጅ መስጠት አልፈልግም። ይህ ይመስለኛል ከባዱን ስራ ያቀለልኝ፤ ወደ ስኬትም እንድገባ ያደረገኝ። ከተጫዋቾቼም ጋር በዚህ መልኩ ነው ተግባብቼ በመስራቴ ነገሮች እንዲቀለኝ ያደረገው። ፈጣሪ ይመስገን ሰዎችም ያከብሩኛል። በዚህ በዚህ ፈተና ቢኖርም አሸናፊነትን በመሥራት አሳካለሁ። አልችልም የሚባል ነገር የለም በሚል መርህ እየሰራሁ እገኛለሁ።

በአንድ አጋጣሚ በቤንሻንጉል ክልል አሶሳ አንድ የሴት ቡድን መሪ አጋጥማኛለች። ከዛ በኃላ አንቺን አይቻለሁ። እንዴት ነው ተጫዋቾች ባህሪ ከባድ በመሆኑ ሥራው አልከበደሽም ?

እኔ በባህሪዬ ቁጡ ነኝ። ያም ቢሆን ከ2009 ጀምሮ ከአሰልጣኝ ደረጄ በላይ እና ገብረመድህን ኃይሌ ከመሳሰሉ ትልልቅ አሰልጣኞች ጋር ሰርቼ አልፌያለው። በዚህም ምክንያት ቡድን መምራት ምን እንደሆነ ከእነርሱ ትልቅ ትምህርት ወስጃለው። ከዚህ በፊት የነበረው ቡድን መሪ ፍቅሩም ትልቅ ትምህርት አስተምሮኛል። እኔ ፋይናንሱን ብሰራም ቡድን መሪ ምንድነው የሚሰራው የሚለውን ስለማውቅ ከዛ የወሰድኩት ትምህርት ስላለ ብዙም አልከበደኝም። ያም ቢኖን የተጫዋች ባህሪ አስቸጋሪ ነው። ግን ነገሮችን ለማስተካከል እንደ እናት በመቆጣት እንደ እናት በመምከር በጣም ገፍቶ ሲነጣም በማስጠንቀቂያ እየሰራሁ ነው።

ሴት ቡድን መሪ አልተለመደም። ለዚህ ያለሽ አስተያየት ምንድነው?

አዎ! ብዙም አልተለመደም። ግን እኔ የምለው ቡድን መሪነትን ለሴቶች ቢሰጥ ጥሩ ነው እላለሁ። ከወንዶችም በላይ ይሰሩታል። ምክንያቱም አንደኛ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ይፈልጋሉ። ሁለተኛ ለሥራቸው ታማኝ ታታሪ ናቸው። ስለዚህ ከወንዶች በላይ ይሰራሉ ብዬ አስባለሁ።

ከዚህ በኃላ በቡድን መሪነት የመቀጠል ሀሳብ አለሽ ?

አዎ በጣም አስባለው። ቅድም እንዳልኩህ እግርኳስን ከልጅነቴ ጀምሮ እያየሁት ያደግኩት የምወደው ስፖርት ነው። አሁንም ባለችኝ ቀሪ ዕድሜ እንደ ፈጣሪ ፍቃድ መሥራት ነው የምፈልገው።

የቤተሰብ ህይትሽ ምን ይመሰላል ?

ሁለት የ22 እና የ24 ዓመት የሴት እና የወንድ ልጆች አሉኝ። የልጆቼ አባት በህይወት የለም። ከባለቤቴ ህልፈት በኃላ አላገባሁም። ልጆቼንም እንደ እናት አባት ሆኜ ነው ያሳደኩት። ከእግርኳሱ በፊት አንድ ሦስት የተለያዩ ድርጅቶች ሰርቻለሁ።

በመጨረሻም መናገር የምትፈልጊው ነገር ካለ ?

በሥራዬ ደስተኛ ነኝ። ብዙ ማመስገን የምፈልጋቸው አካላት አሉ። በመጀመርያ የክልሉ ስፖርት አመራሮች አቶ ናስር እና አቶ ፍስሐን እጅግ በጣም አመሰግናለው። አቶ ፍሮምሳን እጅግ አመሰግናለሁ። የጅማ ዞን ስፖርት ቢሮ አቶ ነጉማን እንዲሁም የክለቡ ፕሬዝደንት አቶ ሰብስብ፣ ምክትል ፕሬዝደንት ፀጋዬን በዚህ አጋጣሚ በጣም አመሰግናለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ