የአሠልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 1 – 2 ጅማ አባጅፋር

ከአራት ሰዓቱ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከቡድኖቹ አሠልጣኞች አስተያየት ተቀብሏል።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ጅማ አባ ጅፋር

የዛሬው ጨዋታ ያው ከዜሮ መጀመር ነው። አንደኛው ዙር የራሱ ደካማ እና ጠንካራ ጎን ይኖረዋል። በዛሬው ጨዋታ የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንደመገኘታችን ጠንካራ ፉክክር እንደሚኖረው ጠብቀናል። በተለይም እነሱ በሁለተኛው አጋማሽ ተፈጥሯዊ ክህሎት ያላቸው የመሀል ሜዳ ተጫዋቾች አስገብተው ጠንካራ ፉክክር አድርገዋል። ዞሮ ዞሮ የዛሬ ውጤታችን ትዕግስተኛ በመሆናችን ነው። በትዕግስት መጨዋታችን ነው የጠቀመን። እንጂ እነሱም ቀላል ቡድን አይደሉም። አዳማ አሁን ያለበት ደረጃ የሚገባው አይደለም። አሁንም ቢሆን በከፍተኛ ተነሳሽነት ይህንን ውጤት እያመጡ ያሉ የእኛ ተጨዋቾች ምስጋና ይገባቸዋል። አንድ ተጨዋች ብቻ ነው ያስገባነው እንጂ የነበረው ቡድን ነው። በከፍተኛ ቁርጠኝነት እና ፍላጎት ጅማ አባ ጅፋርን የሆነ ቦታ ማድረስ አለብን በማለት እየሰሩ ያሉትን ተጨዋቾች ማድነቅ እፈልጋለሁ።

ቡድኑ ይተርፋል ብለው ስለማሰባቸው

ይሄማ የግድ ነው! ከፊታችን እኮ 11 ጨዋታዎች ይቀራሉ። በሂሳብ ስሌት ካየነው 33 ነጥቦች ማለት ነው። በፕሪምየር ሊጉ ለመቆየት ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን። ቻምፒዮን የሚሆነውንም የሚወርደውንም ቡድን ለመለየት የ 24ቱም ጨዋታ ውጤት ወሳኝ ነው። እያንዳንዱን ጨዋታ የጥሎ ማለፍ ባህሪ የተላበሰ አጨዋወት እየተጫወትን ውጤታማ ለመሆን እንሞክራለን።

ስለ ሳዲቅ ሴቾ ወደ አስቆጣሪነት መመለስ

ሳዲቅ ሴቾ በፕሪምየር ሊጉ ጥሩ ክህሎት ካላቸው አንዱ እና ሳጥን ውስጥ ብዙ ነገር መስራት የሚችል ተጨዋች ነው። አሁን ላይ ወደ ትክክለኛ አቋሙ እና በራስ መተማመኑ እየተመለሰ ያለ ይመስለኛል።

አሰልጣኝ ዘርዓይ መሉ – አዳማ ከተማ

ስለጨዋታው

ከቡድኑ ጋር ያው አንድ ቀን ነው ልምምድ የሰራነው። ጥሩ ነገር ነበር ፤ የተሻልን ነበርን። ኳስ ይዘው ተጫውተዋል ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል። ግን ያው በተነጋገርነው በቆሙ እና በተሻማ ኳስ ግቦች ገብተዋል። ጥሩ መሻሻሎች ነበሩ። ጎል ጋር ቶሎ ደርሰናል። ያጠቃቀም ችግር እንጂ ማግባት እንችል ነበር። በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ማስቆጠር እንችል ነበር። ያው በሽንፈት የቆየ ቡድን ከመሆኑም አንፃር ይፈጠራል። ባለቀ ሰዓት በቆመ ኳስ ነው የገባብን። መሀል ተከላካያችን ተጎድቶ ዳኛው ማስቆም ነበረበት። ጨዋታው ስለቀጠለ ያ ኳስ ሄዶ ፋዎል ተሰራ እና የቆመ ኳስ ነው የገባው። ግን ኳሱ ጥሩ ነበር ፤ ጥሩ መሻሻል ነበር ቡድኑ ላይ። የተሻለ ነገር ይኖረናል ብዬ አስባለው በቀጣይ ጨዋታዎች።

ስለአዲስ ፈራሚዎች አቋም

አዎ ጥሩ ነው። ምንም ልምምድ ሳይሰሩ ነው በጉዳት እና በቅጣት የወጡ ስለነበሩ በድፍረት ያጫወትናቸው። የተሻለ ነገር ነበር ሲያደርጉ የነበሩት። አንድ ላይ ተዋህደው ልምምድ ሲሰሩ ወደ አሸናፊነት እንመለሳለን ብዬ ነው የማስበው።

ቡድኑ ይተርፋል ብለው ስለማሰባቸው

አዎ ብዙ ክፍተቶች አሉት ቡድኑ። ከክለቡ ኃላፊዎች ጋርም አውርቻለው። በአፋጣኝ ተጫዋቾች መምጣት አለባቸው። ያንን ነገር ማስተካከል የሚቻል ከሆነ አሁንም ልዩነቱ ሰፊ አይደለም። የአራት አምስት ነጥብ ልዩነት ነው። በተለይ መሀል ላይ ተሰብስበው ነው ያሉት ቡድኖች። አንድ ሁለት ጨዋታ ማሸነፍ የሚቻል ከሆነ ተመልሰህ እዛው ጋር ነው የምትደርሰው። ሀሉም ጨዋታዎች እንደፍፃሜ የሚታዩ በመሆኑ እነዚህ ነገሮች ከተስተካከሉ አዳማ በሊጉ ይቆያል ብዬ ነው የማስበው።


© ሶከር ኢትዮጵያ