ሁለት ጎሎች ከተስተናገዱበት ከከሰዓቱ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሠልጣኞች የድህረ-ጨዋታ አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።
ዘላለም ሽፈራው – ወላይታ ድቻ
ስለ ጨዋታው?
በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረን እንቅስቃሴ ትንሽ ደከም ያለ ነበር። የምንፈልገውን አላደረግንም። ከእረፍት በኋላ ግን የምንፈልገውን ነገር ሜዳ ላይ ተግብረናል። ቁጥሮችም የሚናገሩት ይህንኑ ነው። ግብ ማስቆጠራችን ብቻ ሳይሆን የሜዳው ሦስተኛው ክፍል ላይ የምንደርስበት መንገድ ጥሩ ነበር። ከሌላው ጊዜ በተሻለም ኳስን ተቆጠቀጥረን የመጫወት አቅማችን ጥሩ ነበር።
እንደየጨዋታው ስለሚቀርብበት የአጨዋወት መንገድ?
ተጋጣሚ ቡድኖችን አጠናለሁ። የቶርናመንት ውድድር አንዱ ጠቀሜታውም ይሄው ነው። ሁለተኛ ደግሞ ጨዋታው ስለሚተላለፍ በድጋሜ የመመልከት ዕድሉ አለ። ይህ እንደ ቡድን ብቻ አደለም። በተናጥልም ተጋጣሚ ቡድኖች ውስጥ ያሉትን ተጫዋቾች እናጠናለን።
ዛሬ ሜዳ ላይ ስለተሰለፏቸው አዳዲስ ተጫዋቾች?
በእርግጥ አዲስ የመጡት ተጫዋቾች በቶሎ ከቡድኑ ጋር ይዋሃዳሉ ብሎ ማሰብ ትንሽ ይከብዳል። አስናቀ በጨዋታው ተጎድቶ ወቷል። ግን ተጎድቶ እስኪወጣ የነበረው እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር። ነፃነት ኳሶችን የማሸነፍ አቅሙ መልካም ነው። ነገርግን ኳሶችን የማደራጀት ነገር ላይ ይቀረዋል። ግን በአማካይ ክፍሉ ላይ ጋቶች ሲመጣ ደግሞ ጥሩ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።
ቡድኑ በደረጃ ሠንጠረዡ ስለሚጨርስበት ቦታ?
በደረጃ ሠንጠረዡ ከአንድ እስከ አምስት ያሉ ቡድኖች ጋር እንዳረሳለን። ዋናው አላማችንም አደገኛ ከነበረው ቀጠና መውጣት እና ወገብ ላይ ካሉ ቡድኖች ጋር መዳረስ ነበር። አሁን ላይ በደንብ እየተንደረደርን ነው። ውድድሩም ገና ስለሆነ ይሄንን ነገር ማስቀጠል ደግሞ ወሳኝ ነው።
አሸናፊ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና
ስለ ጨዋታው?
ባሰብኩት እና ባቀድኩት መንገድ ጨዋታው አልሄደም። በጨዋታው ክፍተቶች ነበሩብን። የአቋቋም ስህተቶችም ነበሩብን። በአንድ ጨዋታ ብዙ ግብ ሲቆጠርብንም የመጀመሪያችን ነው። ይህንን ደግሞ እናርማለን።
ቡድኑ የሰላ የግብ ሙከራ ማድረግ ስላለመቻሉ?
ከመሐል ሜዳ የሚላኩት ኳሶች ጊዜያቸውን የጠበቁ አለመሆናቸው፣ አጥቂ ቦታ ላይ የተሰለፉት ተጫዋቾች ኳስ ለመቀበል የነበራቸው ዝግጁነት ማነስ እንዲሁም ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ስንሄድ በቁጥር አንሰን መሆኑ ክፍተታችን ነበር። ወደፊትም ይሄንን ለማስተካከል እንሞክራለን።
ቡድኑ እየተመራ ስላደረገው የተጫዋች ለውጥ?
ካሉሻ የተፈለገውን ያህል ሊረዳን አልቻለም። ዛሬ የመጨረሻ ኳሶችን ከእርሱ ነበር ስንጠብቅ የነበረው። ነገርግን ጥሩ አልነበረም። በዚህም ምክንያት ልንቀይረው ተገደናል።
ስለ ዋንጫ ፉክክሩ?
የዋንጫው ዕድል አሁንም አለን። ልዩነቱ የጎላ አደለም። ግን ከዚህ በኋላ የምናደርጋቸውን ጨዋታዎች በሙሉ በጥንቃቄ ማከናወን እንዳለብን ይሰማኛል።
© ሶከር ኢትዮጵያ