አዝናኝ ፉክክር ባስመለከተን የረፋዱ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ወልቂጤ ከተማን 2-1 ማሸነፍ ችሏል።
ወልቂጤ ከተማ በቅዱስ ጊዮርጊስ ከደረሰበት ሽንፈት በግብ ጠባቂው ጆርጅ ደስታ፣ ተስፋዬ ነጋሽ እና አቡበከር ሳኒ ምትክ ዮሐንስ በዛብህ ፣ ሀብታሙ ሸዋለም እና በኃይሉ ተሻገርን በመቀየር ጨዋታውን ጀምሯል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል በተደረጉ ለውጦች ደግሞ አሥራት ቱንጆ በኢያሱ ታምሩ እንዲሁም ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን በአማኑኤል ዮሐንስ ተተክተዋል።
የዛሬው ማለዳ ጨዋታ የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ባዘዘው ጫኔ በተገኙበት በማርሽ ባንድ አሸብርቆ 125ኛውን የዐድዋ ድል በዓል በማሰብ በኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር የጀመረ ነበር።
ጨዋታው በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ግብ አስተናግዷል። 4ኛው ደቂቃ ላይ ልማደኛው አቡበከር ናስር ሳጥን ውስጥ ከሚኪያስ መኮንን የተቀበለውን ኳስ ከተካላካዮች ጋር ታግሎ በማስቆጠር በጊዜ ቡናን መሪ ማድረግ ችሏል።
ዛሬም የኋላ ክፍላቸው በቀላሉ ግብ ያስተናገደው ወልቂጤ ከተማዎች ቀሪውን የአጋማሹን ደቂቃዎች በጨዋታ በልጠው ታይተዋል። የተሻለ የኳስ ቁጥጥርን በመያዝ በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ መቆየት ይቻሉት ወልቂጤዎች ቅብብሎቻቸው እስከ ቡና ሳጥን ድረስ ዘልቀው መግባት የቻሉም ነበሩ።
ከእንቅስቃሴ ባለፈ ወልቂጤ ከተማ የተሻሉ የግብ ዕድሎችን መፍጠሩም አልቀረም። 17ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ታደሰ ሳጥን ውስጥ ጥሩ የግብ አጋጣሚ ቢያገኝም አቤል ማሞ ቀድሞ ደርሶ አውጥቶበታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ረመዳን የሱፍ በግራ መስመር በፈጣን ጥቃት ገብቶ ያመቻቸውን ኳስ ጥሩ የነበረው አብዱልከሪም ወርቁ ወደ ግብ ሞክሮ በድጋሚ አቤል አድኖበታል። አብዱልከሪም 24ኛው ደቂቃ ቶማስ ስምረቱ ደግሞ 39ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ግብ ያደረጓቸው ሙከራዎችም ኢላማቸውን ባይጠብቁም ጠንካራ ነበሩ።
ከወትሮው በተለየ የጨዋታ ብልጫ የተወሰደባቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች የኳስ ምስረታቸው የሜዳውን አካፋይ እንዳለፈ በተደጋጋሚ ይቋረጥ ነበር። 43ኛው ደቂቃ ላይ ብቻ እጅግ ወደ መሀል ሜዳው የተጠጋው የተጋጣሚያቸው የተከላካይ መስመር ጀርባ መግባት ቢችሉም እንቅስቃሴውን ያስጀመረው አቡበከር ናስር ከግራ ወደ መሀል ለታፈሰ ሰለሞን ያሳለፈውን ኳስ አማካዩ አክርሮ ሞክሮ ዮሐንስ በዛብህ አድኖበታል።
ከዕረፍት መልስ ኢትዮጵያ ቡናዎች በእርጋታ ኳስ ወደ መቆጣጠሩ ተመልሰዋል። ክፍተቶችን ለማግኘት ትኩረታቸውን በሰበስቡበት ሰዓትም የጨዋታውን ጫና ይበልጥ የሚያቀልላቸውን ጎል አግኝተዋል። 58ኛው ደቂቃ ላይ የቡድኑ የልብ ትርታ አቡበከር ናስር ከዳግም ንጉሴ የነጠቀውን ኳስ ሁለተኛ ግብ አድርጎታል። ከተከላካይ ጀርባ ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት በአቤል ማሞ ንቃት አልሰምር ያላቸው ወልቂጤዎች ልብ የሚሰብረውን ጎል ካስተናገዱ በኋላ ተቀይሮ በገባው ፈጣኑ አህመድ ሁሴን ለማስቆጠር ቢቃረቡም የአህመድ ጥረት አቤልን አልፎ ለጥቂት ወደ ላይ ወጥቶበታል።
ከዳግም ንጉሤ ስህተት መነሻነት ቡናዎች ሦስተኛ ግብ ለማግኘት ተቃርበው የነበረ ሲሆን ኃይሌ ገብረትንሳይ እና ምንተስኖት ከበደን በጉዳት ለመቀየር መገደዳቸው ጨዋታው እንዳይቀላቸው ሲያደርግ በሁለቱ ጉዳቶች መሀልም ግብ ተቆጥሮባቸዋል። 59ኛው ደቂቃ ላይ የቡድኑ ኮከብ አብዱልከሪም ወርቁ ያመቻቸውን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው አቡበከር ሳኒ ወደ ሳጥን በመግባት ወልቂጤ ልዩነቱን እንዲያጠብ አድርጓል። 77ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ከገባው ዊሊያም ሰለሞን በተነሳ ኳሱ ቡናዎች በአቡበከር ዳግም መሪነታቸውን ለማስፋት ቢቃረቡም ሙከራው ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል።
ድንቅ ፉክክር እያስመለከተን በቀጠለው ጨዋታ ቡናዎች ይበልጥ ኳስ ይዘው ጫናቸውን በመጨመር ወደ ግብ ተጠግተው ሲቆዩ ወልቂጤዎች ደግሞ የአህመድ ሁሴንን ፍጥነት ለመጠቀም የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ጥረዋል። በጭማሪ ደቂቃ በአቡበከር ተመቻችቶ በዊልያም ለጥቂት ከተሳተው ኳስ በኋላም ሌላ አጋጣሚ ሳይፈጠር ጨዋታው በቡና 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ