ነገ ረፋድ ላይ እንደሚደረግ የሚጠበቀውን ጨዋታ በዳሰሳችን ተመልክተነዋል።
በእንቅስቃሴ ጥሩ ፉክክር እንደሚያስመለክተን በሚጠበቀው ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ በሰንጠረዡ አጋማሽ ካለው የነጥብ መቀራረብ ከፍ ለማለት ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ካሉት እና ሽንፈት ከገጠማቸው ተካታዮቹ ርቆ ከፋሲል ጋር ያለውንም ልዩነት መልሶ ከማጥበብ አንፃር ጨዋታው እስፈላጊያቸው ይሆናል።
ቀድሞ መምራት በቻለበት የቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ አራት ግቦችን ለማስተናገድ የተገደደው ወልቂጤ ከተማ የመከላከል ግርማ ሞገሱን መልሶ ማግኘት ይኖርበታል። ከቡድኑ የኋላ መስመር ጥንካሬ በማይጠበቅ ሁኔታ እስከ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ድረስ የተቆጠሩበትን ስምንት ጎሎች ግማሽ ያህል ጊዜ መረቡን ማስደፈሩ ከነገ ተጋጣሚው ክፍተቶችን የማነፍነፍ ባህሪ አንፃር ሊያስተካክለው የሚገባው ትልቁ ድክመቱ ሆኗል። በግብ ጠባቂ ቦታ ላይ ጀማል ጣሰውን ማጣቱ የፈጠረው ክፍተት በአግባቡ የሚሸፈንበት መላም መገኘት ይኖርበታል። መሰል ክስተቶች በተከላካዮች ላይ የሚፈጥሩት የሥነ ልቦና ጥንካሬ መንሸራተትም የቡና አጥቂዎች በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ከማቆም አንፃር ቡድኑን ሊፈትኑት ይችላሉ።
በመጀመሪያው ዙር ቡናን ከኋላ በመነሳት ነጥብ የተጋራው ወልቂጤ አሁንም ይህ አልሸነፍ ባይነቱ አብሮት እንዳለ ለድል ባይበቃም ልዩነቱን ማጥበብ በቻለበት በጊዮርጊስ ጨዋታ ማሳየቱ ደግሞ በበጎ መልኩ ወደ ነገው ጨዋታ ይዞት ሊመጣ የሚገባው ነጥብ ነው። ከአጨዋወት አንፃር ቡድኑ አማካይ ክፍል ላይ ካለው ታታሪነት በመነሳት ከኳስ ውጪ የኢትዮጵያ ቡናን ቅብብሎች ወደ ፊት ገፍተው እንዳይሄዱ በማድረጉ ላይ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያደርግ ይጠበቃል። ከሚቋረጡ ኳሶችም በሁለቱ ኮሪደሮች የሚነሱ ጥቃቶች ለሰራተኞቹ የግብ ማግኛ መንገዶች እንደሚሆኑ የሚገመት ነው። እዚህ ላይ ግን ተጋጣሚው መሀል ሜዳውን ካለፈ በኋላ የሜዳውን ስፋት ተጠቅሞ የሚያጠቃበትን አኳኋን ለመግታት በጊዮርጊሱ ጨዋታ ካሳየው መዘነጋት በእጅጉ ተሽሎ መቅረብ የግድ ይለዋል።
ኢትዮጵያ ቡና አዳማ ከተማን በሰፊ የግብ ልዩነት ከረታ በኋላ ለነገው ጨዋታ ይደርሳል። ደካማ የተጋጣሚ የመከላከል አደረጃጀት ሲኖር ወይንም በጥሩ ሁኔታ የጀመረ ተጋጣሚው በመሀል ክፍተቶችን ከፈጠረ ቡድኑ በተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን መፍጠር እንዲሁም ለውጤት ማብቃት እንደሚችል ከሲዳማው ጨዋታ ባለፈ አዳማ ላይም ደግሞ አሳይቶናል። ከዚህ አንፃር ወልቂጤን ከአንድ ጨዋታ በፊት ጥያቄ ላናነሳበት እንችል የነበረ ቢሆንም የመጨረሻው ጨዋታ ላይ ያሳየው ያልተጠበቀ ባህሪ ግን ቡና በሲዳማ እና አዳማ ላይ ያገኘው ዓይነት ደካማ ጎን ዳግም ሊገጥመው እንደሚችል እንድንገምት ያደርገናል።
ያ የማይሆን ከሆነ እና ወልቂጤ እንደቀደመ ጥንካሬው ሁሉ እንደ ሀዋሳ እና ሀዲያ ሆሳዕና ዓይነት ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ይዞ ከቀረበ ደግሞ የአሰልጣኝ ካሳዬ ቡድን አልፎ አልፎ የሚታይበት ደካማ ጎኑ እንዳይመለስበት ያሳስባል። የመጀመሪያው በሙሉ ማጥቃት ውስጥ ሆኖ ከኋላ በሚተወው ክፍተት ለጥቃት መጋለጥ ወይም በታታሪዎቹ የወልቂጤ ተጨዋቾች በራሱ ሜዳ ለቅብብል ስህተቶች መዳረግ ሊሆን ይችላል። ይህን ጉዳይ ቡና በቅርብ ጨዋታዎቹ በእጅጉ ቀንሶ ቢታይም ከሚመርጠው አጨዋወት አንፃር ግን በድጋሚ አይከሰቱም ማለት አይቻልም። ከዚህ በተጨማሪ በሰፉ የደቂቃ ልዩነቶች ብቻ የግብ ዕድሎችን ሲፈጥር በግብ ፊት የሚታይበት የአጨራረስ ችግሩ ነው። በዚህም ቡድኑ ደጋግሞ የተጋጣሚውን በር ማንኳኳት ሲቸግረው የሚገኙ ጥቂት ዕድሎችን ወዲያውኑ ወደ ውጤት መቀየር ከአቡበከር ናስር ውጪ ካሉት አጥቂዎቹም አጥብቆ የሚጠብቀው ጥንካሬ ይሆናል።
ወልቂጤ ከተማ አሳሪ አልመሀዲ ፣ ፍሬው ሰለሞ እና አዳነ በላይነህን በጉዳት ጀማል ጣሰውን ደግሞ በቅጣት ሲያጣ የሀብታሙ ሸዋለም መመለስ ትልቁ ዜና ሆኖለታል። ኢትዮጵያ ቡና ምንም የሚያጣው ተጨዋች የሌለ ሲሆን ሀብታሙ ታደሰም ልምምድ ጀምሯል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ቡድኖቹ በዚህ የውድድር ዓመት ያደረጉት የመጀመሪያ የሊግ ግንኙነት በ 2-2 ውጤት የተጠናቀቀ ነበር።
ግምታዊ አሰላለፍ
ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)
ዮሐንስ በዛብህ
ተስፋዬ ነጋሽ – ቶማስ ስምረቱ – ዳግም ንጉሴ – ረመዳን የሱፍ
ያሬድ ታደሰ – ሀብብታሙ ሸዋለም – አብዱልከሪም ወርቁ
አቡበከር ሳኒ – ሄኖክ አየለ – አሜ መሀመድ
ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)
አቤል ማሞ
ኃይሌ ገብረትንሳይ – ወንድሜነህ ደረጄ – አበበ ጥላሁን – አስራት ቱንጆ
ታፈሰ ሰለሞን – ረመዳን ናስር – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን
ሚኪያስ መኮንን – አቡበከር ናስር – አቤል ከበደ
© ሶከር ኢትዮጵያ