የአሠልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 1-2 ኢትዮጵያ ቡና

ከአራት ሰዓቱ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሠልጣኞች አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

በጨዋታው ተፈትነዋል ማለት ስለመቻሉ

ይቻላል! ሂደቶቹን ቶሎ ቶሎ ያቋርጡብን ነበር። አንድ የጠበበ ቦታ ውስጥ ሊያስገቡን ይፈልጉ ነበር። ትንሽ የእኛ ልጆች ያልተረዱት ነገር ነበር። የት ቦታ የተከፈተ መጫወቻ ቦታ እንዳለ ፣ በተለይ ማየት የሚገባቸው ሰዎችን ፣ ቦታቸውን ለቀው የሚወጡ ሰዎችን አንቆጣጠርም ነበር። የሚፈልጉት ኢላማ ውስጥ ያስገቡን ነበር። ስለዚህ ሂደቱ ቶሎ ቶሎ ይቋረጥ ነበር። ኳስ ከያዙ በኋላ ደግሞ ያቆዩት ነበር ፤ መንጠቁ ላይ ብቻ ሳይሆን ትኩረታቸው መጫወቱ ላይም ስለነበር። በእንቅስቃሴ የተሻሉ ነበሩ ማለት እችላለሁ።

ከጨዋታ ይልቅ ለውጤት ቅድሚያ ስለመስጠታቸው

እኛ ሁሌም በመጫወት ውስጥ ነው ውጤት የሚመጣው ብለን ነው የምናስበው። የግዴታ ጨዋታውን መቆጣጠር አለብህ ውጤት ለማምጣት። ምንአልባት በዛሬው ዓይነት ሁኔታ ውጤት ልታመጣ ትችላለህ። ግን ጨዋታውን ባልተቆጣጠርክበት ሁኔታ ቀጣይነት አይኖረውም። የነጥቡ መጥበብ እና መስፋት የሚያመጣው ለውጥ የለም ለእኛ። ሁሌም ትኩረታችን ጨዋታውን ተቆጣጥረን ውጤት የምናመጣበት መንገድ ላይ ነው።

አቡበከር ወደ ዮርዳኖስ ዓባይ ደረጃ መድረስ ስለመቻሉ

አዎ ትልቅ አቅም ያለው ተጨዋች ነው። ምንአልባት አቡበከር የተጫወተበት ጊዜ ትንሽ ነው። ዮርዳኖስ ብዙ ዓመት ከተጫወተ በኋላ ነው ስለእሱ ይህን እያልን ያለነው። አቡበከር ብዙ እየተጫወተ ሲመጣ ከልምዱ ብዙ የሚያካብታቸው ነገሮች ስለሚኖሩ እዛ ደረጃ ላይ ይደርሳል ብዬ አስባለሁ።

ደግአረገ ይግዛው – ወልቂጤ ከተማ

ስለጨዋታው

መጀመሪያ ስንገባ የላይኛው የሜዳ ክፍል ላይ ተጭነን ለመጫወት ነበር። ያንን ተግባራዊ ለማድረግ ልጆቻችን ጥረት አድርገዋል። ሆኖም ግን በጊዜ ያስተናገድነው ጎል ጨዋታው ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል። ሆኖም ግን ልጆቻችን ቶሎ ወደራሳቸው እንቅስቃሴ ተመልሰው ጨዋታውን ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል ሁኔታ ተቆጣጥረው እየተጫወቱ ነበር። ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችንም መፍጠር ችለናል። ግን ደግሞ ያገኘናቸውን ዕድሎች መጠቀም አልቻልንም። ምንአልባት የጨዋታው ውጤትም ይቀየር ነበር ብዬ አስባለሁ። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የተወሰኑ ማስተካከያዎችን ለማድረግ ሞክረናል። ሜዳ ላይ የሚፈጠሩ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ቡድናችንን ዋጋ አስከፍሎታል።

አቡበከርን መቆጣጠር ተስኗቸው እንደሆነ

እሱን መቆጣጠር አቅቶናል ብዬ አላስብም። ጎሎቹ የተገኙበት መንገድ የእኛ የመከላከል አደረጃጀት ደካማ በመሆኑ ነው። ሁለቱም ጎሎች ከእኛ ስህተቶች የመጡ ናቸው። እንደ ቡድን ማስተካከል የሚገባን ስህተት ነው በቀጣይ ያንን አስተካክለን እነመጣለን። እንደተጨዋች ግን ለአቡበከር ትልቅ አክብሮት አለኝ። ጠንካራ ልጅ ነው። ሀገራችን ውስጥ አሁን ከሚታዩ አጥቂዎች በግንባር ቀደምነት የምትጠቅሰው ነው እና ለቡና ትልቁን ሥራ ሰርቷል ብዬ አስባለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ