በዝውውር መስኮቱ ድቻን ተቀላቅሎ ዛሬ በመጀመርያ ጨዋታው ጉዳት የገጠመው አስናቀ ሞገስ ስለ ጉዳቱ ሁኔታ ይናገራል።
በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የሚመራው ወላይታ ድቻ ሀዲያ ሆሳዕናን ዛሬ ማሸነፉን ተከትሎ ደረጃውን በአስገራሚ ሁኔታ ማሻሻሉን በመቀጠል ከወራጅ ቀጠና ርቆ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። አሰልጣኙ ቡድኑን በሁለተኛው ዙር ለማጠናከር ካስፈረሟቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው አስናቀ ሞገስ ይገኝበታል። የግራ መስመር ተከላካዩ የመጀመርያውን ጨዋታ ለማድረግ ወደ ሜዳ ቢገባም ለሰባት ደቂቃ ብቻ ቆይቶ እጁ ላይ ባጋጠመው ከፍተኛ ጉዳት ተቀይሮ ሊወጣ ችሏል። በጉዳቱ ዙርያ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ስለሁኔታ አዋርተነው ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶናል።
” ያጋጠመኝ ጉዳት ትከሻዬ አካባቢ የጅማት መበጠስ እንዲሁም የእጅ ውልቃት ነው። አስፈላጊውን የራጅ ምርመራ አድርጌያለሁ። ወደ አዲስ አበባ በመሄድ የተሻለ ህክምና እንዳገኝ ሪፈር ተፅፎልኛል። እዚህ ያሉት ሀኪሞች ቀዶ ጥገና እንዳደርግ እንዳለብኝ ቢነግሩኝም እንዳጋጣሚ ፊዚዮትራፒስት ይስሐቅ ሽፈራው ባህር ዳር በመሆኑ እርሱ ውልቃቴንም ወደ ቦታው መልሶት ‘ቀዶ ጥገና አያስፈልገውም፤ ትሪት በማድረግ ይስተካከላል’ ብሎኛል። ለማንኛውም ነገ አዲስ አበባ በመሄድ ከታየሁት በኋላ የሚሉኝን የምሰማ ይሆናል። አንዳንዴ በእግርኳስ ድንገተኛ ነገር ይፈጠራል። ሁሉም ነገር ፈጣሪ እንደፈቀደ ነው የሚሆነው። በፍጥነት ከጉዳቴ አገግሜ ወላይታ ድቻን አገለግላለሁ።”
© ሶከር ኢትዮጵያ