ቅድመ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ፋሲል ከነማ

እጅግ ወሳኝ የሆነውን ጨዋታ በዳሰሳችን እንዲህ ተመልክተነዋል።

ነገ ረፋድ ላይ የሚደረገው ይህ ጨዋታ በዋንጫ ፉክክሩ ላይ የሚፈጥረው ልዩነት የተጋጣሚ ቡድኖችን ብቻ ሳይሆን የሊጉን ተከታታዮች ሁሉ ትኩረት የሳበ ሆኗል። ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን ያሸነፈው ኢትዮጵያ ቡና ከዘጠናኛው ሳምንት የወላይታ ድቻ ሽንፈት በኋላ ሳይረታ ከነገ ተጋጣሚው ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት እንዳይሰፋ በማድረግ ለጨዋታው ደርሷል። ድል ቀንቶት ያሁኑን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ ማድረግ ከቻለም ኮስታራ ተፎካካሩነቱን አረጋግጦ ቀጣይ ጨዋታዎቹን ይከውናል።

በነገ ተጋጣሚው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ በኋላ ለሽንፈት እጅ ያልሰጠው ፋሲል ከነማም ልዩነቱን ስምንት አድርሶ በፉክክሩ ላይ ትንፋሽ ለመውሰድ ቡናን ማሸነፍ ብቸኛ አማራጩ ነው። የስድስት ተከታታይ ድል ጉዟቸው በሰበታ ነጥብ ሲጥሉ የተቋረጠባቸው ፋሲሎች በ11 ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ጉዞ ሪከርዳቸውን ግን አሁንም በእጃቸው አድርገው ነው ነገ ለፍልሚያው የሚቀርቡት።

ኢትዮጵያ ቡና የዋንጫ ተፎካካሪ ቡድኖች ባህሪን ባንፀባረቀበት የመጨረሻው ጨዋታ በወልቂጤ ከተማ ብልጫ ተወስዶበትም ቢሆን ማሸነፍ ችሏል። ነገር ግን በጨዋታው ዋነኛ ጠንካራ ጎኑ የሆነው አማካይ መስመሩ ላይ ብልጫ ተወስዶበት ማለፉ ከድሉ ባሻገር ከእንደነገ ዓይነቱ ከባድ ጨዋታ በፊት ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው። አማኑኤል ዮሃንስ እና ሬድዋን ናስርን በአንድነት ማሰለፉ በፈጠራው ረገድ አብዛኛው ኃላፉነት ታፈሰ ሰለሞን ላይ መጣሉ ብቻ ሳይሆን መዳረሻቸውን ወደ መስመር አጥቂዎቹ ያደርጉ የነበሩት ኳሶች ከወትሮው በተለየ ደካማ የመስመር ተከላካዮች ተሳትፎ በነበረበት ጨዋታ ላይ በተደጋጋሚ በተጋጣሚው ኮሪደሮች ላይ የማጥቃት ሂደቱ እንዲቋረጥ ምክንያት ሆነው ታይቷል። ይህም በተለይም የቡድኑ የግራ ወገን የማጥቃት ስልነት አውርዶት ታይቷል። በማጥቃቱ ረገድ በርካታ የግብ ዕድሎችን በሚፈጥረው ቡድን ውስጥ መሰል ክፍተት መታየቱም የነገው ጨዋታ በሊጉ ዝቅተኛ ግብ በማስተናገድ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ካለ ቡድን ጋር እንደመሆኑ የቡድኑን ትኩረት የሚስብ ይሆናል።

እንደ ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና ባይሆንም በአመዛኙ ለኳስ ቁጥጥር ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው ፋሲል ከነማም በቅዱስ ጊዮርጉሱ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን ሰበታንም ሲገጥም የማጥቃት ዕቅዱ የግብ ዕድሎችን በሚፈልገው መጠን መፍጠር ባለመቻሉ ተፈትኖ አሳልፏል። ከሙጂብ ቃሲም ጀርባ ከሚጠቀማቸው አማካዮች ውስጥ በግራ እና በቀኝ የሚገኙ ተሰላፊዎቹ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ የሚያደላ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ በመሆናቸው እና ከጎን የሚተዉትን ክፍተት ቡድኑ በአግባቡ መጠቀም ላይ ተዳክሞ መታየቱ ለችግሩ አንዱ ምክንያት ነው ማለት ይቻላል። በሌላ ወገን መሀል ሜዳ ላይ ከኳስ ጋር የተሻለ ምቾት የሚሰማቸው ተጨዋቾችን የሚጠቀመው ፋሲል ነገ በዚህ የተጨዋቾች ምርጫው የተጋጣሚውን ቅብብሎች የማቋረጥ ብቃቱ ኳስ ከመያዝ ባሻገር በፈጣን ሽግግር ጎል ላይ የሚደርስበትን አማራጩን ስኬት የሚወስን ይሆናል። ከዚህ ጎን ለጎን ቀጥታ ወደ ሳጥን የሚላኩት የሱራፌል ዳኛቸው መካከለኛ እና ረዥም ኳሶችም ሌላው የቡድኑ የማጥቃት አማራጮች ሊሆኑ ይችላሉ።

የነገው ጨዋታ በቡድኖች ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ደረጃም መሪዎቹን እርስ በእርስ የሚያገናኝ ነው። ዘንድሮ ቡድኑ ካደረጋቸው ጨዋታዎች ውስጥ በሦስቱ ብቻ ግብ ያልቀናው አበበከር ናስር የቡና ብቻ ሳይሆን የሊጉ አስደናቂ ተጨዋች እንደሆነ ቀጥሏል። የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ፉክክሩ መሪ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ብቻ አምስት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። በተለይም በወልቂጤው ጨዋታ በድኑ በቂ ዕድሎችን ባይፈጥርም በግል ልዩነት መፍጠር እንደሚችል ባሳየበት ሁኔታ ለተከላካዮች ፈታኝ ሆኖ መታየቱ ነገ ከፍ ያለ የመከላካል ሪከርድ ካለው ቡድን ተከላካዮች ጋር የሚኖረውን ፍልሚያ ተጠባቂ ያደርገዋል። ከአጥቂዎች ውጪ ሌሎች ተሰላፊዎች ግብ ማግባቱ ላይ በሚያደርጉት ትተሳትፎ ከተጋጣሚው ፋሲል ጋር ሲነፃፀር ደከም ያለው ቡና ነገም ዳግም የአስር ቁጥሩን ልዩ ብቃት የሚጠብቅ ይሆናል።

የፋሲሉ የግብ አዳኝ ሙጂብ ቃሲም ደግሞ ከዚህ በተለየ ወቅታዊ አቋም ላይ ይገኛል። ለሰባት ተከታታይ ጨዋታዎች የዘለቀው የግብ ማስቆጠር ሂደቱ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ተቋርጦ ቆይቷል። በጊዮርጊሱ ጨዋታ ላይ በፍቃዱ ዓለሙ መቀየሩ እና ፍቃዱም ለውጤቱ መገኘት ምክንያት መሆኑ ነገ የሙጂብን የሜዳ ላይ ደቂቃዎች ይበልጥ ዝቅ ሊያደርጋቸውም ይችላል። ይሁን እንጂ መሰል ተጨዋቾች በትልልቅ ጨዋታዎች ላይ መልሰው ራሳቸውን አግኝተው ወደ ጥንካሬያቸው መመለስ የሚችሉ መሆኑ ሙጂብ በነገው ጨዋታ አንዳች ነገር ሊያደርግ እንደሚችል እንድንጠብቅ ምክንያት ይሆናል። በተለይም ተጨዋቹ ፍጥነቱን እና ተክለ ሰውነቱን በመጠቀም በግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ጥረት ሲድኑ የሚታዩ ከተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ ኳሶችን የመጠቀም ዕድሉ የጎላ ይሆናል።

ኢትዮጵያ ቡና ወልቂጤ ከተማን ሲገጥም በሜዳ ላይ ተደጋጋሚ ጉዳቶች መታየታቸው ከነገው ጨዋታ በፊት ስጋትን የሚጭርበት ነበር። ሆኖም የሀብታመ ታደሰ እና ወንድሜነህ ደረጄ ወደ ልምምድ መመለስ እንዲሁም በጨዋታው ምቾት አጥተው የታዩት ምንተስኖት ከበደ ፣ ሬድዋን ናስር እና ታፈሰ ሰለሞን መልካም ጤንነት ላይ መገኘት ለአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ እፎይታ ነው። ነገ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ የሆነው ኃይሌ ገብረትንሳይ ውጪ አስራት ቱንጆም ለነገው ጨዋታ ዝግጁ እንደሆነ ተስምቷል። ከውጤት ባሻገር በአካል ብቃቱ ረገድ ጥሩ ዓመት እያሳለፉ የሚገኙት ፋሲል ከነማዎችም ሙሉ ስብስባቸው መልካም ጤንነት ላይ ሆኖ ነው ለነገው ጨዋታ የሚደርሱት።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ክለቦቹ እስካሁን በተገናኙባቸው ሰባት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና ሦስት ጊዜ ፋሲል ከነማ ደግሞ ሁለት ጊዜ ማሸነፍ ችለዋል። ቀሪዎቹን ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ያጠናቀቁ ሲሆን እስካሁንም ኢትዮጵያ ቡና 10 ፋሲል ከነማ ደግሞ 6 ግቦችን ማስመዝገብ ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

አቤል ማሞ

እያሱ ታምሩ – ወንድሜነህ ደረጄ – አበበ ጥላሁን – አሥራት ቱንጆ

ታፈሰ ሰለሞን – ረመዳን ናስር – ፍቅረየሱ ተወልደብርሀን

ሚኪያስ መኮንን – አቡበከር ናስር – ሀብታሙ ታደሰ

ፋሲል ከነማ (4-2-3-1)

ሚኬል ሳማኬ

እንየው ካሳሁን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

ሀብታሙ ተከስተ – በዛብህ መለዮ

በረከት ደስታ – ሱራፌል ጌታቸው – ሽመክት ጉግሳ

ሙጂብ ቃሲም


© ሶከር ኢትዮጵያ