የሁለተኛ ዙር የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ-ግብር ከሆነው ጨዋታ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከቡድኖቹ አሠልጣኞች አስተያየት ተቀብሏል።
ፋሲል ተካልኝ – ባህር ዳር ከተማ
ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ድል ስለማግኘቱ?
ከባድ ነበር። ባለፉት ጨዋታዎች ነጥብ በመጣላችን ምክንያት ተጫዋቾቼ ውጥረት ውስጥ ሆነው ነበር እየተጫወቱ የነበሩት። የዛሬውም ድል ለተጫዋቾቼም ሆነ ለአሠልጣኝ ቡድን አባላቱ ብዙ ነገር ማለት ነው። ደጋፊዎቻችን ከዚህ የተሻለ ውጤት እንዲሁም ከዚህ የተሻለ ቡድን ሜዳ ላይ እንደሚፈልጉ አውቃለሁ። ለዚህም ደግሞ ጠንክረን እንሰራለን።
ቡድኑ እየተመራ የመጀመሪያውን አጋማሽ ስለማገባደዱ እና መልበሻ ክፍል ስለነበረው ስሜት?
መልበሻ ክፍል ቁጭቶች ይታዩ ነበር። ጨዋታው ከአቅማችን በላይ አልነበረም። በተለይ በተቃራኒ ሜዳ በጣም ቀላል ኳሶች ይበላሹብን ነበር። በተቻለን መጠንም ይህንን ለማስተካከል እና የተጫዋቾቻችንን ስነ-ልቦና ከፍ ለማድረግ ነበር የሞከርነው። በሁለተኛው አጋማሸም ቶሎ ግብ ማግባታችን ጨዋታውን እንድናሸንፍ ረድቶናል ብዬ አስባለሁ።
ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና
ስለ ጨዋታው?
የምንችለውን ሁሉ አድርገን ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ነበር ጥረታችን። ዕድሉንም አግኝተን መርተን ነበር። ከዚህም አልፎ ጨዋታውን የምንጨርስበት ዕድል አግኝተን ነበር። ግን ግልፅ የነበሩ የዳኝነት ውሳኔዎች ከባድ ሆነውብን ነበር። ዳኛውም እንዴት እንዳለፈው አላቅም። ከዛ በኋላ ግን መረጋጋት አልተቻለም። የዛሬው ሽንፈት የሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ነው። ግን ብዙ ስራ ይጠብቀናል። የተወሰኑ ተጫዋቾችን አስተካክለን እና አደራጅተን በቀጣይ ከዚህ አደጋ ለመውጣት ጥረት እናደርጋለን።
አዲሱ አቱላ በመጀመሪያው አጋማሽ ተቀይሮ ገብቶ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ስለመውጣቱ?
የምፈልገውን ነገር አልሰራልኝም። እርግጥ እርሱ ብቻ ሳይሆን ብዙዎቹ ተጫዋቾች ችግር ይታይባቸዋል። ይህም ብዙ ነገሮች መቀየር እንዳለባቸው እና መስራት እንዳለብን የሚያሳይ ነው። ይህንንም ለማድረግ እንሞክራለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ