ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ተጠባቂው ጨዋታ በንግድ ባንክ አሸናፊነት ተጠናቋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአስራ አራተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ተጠባቂ ጨዋታ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መከላከያ መካከል ተከናውኖ በንግድ ባንክ 2ለ0 አሸናፊነት፡፡

10፡00 ሲል በፌዴራል ዳኛ ምስጋና ጥላሁን መሪነት የጀመረው ጨዋታ እስኪጋመስ የንግድ ባንክ የተሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እንዲሁም ወደ ሳጥን ቶሎ ቶሎ በመጠጋት አደጋ በተጋጣሚው መከላከያ ላይ በመውሰድ የበላይነትን ማሳየት የቻለበት ነበር፡፡ በፈጣን ሽግግር በሰናይት ቦጋለ ከሚመራው የመሀል ክፍል በሚገኙ ኳሶች ወደ መከላከያ የግብ ክልል ለመድረስ ያልተቸገሩት ንግድ ባንኮች ቀዳሚ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል፡፡ 11ኛው ደቂቃ ላይ ረሂማ ዘርጋው ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት በግምት ከ35 ሜትር ርቀት በሁለት ጨዋታዎች በጉዳት ሳትሰለፍ ቀርታ ዛሬ ወደ ሜዳ የተመለሰችሁ ልማደኛዋ አጥቂ ሎዛ አበራ እጅግ ግሩም ግብ ከመረብ አዋህዳ ባንክን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡

ንግድ ባንኮች አሁንም በተሻለ በመልሶ ማጥቃት እና በመስመር አጨዋወት በተለይ አመዛኙን ወደ አረጋሽ ካልሳ በማዘንበል ሲጫወት የታየ ሲሆን መከላከያዎች በሂደት ካልሆነ በቀር አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች መሀል ሜዳ ላይ ብቻ ተገድበው ሲጫወቱ ተስተውሏል፡፡ በዚህም የጨዋታ መንገድ ከቀኝ ከግራ በኩል አረጋሽ ካልሳ እና ሰናይት ቦጋለ ባደረጉት እጅግ ማራኪ ቅብብል በመጨረሻም ሰናይት ለሎዛ አመቻታ ከሰጠቻት በኃላ በፍጥነት ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረችው ረሂማ አቀብላት አምበሏም ሁለተኛውን ጎል አስቆጥራ የንግድ ባንክን የግብ መጠን ወደ ሁለት ለምንም አሳድጋለች፡፡

ሁለት ጎል ለማስተናገድ የተገደዱት መከላከያዎች ልክ ከ30ኛው ደቂቃ በኃላ ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመግባት ጥረት አድርገዋል። በዚህም ከቅጣት ምት አይዳ ዑስማን ሞክራ ንግስቲ መዐዛ የመለሰችባት እና ስራ ይርዳው ከርቀት ሞክራ ለጥቂት የወጣባት የሚጠቀሱ የመከላከያ ሙከራዎች ናቸው፡፡ ቡድኑ ምንም እንኳን ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረቶች ይታዩበት እንጂ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ግን ግላዊ እንቅስቃሴን ማዘውተራቸው እክል የፈጠረባቸው እንደሚመስል መመልከት ይቻላል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለት ለዜሮ እየተመሩ ጨዋታውን የቀጠሉት መከላከያዎች የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ዳግም ቢመለሱም በአጥቂ መስመር የተሰለፉት አጥቂዎች ኳስን ከየትኛውም አቅጣጫ በሚያገኙበት ወቅት እንደ ቡድን ከመንቀሳቀስ ይልቅ በግል ጥረትን ለማድረግ ሲሞክሩ ያገኟቸውን ጥቂት ዕድሎች ለማምከን ተገደዋል፡፡

ከመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቀዝ ብለው መታየት ቢችሉም ተሻጋሪ ኳሶቻቸው አደገኛ እንደሆኑ የሚስተዋልባቸው ንግድ ባንኮች በተደጋጋሚ ሙከራን ሲያደርጉ ግን ተመልከተናል፡፡ ከግራ በኩል ወደ መሀል አዘንብላ አረጋሽ ካልሳ ሰጥታ ሰናይት ከመሀል ሾልካ ወጥታ በቀጥታ ስትመታ ታሪኳ በርገና እንደምንም አውጥታባታለች፡፡

ጨዋታው ሊጠናቀቅ 20 ደቂቃ ሲቀረው ጫን ብሎ ለመጫወት ሙከራን ሲያደርጉ የነበሩት መከላከያዎች በመዲና ዐወል በሁለት አጋጣሚ ዕድል አግኝቶ መጠቀም አልቻሉም፡፡ በተለይ 80ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ በኩል መሳይ ተመስገን ከርቀት የተገኘን ቅጣት ምት በቀጥታ አክርራ መታ የግቡ የላይኛው ብረት የመለሰባት ምናልባት መከላከያን ወደ ጨዋታ ልትመልስ የምትችል ብትሆንም ሳይሳካ ቀርቶ ጨዋታው በመጀመሪያ አርባ አምስት በተቆጠሩ ሁለት ጎሎች ንግድ ባንክ 2ለ0 አሸናፊ ሆኗል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ሰናይት ቦጋለ በልሳን የሴቶች ስፖርት የጨዋታው ምርጥ ተብላለች፡፡

በየጨዋታው የአዳማ ስታዲየም በተደጋጋሚ እንስሳት ወደ ሜዳ ሲገቡ እያስተዋልን ሲሆን ይህም ጨዋታን ሲረብሽ መመልከት ችለናል። ይህ በተደጋጋሚ የሚታይ ችግር ላይ በሚገባ ቁጥጥር መደረግ ይኖርበታል የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ እንወዳለን፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ