ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

በዚህ የጨዋታ ሳምንት ላይ ትኩረት ያገኙ የተጫዋቾች ነክ ጉዳዮችን በሚከተለው መልኩ ተመልክተናቸዋል።

👉 አዲሶቹ ተጫዋቾች

የውድድር ዘመኑ አጋማሽ የዝውውር መስኮት የአንደኛው ዙር መጠናቀቅን ተከትሎ ተከፍቷል። በኢትዮጵያ እግርኳስ በዚህ የዝውውር መስኮት ከሌላው ዓለም በተለየ በርካታ ተጫዋቾች በገበያ ላይ የሚገኙ በመሆኑ ክለቦች በስብስባቸው ላይ የተለየ ጥንካሬ ከሚጨምር አንድ እና ሁለት ዝውውር ይልቅ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ሲያስፈርሙ ይስተዋላል። በትግራይ ክልል ክለቦች አለመሳተፍ ምክንያት ያለ ክለብ የተቀመጡ በርካታ ተጫዋቾች መኖርም ለክለቦች አማራጭ ፈጥሮላቸዋል።

እስካሁን ወላይታ ድቻ፣ ሲዳማ ቡና፣ ጅማ አባ ጅፋር፣ አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ በርከት ያሉ ዝውውሮች ሲፈፅሙ ወልቂጤ ከተማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ሰበታ ከተማ አንድ አንድ ተጫዋች ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል።

በዚህ ሳምንት ወላይታ ድቻ ሁለት ተጫዋቾችን (አስናቀ እና ነፃነት) በመጀመርያ አሰላለፍ ሲጠቀም በተጠባባቂ ወንበር ላይ አንድ (ዮናስ) ተጫዋች አስቀምጦ ጨዋታ አድርጓል። ሲዳማ ቡና ሦስት (ዮናስ፣ መሐሪ እና ሽመልስ) ተጫዋቾች በመጀመርያ አሰላለፍ ሲጠቀም አንድ (ያሬድ) ከተጠባባቂ ወንበር ተነስቶ ጨዋታ አድርጓል። አዳማ ከተማ ሁለት (አሚን እና ኤልያስ አህመድ) ሲጠቀም ሁለት (ኤልያስ ማሞ እና ሰይፈ ዛኪር) ቀይሮ በማስገባት አጫውቷል። ሀብታሙ ወልዴ እና ያሬድ ብርሀኑ በተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበሩ ሌሎች አዲስ ፈራሚዎች ነበሩ። ጅማ አማኑኤል ተሾመን የተጠቀመ ሌላው ቡድን ነው።

የዝውውር መስኮቱ ገና መጀመርያው ወቅት ላይ እንደመሆኑ በርካታ ዝውውሮች ሲጠበቁ ክለቦችን ተቀላቅለው ጨዋታ ያላደረጉ ተጫዋቾች በቀጣይ ጨዋታዎች ላይ የመጫወት እድል እንደሚያገኙ ይጠበቃል።

👉 ለየት ያለው የፍፁም ገ/ማርያም የደስታ አገላለፅ

በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ፉክክር እና አራት ግቦችን ባስተናገደው የሰበታ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ላይ ፍፁም ገ/ማርያም ለሰበታ ከተማ ሁለቱንም ግቦች ማስቆጠሩ ይታወሳል።

ታድያ ለወትሮውም ግቦች ካስቆጠረ በኋላ የተለመደ የደስታ አገላገፅን ሲያሳይ የምናውቀው ፍፁም ገ/ማርያም በዚህኛው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማ መረብ ላይ ሁለተኛዋን ግብ ካስቆጠረ በኃላ ያሳየው የደስታ አገላለፅ ግን የተለየ ነበር። በቀጥታ እየሮጠ ወደ የማዕዘን ምት መምቻው አካባቢ የሄደው ተጫዋቹ አየር ላይ ተነስቶ እግሮቹን እና እጁን ለየት ባለ መልኩ ካወናጨፈ በኃላ ሜዳው ላይ በደረቱ ተኝቶ በሜዳው ጠርዝ ወደተቀመጠው የሱፐር ስፖርት ቡም ማይክ ጠጋ ብሎ “ሀሎ ሀሎ” በሚል ድምፁን ያሰማበት ቅፅበት ለየት ያለ ነበር።

ከጨዋታው በኋላ ከሱፐር ስፖርት ጋር አጭር ቆይታን ያደረገው ተጫዋቹ ስለደስታ አገላለጹ ተጠይቆ ስሜታዊ ስለነበር ስላደረገው ነገር በውል እንደማያውቅ ሀሳቡን ሰጥቷል።

👉 ባህሩ ነጋሽ እና ዮሐንስ በዛብህ ወደ ሜዳ ተመልሰዋል

በቋሚዎቹ መካከል ከሳምንት ሳምንት በቋሚነት የሚያገለግል አስተማማኝ ግብ ጠባቂ ያጡ የሚመስሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በፋሲል ከነማ በተረቱበት ጨዋታ ላይ ደግሞ ባህሩ ነጋሽን ተጠቅመዋል።

በተሰረዘው የውድድር ዘመን በተጫዋቾች ጉዳት መነሻነት በአዲስ አበባ ዋንጫ የመሰለፍ ዕድል ያገኘው ተጫዋቹ ባሳየው አስደናቂ ብቃት መነሻነት በሊጉ የመጀመርያዎቹ በርካታ ጨዋታዎች ላይ በመሰለፍ ድንቅ ብቃቱን ማሳየቱ የማይዘነጋ ነበር። ዘንድሮም ምንም እንኳን የፋሲል ከነማው ጨዋታ የውድድር ዘመኑ የመጀመሪያው ጨዋታ ቢሆንም በሁለት አጋጣሚዎች የተሰነዘሩበትን ጠንካራ ሙከራዎች ማክሸፍ ችሏል። በቀጣይም በፋሲሉ ጨዋታ ያሳየውን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን እያሳደገ መሄድ የሚችል ከሆነ በቦታው በተመራጭነት የመዝልቅ ዕድል ይኖረዋል።

ከዚህ ቀደም ማታሲ እና ለዓለምን የተጠቀመው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ከተማ በመቀጠል በስብስቡ ያስመዘገባቸውን ሦስቱንም ግብ ጠባቂዎች ከወዲሁ መጠቀም የቻለ ሁለተኛው ቡድን ሆኖ ተመዝግቧል።

በተመሳሳይ በሊጉ ከሚገኙ ግብ ጠባቂዎች መካከል በእግር ኳስን በመጫወት ረገድ ከፍ ያለ ቦታ ከሚሰጣቸው ግብ ጠባቂዎች አንዱ የሆነው ዮሐንስ በዛብህ በወልቂጤ ከተማ መለያ የመጀመሪያውን ጨዋታ በዚህ ሳምንት ማድረግ ችሏል።

እንደ አዳማ እና ጊዮርጊስ ሁሉ ሦስቱንም ግብ ጠባቂዎቻቸውን እስካሁን መጠቀም የቻሉት ወልቂጤ ከተማዎች ጀማል ጣሰው በቅጣት አለመኖሩን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት ያገኘውን ዕድል ባልተጠቀመው ጆርጅ ደስታ ምትክ ዮሐንስ በዛብህን አሰልፈው ነበር።

👉 የሀብታሙ ገዛኸኝ ሁለተኛ ቢጫ እና የሲዳማ ተጫዋቾች መሰላቸት

አዲስ አሰልጣኝ ቢቀጥርም ወደ ውጤት መመለስ የተሳነው ሲዳማ ቡና ከጨዋታ ጨዋታ በሜዳ ላይ ከሚያሳየው ደካማ እንቅስቃሴ ባለፈ የቡድኑ ተጫዋቾች በውጤት አልባ ጉዞው በመነጨ የመሰላቸት ስሜት የሚሰሯቸው ተደጋጋሚ ጥፋቶች ቡድኑን ዋጋ እያስከፈሉ ይገኛል።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ሁለተኛ አምበላቸው ፈቱዲን ጀማልን በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ መወገዱን ተከትሎ በባህር ዳሩ ጨዋታ መጠቀም ያልቻሉ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ሀብታሙ ገዛኸኝ በግልፅ መሰላቸት በሰራው ጥፋት እንዲሁ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ለመወገድ በቅቷል።

በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ሁለት ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን በቀይ ካርድ ያጡት አዲሱ አሰልጣኝ ገብረመድህን እንደ አዲስ ለማዋቀር እየጣሩ በሚገኙት ስብስብ ውስጥ በቡድኑ የኋላ እና የፊት መስመር ላይ ትልቅ ድርሻ ያላቸውን እነዚህን ተጨዋቾች ማጣታቸው የሚፈጠረው ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

👉 ዕድለ ቢሶቹ አስናቀ ሞገስ እና ይገዙ ቦጋለ

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በተለያየ ምክንያት ወደራቁበት የእግርኳስ ሜዳ የተመለሱት አስናቀ ሞገስ እና ይገዙ ቦጋለ እንዳለመታደል ሆኖ በሜዳ ላይ መቆየት የቻሉት በጣም ለጥቂት ደቂቃዎች ነበር።

የመጀመሪያውን ዙር ያለ ክለብ ያሳለፈው አስናቀ ሞገስ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሁለተኛው ዙር ለወላይታ ድቻ ለመጫወት ፊርማውን ማኖሩ ይታወሳል። ታድያ ለግማሽ የውድድር ዘመን ያህል ከእንቅስቃሴ ርቆ የነበረው ተጫዋቹ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ለአዲሱ ክለቡ ወላይታ ድቻ የመጀመሪያውን ጨዋታ ለማድረግ ወደ ሜዳ ቢገባም ከሰባት ደቂቃዎች ቆይታ በኃላ ግን ትከሻው ላይ ባስተናገደው ጉዳት ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።

በተመሳሳይ በጉዳት ክለቡን በአግባቡ ለማገልገል እየተቸገረ የሚገኘው የሲዳማ ቡናው አጥቂ ይገዙ ቦጋለ ከረጅም ጊዜ በኃላ ባህር ዳርን ሲገጥሙ ወደ ሜዳ መመለስ ቢችልም ሜዳ ላይ የቆየው ለአስራ አምስት ደቂቃዎች ብቻ ነበር። ከሀሪሰን ሄሱ ጋር የተጋጨው ተጫዋቹ ለቡድኑ ፍፁም ቅጣት ምት ቢያስገኝም እሱ ግን ከሜዳ የሚያስወጣውን ጉዳት በሒደቱ አስናግዷል።

👉 የወንድማማቾቹ ሳምንት

ይህኛው የጨዋታ ሳምንት በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በተቃራኒ ያገናኘ የጨዋታ ሳምንት ነበር።

ባህር ዳር ከተማን ከሲዳማ ቡና ባገናኘው ጨዋታ ባዬ ገዛኸኝ በባህርዳር እንዲሁም ሀብታሙ ገዛኸኝን በሲዳማ ቡና በኩል ሜዳ ላይ በቋሚ ተሰላፊነት አገናኝቶ ባዬ ለ82 ደቂቃ በሜዳ ላይ ሲቆይ ሀብታሙ ገዛኸኝ በጭማሪ ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ከሜማ ወጥቷል።

በዚሁ ጨዋታ በባህርዳር ከተማ በኩል የመጀመሪያ ተሰላፊ የነበረው ሰለሞን ወዴሳ በተቃራኒው በተጠባባቂ ወንበር የነበረው ግብ ጠባቂው ፍቅሩ ወዴሳን መርታት ችሏል።

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ቡና ከወልቂጤ ከተማ ባገናኘው ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡናዎቹ ሬድዋን ናስር እና አቡበከር ናስር በቅርቡ ወልቂጤ ከተማን የተቀላቀለው ታላቅ ወንድማቸውን ጅብሪል ናስርን መርታት ችለዋል።

በዚህ ሳምንተ ሌላውን የቤተሰብ ግንኙነት ያስተናገደው ጨዋታ የአዳማ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ጨዋታ ነበር። በጅማ በኩል መላኩ ወልዴ ቡድኑ ባሸነፈበት ጨዋታ ሙሉ ዘጠና ደቂቃ በሜዳ ላይ ሲያሳል በዝውውር መስኮቱ አዳማን የተቀላቀለው ታናሽ ወንድሙ ሀብታሙ ወልዴ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ሆኖ ጨዋታውን ጨርሷል።

👉 ወደ ውድድር የተመለሱት ተጫዋቾች

የትግራይ ክልል ክለቦች በወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ በሊጉ መካፈል አለመቻላቸውን ተከትሎ በክለቦቹ የነበሩ በርካታ ተጫዋቾች ወደ ሌሎች ክለቦች የመዘዋወር ፍቃድን ቢያገኙም ዕድሉን የተጠቀሙ እድዳሉ ሆነው በርካቶች ያለ ክለብ የውድድር ዘመኑን አጋማሽ ለማሳለፍ መገደዳቸው ይታወሳል።

የዝውውር መስኮቱ ገና ባይጠናቀቅም በተለይ በአንደኛውን ዙር ቀዳዳ የበዛባቸው ክለቦች ክፍተታቸውን ለመድፈን ወደነዚህ ተጫዋቾች በማማተር አዘዋውረዋል። ከእነዚህም መካከል አስናቀ ሞገስ እና ነፃነት ገብረመድኅን ለወላይታ ድቻ፣ ሽመልስ ተገኝ፣ ዮናስ ገረመው እና ያሬድ ከበደ ደግሞ ለሲዳማ ቡና ጨዋታ አድርገዋል።

ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት ጨዋታ ካላደረጉት ተጫዋቾች በተጨማሪ በውድድር ዘመኑ ያለ ክለብ ቆይቶ የነበረው መሐሪ መናም በሲዳማ ቡና መለያ ጨዋታ አድርጓል።

👉እዮብ ማቲዎስ እና ያስቆጠራት ግብ

ጅማ አባ ጅፋሮች አዳማ ከተማን 2-1 በረቱበት ጨዋታ ላይ አዳማዎች ከመመራት ተነስተው አቻ የሆኑባትን ግብ ወጣቱ ተከላካይ እዮብ ማቲዎስ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በተሰጠ ሁለተኛ ቅጣት ምት ማስቆጠር ችሏል።

የሁለተኛ ቅጣት ምት በዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ሳይሰጥ የቆየ ሲሆን በአዳማ እና ጅማ ጨዋታ ላይ በሁለት አጋጣሚዎች ዋና ዳኛው ኃይለየሱስ ባዘዘው ሰጥተዋል። የመጀመርያው ታፈሰ ሰርካ ወደ ኋላ የመለሰውን ኳስ ዳንኤል ተሾመ በእጁ በመያዙ የተሰጠ ሲሆን የጅማው መላኩ ወልዴ መትቶት በተከላካዮች ተደርቦ ወጥቶበታል። ሁለተኛው ደግሞ ኢላማውን ያልጠበቀ ቀለል ያለ ኳስ የተመታበት አቡበከር ኑሪ ኳሱን ለማቆም እና ኋላ ላይ ደግሞ ለመያዝ ሁለት ጊዜ እጁን በመጠቀሙ የተሰጠ ሲሆን እዮብ ማቲያስ ከኤልያስ ማሞ ጋር ተቀባብሎ አስቆጥሮታል።

ይህች የእዮብ ማቲዮስ ጎል በ2009 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ግዙፉ ናይጄሪያዊ አጥቂ ፒተር ኑዋዲኬ ኤሌክትሪክ ላይ ካስቆጠረው ጎል በኋላ የተቆጠረች መሆኗ ታሪካዊ ያደርጋታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ