ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

በዚህ ሳምንት ትኩረት ያገኙ አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች እንዲሁም ዐበይት አስተያየቶች እንዲከተለው ቀርበዋል።

👉 የገብረመድህን ኃይሌ የመጀመሪያ ነጥብ ፍለጋ ቀጥሏል

ከቀናት በፊት አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን ተክተው የሲዳማ ቡና ዋና አሰልጣኝ በመሆን የተሾሙት ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመናት በተከታታይ የሊጉ ሻምፒየን የነበሩት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ አዲሱን ቡድኑን እየመሩ እስካሁን ምንም ነጥብ ማሳካት አልቻሉም።

እርግጥ ነው ስብስቡን ከተረከቡ ገና ጥቂት ቀናት ቢቆጠሩም አሰልጣኙ በአፋጣኝ ቡድኑን ወደ ውጤት በመመለስ በሊጉ የማቆየትን ዓላማ ይዘው ኃላፊነቱን እንደወሰዱ አሰልጣኝ እያንዳንዱ ጨዋታ ከሚኖረው ትርጉም አንፃር እስካሁን ውጤት መያዝ ያለመቻላቸው ነገር አነጋጋሪ ነው።

በስብስብ ደረጃ አምና ተፎካካሪ ከነበረው ስብስብ አንድ አዲስ ግደይን ብቻ ያጣው ቡድኑ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ጥሩ በሚባለው ስብስባቸው ላይ ሌሎች ተጨማሪ የቡድኑን ጥራት የሚያሳድጉ ተጫዋቾችን እያዘዋወረ ይገኛል። ታድያ የቡድኑን እንቅስቃሴ ግን ለተከታተለ ቡድኑ በአንድ ተጫዋች መልቀቅ ብቻ በዚህ ደረጃ የመውረዱ ነገር በጣም የሚያስገርም ነው።

አሁንም ቢሆን ፊት ላይ ያለው የአጥቂ መስመሩ ችግር የመሻሻል ነገር ባያሳይም በቀጣይ አዳዲስ ከመጡት ተጫዋቾች በተለይ ይህን ጊዜ የማይሰጥ አጣዳፊ ችግር የመቅረፍ ኃላፊነት በአሰልጣኙ እና በተጫዋቹ ጫንቃ ላይ ያረፈ ነው።

👉በአንድ የውድድር ዘመን ሁለተኛ ክለባቸውን የመሩት ዘርዓይ ሙሉ

በቅርቡ ከሲዳማ ቡና ጋር የተለያዩት አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ከቀናት ዕረፍት በኋላ ደግሞ ላለመውረድ የሚታገለውን ሌላኛውን ክለብ አዳማ ከተማን ተረክበው ቡድኑን እየመሩ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ከአሰልጣኝ ዓለማየሁ ዓባይነህ ስንብት በኋላ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሲዳማ ቡናን በሰንጠረዡ አናት ተፎካካሪነቱን አስጠብቀው የዘለቁት አሰልጣኙ ዘንድሮ ይህን ማድረግ አልተቻላቸውም። በ21 ቀናት ልዩነትም ከቀደመው ፈተና በተለየ ፈተና በአዲስ ኃላፊነት ብቅ ብለዋል።

የተጫዋቾች የጥራት ችግር የነበረበትን የአዳማ ስብስብ በምን ያህል ደረጃ አሻሽለው ቡድኑን በሊጉ የማቆየትን ፈተና እንዴት ይወጡት ይሆን ? የሚለው ጉዳይ በጥቂት ወራት ምላሽ የሚያገኝ ይሆናል።

👉በአሰልጣኞች ላይ የሚነበበው እርግጠኝነት

ፕሪምየር ሊጉ ከቀደመው የውድድር ቅርፁ ወጥቶ በተመረጡ ከተማዎች መከናወን ላይ መገኘቱ ለአሰልጣኞች የልብ ልብ የሰጠ ይመስላል።

የወራጅነት ስጋት የተደቀነባቸው ቡድኖች ሆነ በሰንጠረዡ አናት የሚገኙ ቡድኖች በቡድኖቻቸው ያሉትን ተግዳሮቶች መቅረፍ ከቻሉ ውጤቶችን መቀልበስ እንደሚችሉ ማመን ጀምረዋል። ይህ በተለይ አሰልቺ ገፅታን ይላበስ የነበረው ሁለተኛው ዙር የሊግ ውድድርን ነብስ ይዘራበታል ተብሎ ይጠበቃል።

አሰልጣኞቹ በሚሰጡት አስተያየት ይህን መገንዘብ ይቻላል። ውድድሩ ነብስ ይዘራ ይሆን የሚለው ነገር በሂደት የሚታይ ቢሆንም ከሜዳ ውጪ ያሉ እግርኳሳዊ ያልሆኑ ጫናዎች እንደመወገዳቸው ከጥንቃቄ መር አሰልቺ አቀራረቦች ወጥተው አሰልጣኞች መሸናነፍን ታሳቢ ያደረጉ አዝናኝ ጨዋታዎችን ለማየት እንበቃ ይሆን ?

👉ዓድዋን የዘከሩት የአሰልጣኝ ቡድን አባላት

ሲዳማ ቡና ከባህር ዳር ከተማ ባደረጉት እና በዕለተ አድዋ በተከናወነው የጨዋታ መርሃግብር የባህርዳር ከተማ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ከተለመደው ወጣ ያለን አለባበስ ለብሰው ተመልክተናል።

ከአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ውጭ የነበሩት የባህር ዳር ከተማ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት የዓድዋ ድልን የሚዘክርን ቲሸርት ለብሰው ጨዋታ ሲመሩ ተመልክተናል።

👉በውድድሩ አጋማሽ የሚደረጉ ዝውውሮች እና የቡድን ውህደት

በአብዛኞች አሰልጣኞች ዘንድ በተለይ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ የሚደረጉ ዝውውሮች አስገዳጅ ሁኔታዎች እስካልተፈጠሩ ድረስ እምብዛም የሚመከሩ አይደሉም። በሀገራችን ግን በተለይ ከሰንጠረዡ በወገብ በታች በሚገኙ ቡድኖች ዘንድ የፋይናንስ አቅርቦቱ እስከተገኘ ድረስ በገፍ ተጫዋቾች የማዘዋወር ዝንባሌ ይታያል።

ታድያ የቀደሙትን ጊዜያት ወደ ጎን ትተን ለየት ያለ መልክን በተላበሰው እና በመጀመሪያው ዙር መጠናቀቅ እና በሁለተኛ ዙር መጀመር መካከል ሦስት ያህል ቀናት ብቻ ልዩነት ባሉበት የዘንድሮው ውድድር ክለቦች እንደቀመው ጊዜ ተጫዋቾችን ከፍ ባለ ቁጥር እያዘዋወሩ ይገኛል።

ለየትኛውም አሰልጣኝ ሆነ ተጫዋች በአዲሱ ክለቡ ከሁኔታዎች ጋር ራሱን አስተካክሎ በሚጠበቀው ደረጃ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር የተወሰነ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ቢታመንም አሁን ባለው ሁኔታ ግን ተጫዋቾች ከአዲሶቹ ክለቦቻቸው ጋር ለጥቂት ቀናት ልምምድ ብቻ ሰርተው ተፅኗቸውን እንዲያሳዩ እየተጠበቀ ነው። ነገርግን እውነታው ይህ ነው የሚባል ከውድድር በፊት ከቡድኑ ጋር የመዘጋጃ ጊዜ ተጫዋቹ ባላገኙበት ሁኔታ የፉክክር ጨዋታዎችን እንደ ቅድመ ውድድር ጊዜያት የመጠቀማቸው ነገር የግድ የሆነ ይመስላል።

ታድያ በዚህ ሒደት ውስጥ በአዳማ ከተማ ደረጃ አፋጣኝ ውጤትን የሚሹ ቡድኖች እነዚህን አዳዲስ ተጫዋቾች ይዘው በፍጥነት ወደ ውጤት ጉዳና ሊመጡ ይችላሉ የሚለው ጉዳይ የሚጠበቅ ነው።

ዓበይት አስተያየቶች

👉ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ስለቡድኑ የመሻሻል ሒደት

“ባለን ስብስብ እየሄድን ያለበት መንገድ ጥሩ ነው። የተወሰነ መሻሻል እንደሚያስፈልገን ጨዋታው ያሳያል። ነገር ግን እኔ የተደሰትኩት ከመጀመሪያው ጨዋታ ሁለተኛው ጨዋታ የተሻለ ነው። ወደ ጎል የምንሄድበት መንገድ በጣም ጥሩ ነው ፤ ግን ትንሽ ስል አይደለንም። እሱ ላይ የተሻለ ነገር መስራት ከቻልን ተወዳዳሪ የማንሆንበት ምክንያት የለም።”

👉አብርሀም መብራቱ ኦሲ ማውሊ መፈረሙ ስላለው ጥቅም

“ማወሊ አግቢ ብቻም ሳይሆን ሰጪም ጭምር ነው። ሁለተኛ ደግሞ የእኛ ቡድን አጨዋወት ኳሱን ይዞ ወደ ተጋጣሚ ግብ መቅረብ ነው። ስለዚህ እዛ ቦታ ላይ ኳሱን ይዞ የሚቆይ ሰው ያስፈልገናል። ማወሊ ቡድናችንን መቀላቀሉ ማግባት ብቻ ሳይሆን በማጥቃት አጨዋወቱ ላይ የጎላ ሚና የኖረዋል ብዬ አስባለሁ።”

👉ፋሲል ተካልኝ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ድል ስለማግኘታቸው

“ከባድ ነበር። ባለፉት ጨዋታዎች ነጥብ በመጣላችን ምክንያት ተጫዋቾቼ ውጥረት ውስጥ ሆነው ነበር እየተጫወቱ የነበሩት። የዛሬውም ድል ለተጫዋቾቼም ሆነ ለአሠልጣኝ ቡድን አባላቱ ብዙ ነገር ማለት ነው። ደጋፊዎቻችን ከዚህ የተሻለ ውጤት እንዲሁም ከዚህ የተሻለ ቡድን ሜዳ ላይ እንደሚፈልጉ አውቃለሁ። ለዚህም ደግሞ ጠንክረን እንሰራለን።”

👉ገብረመድህን ኃይሌ በባህርዳር ስለተሸነፉበት ጨዋታ

“የምንችለውን ሁሉ አድርገን ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ነበር ጥረታችን። ዕድሉንም አግኝተን መርተን ነበር። ከዚህም አልፎ ጨዋታውን የምንጨርስበት ዕድል አግኝተን ነበር። ግን ግልፅ የነበሩ የዳኝነት ውሳኔዎች ከባድ ሆነውብን ነበር። ዳኛውም እንዴት እንዳለፈው አላቅም። ከዛ በኋላ ግን መረጋጋት አልተቻለም። የዛሬው ሽንፈት የሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ነው። ግን ብዙ ስራ ይጠብቀናል። የተወሰኑ ተጫዋቾችን አስተካክለን እና አደራጅተን በቀጣይ ከዚህ አደጋ ለመውጣት ጥረት እናደርጋለን።”

👉ካሣዬ አራጌ ከጨዋታ ይልቅ ለውጤት ቅድሚያ ስለመስጠታቸው

“እኛ ሁሌም በመጫወት ውስጥ ነው ውጤት የሚመጣው ብለን ነው የምናስበው። የግዴታ ጨዋታውን መቆጣጠር አለብህ ውጤት ለማምጣት። ምንአልባት በዛሬው ዓይነት ሁኔታ ውጤት ልታመጣ ትችላለህ። ግን ጨዋታውን ባልተቆጣጠርክበት ሁኔታ ቀጣይነት አይኖረውም። የነጥቡ መጥበብ እና መስፋት ለእኛ የሚያመጣው ለውጥ የለም። ሁሌም ትኩረታችን ጨዋታውን ተቆጣጥረን ውጤት የምናመጣበት መንገድ ላይ ነው።”

👉ዘላለም ሽፈራው እንደየ ጨዋታው ስለሚቀርብበት የአጨዋወት መንገድ?

“ተጋጣሚ ቡድኖችን አጠናለሁ። የቶርናመንት ውድድር አንዱ ጠቀሜታውም ይሄው ነው። ሁለተኛ ደግሞ ጨዋታው ስለሚተላለፍ በድጋሜ የመመልከት ዕድሉ አለ። ይህ እንደ ቡድን ብቻ አደለም። በተናጥልም ተጋጣሚ ቡድኖች ውስጥ ያሉትን ተጫዋቾች እናጠናለን።”

👉 ዘርዓይ መሉ ቡድኑ ይተርፋል ብለው ስለማሰባቸው

“አዎ ቡድኑ ብዙ ክፍተቶች አሉት። ከክለቡ ኃላፊዎች ጋርም አውርቻለው። በአፋጣኝ ተጫዋቾች መምጣት አለባቸው። ያንን ነገር ማስተካከል የሚቻል ከሆነ አሁንም ልዩነቱ ሰፊ አይደለም። የአራት አምስት ነጥብ ልዩነት ነው። በተለይ መሀል ላይ ተሰብስበው ነው ያሉት ቡድኖች። አንድ ሁለት ጨዋታ ማሸነፍ የሚቻል ከሆነ ተመልሰህ እዛው ጋር ነው የምትደርሰው። ሀሉም ጨዋታዎች እንደፍፃሜ የሚታዩ በመሆኑ እነዚህ ነገሮች ከተስተካከሉ አዳማ በሊጉ ይቆያል ብዬ ነው የማስበው።

👉ፀጋዬ ኪዳነማርያም ቡድኑ ይተርፋል ብለው ስለማሰባቸው

“ይሄማ የግድ ነው! ከፊታችን እኮ 11 ጨዋታዎች ይቀራሉ። በሂሳብ ስሌት ካየነው 33 ነጥቦች ማለት ነው። በፕሪምየር ሊጉ ለመቆየት ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን። ቻምፒዮን የሚሆነውንም የሚወርደውንም ቡድን ለመለየት የ 24ቱም ጨዋታ ውጤት ወሳኝ ነው። እያንዳንዱን ጨዋታ የጥሎ ማለፍ ባህሪ የተላበሰ አጨዋወት እየተጫወትን ውጤታማ ለመሆን እንሞክራለን። ”

👉ሥዩም ከበደ ስለ ዋንጫ ፉክክሩ?

“ከተከታያችን ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት አስፍተን መያዛችን ለእኛ ትልቅ ነገር ነው። በራስ መተማመን ይሰጠናል። ነገርግን ገና 11 ጨዋታ አለ። ይሄንን አስጠብቆ ለመሄድ ትልቅ ስራ ይጠብቀናል። በቀጣይ ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነው የምንጫወተው። በዛም ጨዋታ በተሻለ ቅርፅ ለመቅረብ እንሞክራለን። በአጠቃላይ ትልቅ ነጥብ ነው ዛሬ ያገኘነው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ