ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

የአስራ አራተኛ ሳምንት ዐበይት ጉዳዮችን የምናጠቃልለው እንደተለመደው በአራተኛ ክፍል ጥንቅራችን ነው።

👉125ኛው የአድዋ ድል በባህርዳር ሲዘከር

ታላቁ የጥቁር አፍሪካዊያን የነፃነት ቀን ተደርጎ የሚዘከረው የአድዋ ድል በዓል በበባህርዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም ተዘክሯል። በ14ኛ የጨዋታ ሳምንት የመጨረሻ ቀን የጨዋታ መርሐግብር እና ክብረ በዓሉ መገጣጠሙን ተከትሎ ያልተለመደ እና ሳቢ የነበረ ሁነትን በዕለቱ በተካሄዱት የኢትዮጵያ ቡና እና ወልቂጤ ከተማ እንዲሁም ባህርዳር እና ሲዳማ ጨዋታዎች መስከመር በፊት ተመልክተናል።

ሁለቱም ጨዋታዎች ከመጀመራቸው የቡድኖቹ አሰልጣኞች የዕለቱ የክብር እንግዶች ከነበሩት ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ከሆኑት አቶ ባዘዘው ጫኔ በጠዋቱ ጨዋታ እንዲሁም ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በከሰዓቱ መርሐግብር ጋር በመሆን ለሀገራችን ነፃነት መስዋዕት ለሆኑት ጀግኖች አርበኞች ማስታወሻ የሚሆን የአበባ ጉንጉን ያስቀመጡ ሲሆን ከዚያም በክልሉ የማርሽ ባንድ መሪነት የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ተዘምሮ ጨዋታው የተጀመረበት መንገድ እጅግ የሚደነቅ ነበር።

ይህን የድል በዓል በተለየ የዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ሽፋን በሚያገኙ ሁነቶች ላይ ከፍ ብሎ እንዲታይ መደረጉ በእግርኳሳችን በኩል ታሪካችንን ከማስተዋወቅ አንፃር በጎ ጅምር መሆኑን መጠቆም እንወዳለን። ሥነ ስርዓቱን ለማከናወን ተነሳሽነቱን ከመውሰድ ባለፈ እጅግ ውብ በሆነ ፣ መደናገር ባልታየበት ፣ አሰልጣኞችን ጭምር ተሳታፊ ባደረገ እና ባልተንዛዛ መልኩ እንዲከወን ማድረግ የሚጠይቀውን የሥራ ትጋት በተግባር ስላሳዩን በቦታው ለነበሩ አስተባባሪዎችም ከፍ ያላ ምስጋና ይገባቸዋል።

👉 የፋሲል እና የጊዮርጊስ ጨዋታ መጨረሻ

በ14ኛው ሳምንት ከተደረጉ ጨዋታዎች ሁሉ በላይኛው የደረጃ ሰንጠረዥ ክፍል ላይ ከሚኖረው ተፅዕኖ አንፃር የፋሲል እና የጊዮርጊስን ጨዋታ ያህል ተጠባቂ አልነበረም። ያዛኑ ያህል ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ዘንድሮ ከተካሄዱ ጨዋታዎች ሁሉ ከፍተኛ ወከባ የታየበት ሌላ ጨዋታ ፈልጎ ማግኘትም ይከብዳል ። ለነበረው ግርግር መነሻ የነበረው ደግሞ በጨዋታው ማብቂያ ላይ የዕለቱ አርቢትር ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ የሰጡት የፍፁም ቅጣት ምት ተገቢነት ጉዳይ ነበር።

በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ በተሰጠው እና ጨዋታው በፋሲል አሸናፊነት እንዲደመደም ምክንያት የሆነው ውሳኔ በተለይ ግቡ ከተቆጠረ በኋላ የጊዮርጊስ ተጨዋቾች ፣ አሰልጣኝ ቡድን አባላት እና ደጋፊዎች በከፍተኛ ስሜት ውስጥ ሆነው ተቃውሟቸውን እንዲገልፁ ያደረገ ነበር። የጨዋታው ክብደት፣ ውጤቱን የማጣት ቁጭት በተደጋጋሚ ሲስተዋል የነበረው የዳኞች ውሳኔ በዛን ቅፅበት ከፈጠረው የእርግጠኝነት ስሜት ጋር ተደምሮም ተቃውሞውን ከልክ ሲያሳልፈው ተመልክተናል። እግር ኳስ በባህሪው ስሜታዊ ቢያደርግም ነገሮችን በማረጋጋት እና በሰከነ መንገድ ከማሳለፍ አንፃር በተለይ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ሚና ከፍ ያለ ቢሆንም በወቅቱ የቡድኑ ስብስቡ አባላት ከዳኞች ባለፈ ከስታድየሙ ተንካባካቢዎች ጋር ጭምር የተካረረ ምልልስ ውስጥ መግባታቸው የሚያስወቅስ ነበር። ከዚህ በተቃራኒ በድህረ ጨዋታ አስተያየት ወቅት ዋና አሰልጣኙ ማሂር ዴቪድስ ስሜታቸው ተቆጣጥረው ውሳኔውን በድጋሚ በምስል ማየት እንደሚኖርባቸው የገለፁበት መንገድ ለብዙዎች ትምህርት የሚሰጥ ሆኖ አልፏል።

👉 የማቀዝቀዣ ዕረፍት

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ዙር ውድድር ከሳምንቱ መጨረሻ አንስቶ በባህርዳር ዓለምቀፍ ስታድየም መካሄዱን ቀጠሏል። በሁለተኛው ዙር ውድድር ላይ በአዲስ መልክ ከተመለከትናቸው ጉዳዮች አንዱ በጨዋታዎች መካከል በሁለቱም አጋማሾች ማለትም በ25ኛው እንዲሁም በ75ኛው ደቂቃ የማቀዝቀዣ የውሃ ዕረፍት እንዲኖር መደረጉ ነው።

በተለይ በአሁኑ ወቅት ውድድሩ እየተካሄደባት የምትገኘው የባህርዳር ከተማ ካላት ከፍተኛ ፀሀያማ እንዲሁም ሞቃታማ የአየር ፀባይ አንፃር መሰል የማቀዝቀዣ ዕረፍቶች መኖራቸው ለተጫዋቾች የሚሰጠው ጥቅም የላቀ በመሆኑ መልካም የሚባል ጅማሮ ነው።

👉 የመጫወቻ ኳሶች ጉዳይ

የቅድመ ጨዋታ ዝግጅት አካል ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ በጨዋታ ዕለት ግልጋሎት የሚውሉ ኳሶችን በብዛት እና በሚፈልገው የአየር መጠን ተሞልተው የመዘጋጀታቸው ጉዳይ በቀዳሚነት ከሚከወኑ ተግባራት አንዱ መሆኑ ይታወሳል።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማ ባደረጉት ጨዋታ በሁለት አጋጣሚዎች ጨዋታው እንዲቋረጥ ያስገደዱ በቂ የአየር መጠን ያልተሞሉ ኳሶች ጉዳይ ነበር።

ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ በጅማ ዩኒቨርስቲ ስታድየም ሲዳማ ቡና ከሰበታ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ መሰል የኳሶች ጉዳይ በመጀመሪያ ደቂቃዎች ጨዋታው እንዲቋረጥ ሲያስገድዱ ተመልክተናል ። እርግጥ መሰል ጥቃቅን የሚመስሉ በጥቂት ግለሰቦች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ባለመቻላቸው መነሻነት የሚፈጠሩ ጉድለቶች በቀጥታ የቴሌቪዥን ሽፋን በሚያገኘው ውድድሩ ላይ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ በቀላል የሚታይ ባለመሆኑ አሁንም በጥንቃቄ ሊታዮ ይገባል።

👉 የዳኞች ባጅ ጉዳይ

በኢትዮጵያ ውስጥ በሚካሄድ የተለያዩ የእግርኳስ ውድድሮች ላይ የሚዳኙ ዳኞች ከሚለብሷቸው መለያዎች ላይ በግራ የደረት ኪሳቸው ላይ እንደየደረጃቸው የፊፋን አልያም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን የዳኝነት ባጅን ሲያደርጉ ይስተዋላል።

በቅርቡም በዋቢ ሸበሌ በተደረገ አንድ መርሐግብር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለኢንተርናሽናል ዳኞች የ2021 የፊፋ ባጅ እና ፌዴሬሽን ያሰራውን የዳኞች ትጥቅ ማስረከቡ ይታወሳል። ነገርግን የፌደራል ዳኞች ባጅ ጉዳይ ግን አሁንም ችላ የተባለ ይመስላል።

የፌደራል ዳኞች የሚጠቀሙት ባጅ ለረጅም ዓመታት ግልጋሎት የሰጠ ከመሆኑ መነሻነት የተጎሳቆለ እና በዘመኑ ያልተዋጀ የንድፍ (Design) እና የመስሪያ ቁስ የተሰራ መሆኑ ለተመልካች በግልፅ የሚታይ ነው።

በመሆኑም የሚመለከተው አካል ለዳኞቹ ትጥቅ ማሰራቱ የሚያስመሰግነው ቢሆንም ከባዱን የትጥቅ ጉዳይ ካከናወኑ በኃላ በንፅፅር ትንሿ እና ቀላል በሆነችው የደረት ባጅ ጉዳይን ትኩረት መንፈጋቸው ግን የሚያስወቅሳቸው ስለሆነ በአፋጣኝ አንዳች መፍትሔን ማበጀት ይኖርባቸዋል።

👉የመለያዎች ህትመት ጥራት

በሀገራችን የእግርኳስ ክለቦች ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ ክለቦቹን በሚገልፅ መልኮ የተነደፉ ማሊያዎችን መጠቀም እየጀመሩ ይገኛል። በመለያዎች ጥራት ረገድ ጥሩ መሻሻሎችን ቢታዩም አሁንም ግን የሚቀሩ ብዙ ሥራዎች ስለመኖራቸው እያስተዋልን እንገኛለን ለማሳያነትም በዚህ የጨዋታ ሳምንት ትዝብታችንን ለማስቀመጥ ወደናል።

ከመለያ ቀለም ለውጥ ጋር በተያያዘ በሊጉ ጅማሮ የተለያየ ሀሳብን ሲያስተናግዱ የቆዩት ድሬዳዋ ከተማዎች ሊጉ ከተጀመረ ከጥቂት ጨዋታዎች ወዲህ የክለቡ የቀድሞ ተጫዋች የሆነው ፉአድ ኢብራሂም አሰርቶ ያበረከተላቸውን ብርትኳናማ መለያን በመጀመሪያ ተመራጭ መለያነት እየተጠቀሙ ይገኛሉ።

በንድፍ ረገድ የብዙዎችን አድናቆት ያገኘው አዲሱ የድሬዳዋ ከተማ መለያ ላይ የታተመው የክለቡ መለያ (ሎጎ) ግን ከጨዋታ ጨዋታ እየደበዘዘ አሁን ላይ ከነጭርሱ እየጠፋ ይገኛል። ይህም አርማው መለያው ላይ በታተመበት መንገድ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኖ አግኝተዋል።

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ቡናዎች በቅርቡ ከዚህ ቀደም ይጠቀሙበት የነበረውን መለያ ላይ በተወሰኑ መልኩ ማሻሻያዎችን አድርገው በተሻሻለው መለያ መጠቀም ጀምረዋል። ከዚህ ቀደም የነበረው መለያ በጣሊያኑ የትጥቅ አምራች ይቀርብ የነበረ ሲሆን የአሁን መለያ ግን ከሀ እስከ ፐ በተሰኘ የሀገር ውስጥ ኩባንያ የተዘጋጀ ነው።

የሀገር ውስጥ የትጥቅ አምራች ኩባንያዎች መሰል ሥራዎችን በኃላፊነት ተረክበው መስራት በመጀመራቸው መበረታት እንደሚገባቸው ብናምንም አሁንም ድረስ በሀገር በቀል ኩባንያዎች ላይ የሚነሳው ተቀዳሚው ጥያቄ የሚጠቀሙት የጨርቅ እና የህትመት ጥራት ጉዳይ አሁንም በአዲሱ የኢትዮጵያ ቡና መለያ ላይ በተወሰነ መልኩ እንመለከታለን።

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ቡና ባካሄዳቸው የሩጫ ውድድሮች ላይ መለያዎችን በማቅረብ ልምድ ያለው ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ለተጫዋቾች ሆነ ለደጋፊዎች እያቀረበው የሚገኘው መለያ ላይ በተለይ የጨርቁ ጥራት ግን ትኩረት የሚሻ ነው ከወዲሁ የተሸበሸቡ እና የተጨማደዱ መለያዎችን ለመመልከት ችለናል።

በተያያዘ ሲዳማ ቡና በውድድሩ አጋማሽ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ማዘዋወሩ ይታወቃል። ታድያ እነዚሁ ተጫዋቾች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ሲያደርጉ የተወሰኑት አዳዲስ ተጫዋቾች የለበሷቸው መለያዎች ላይ ቁጥራቸው እና ስማቸው የተፃፈበት መንገድ እና ቀለም የተለያየ መሆኑን አስተውለናል። በተጨማሪም ዮናስ ገረመው እና ያሬድ ከበደ የተጠቀሙባቸው መለያዎች ጀርባ ላይ በጉልህ ተለጥፎ የተሸፈነ ፅሁፍ መኖሩን ተመልክተናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ