ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

የሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽ በ14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ተጀምሯል። በጨዋታ ሳምንቱ የተከሰቱ ክለብ ተኮር ጉዳዮችንም እንደሚከተለው አሰናድተናል።

👉 ዐፄዎቹ ወሳኙን ጨዋታ በድል ተወጥተዋል

በጨዋታ ሳምንቱ እጅግ ተጠባቂ በነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ ያለ ግብ አቻ ለመጠናቀቅ ቢቃረብም መደበኛው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተሰጠው ተጨማሪ ደቂቃ ላይ ፋሲል ከነማዎች ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት አምበላቸው ያሬድ ባየ በተረጋጋ ሁኔታ አስቆጥሮ ቡድኑ በሰንጠረዡ አናት ልዩነቱን አስጠብቆ መሪነቱን ማስቀጠል ችሏል።

ተመጣጣኝ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የሚያስቆጩ የግብ አጋጣሚዎችን በተሻለ መልኩ መፍጠር ችለዋል። በዚህም በሁለት አጋጣሚዎች አዲስ ግደይ እና አማኑኤል ገ/ሚካኤል ያደረጓቸው ሙከራዎች በግቡ ቋሚ ሊመክኑባቸው ችለዋል።

ነገር ግን ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር የተሳነውን ሙጂብ ቃሲምን በፍቃዱ ዓለሙ የተኩት አሰልጣኝ ሥዩም ቅያሬያቸው በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ፍሬ አፍርቶ በጭማሪ ደቂቃ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አስቻለው ታመነ ተቀይሮ በገባው ፍቃዱ ዓለሙ ላይ በሰራው ጥፋት በተገኘው የፍፁም ቅጣት ምት የጨዋታው ውጤት ሊቀየር ችሏል።

ይህ ድል በቀጥተኛ ተፎካካሪያቸው ላይ የተገኘ መሆኑ በነጥብ እንዲርቁ ከማስቻሉ በተጨማሪ በቀሪው የውድድር ዘመን ከሚጠብቃቸው ፈታኝ ጨዋታዎች አንዱን በአዎንታዊ ውጤት እንዲወጡ ብሎም በስነልቦናው ረገድ የሚሰጣቸው ጥንካሬ ቀላል አይሆንም።

ፋሲል ከነማ ቀጣይ ፈተናው በአምስት ነጥብ አንሶ ከሚከተለው ኢትዮጵያ ቡና ጋር በመጪው ቅዳሜ የሚያደርገው ጨዋታ ሲሆን መሸናነፍ በሊጉ የቻምፒዮንነት ፉክክር ላይ ከሚያመጣው ለውጥ አንፃር የዓመቱ እጅግ ወሳኝ ፍልሚያ እንደሆነ ከወዲሁ መናገር ይቻላል ።

👉 ወላይታ ድቻ ማስገረሙን ቀጥሏል

ቀስ በቀስ ከወራጅ ቀጠና እየራቁ የመጡት ወላይታ ድቻዎች በዚህኛው ሳምንት ደግሞ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕናን በመርታት ከሰንጠረዡ አጋማሽ ተደላድለው ለመቀመጥ በቅተዋል።

ሁለት ለጥንቃቄ ቅድሚያ የሚሰጡ አሰልጣኞች የሚመሩ ቡድኖችን ያገናኘው ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱ ቡድኖች በኩል የመከላከል ጥንካሬያቸው በስፋት የታየ ነበር። በሁለቱም ቡድኖች በኩል ለማጥቃት የነበራቸው ፍላጎት ግን እጅግ ደካማ ሆኖ ተስተውሏል።

ከዕረፍት መልስም የቡድኖቹ እንቅስቃሴዎች በሁለቱ ሳጥኖች መካከል ተገድቦ ከሙከራዎች ርቀው የቆዩ ሲሆን ወላይታ ድቻዎች በሰሞንኛው የቆመ ኳስ አጠቃቀም ጠንካራ ጎናቸው መነሻነት በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ሁለት ጎሎችን በማከታተል አስቆጥረዋል። እነዚህ የፀጋዬ ብርሀኑ እና ቸርነት ጉግሳ ጎሎችም በሀዲያ ሆሳዕና ላይ በአንድ ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቆጠሩ ሁለት ጎሎች ሆነው ድቻን ለድል አብቅተውታል።

በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው መሪነት እስካሁን ሽንፈት ያላስተናገዱት ድቻዎች ካለፉት አምስት ጨዋታዎች አራት አሸንፈው አንድ አቻ በመለያየት ከፋሲል ከነማ ጋር በጋራ በጥሩ አቋም የሚገኝ ቡድን መሆን የቻሉ ሲሆን ወደ ሰንጠረዡ አናት ከሚገኙት ቡድኖች ተርታ ለመሰለፍ በሚያደርጉት ጥረት በሊጉ ግርጌ የሚገኘውን አዳማ ከተማን በ15ኛው የጨዋታ ሳምንት የሚገጥሙ ይሆናል።

👉 እያንሰራራ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር

በአዲሱ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም እየተመሩ ሦስተኛ ጨዋታቸውን ያደረጉት ጅማ አባ ጅፋሮች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ድላቸውን በሊጉ ግርጌ የሚገኘው አዳማ ከተማ ላይ ማስመዝገብ ችለዋል።

አዳማ ከተማዎች ከራሳቸው የሜዳ አጋማሽ ብዙም ባልዘለለው የሜዳ ክፍል ኳስን እንዲቆጠጠሩ የፈቀዱት ጅማዎች ይህን ሒደት በማቋረጥ ወደ ግብ ለመሄድ ያደረጉት ጥረት እምብዛም ውጤታማ አልነበረም።

በ29ኛው ደቂቃ ሳዲቅ ሴቾ ቀለል ባለ አጨራረስ መሪነቱን የተረከቡት ጅማዎች በሁለተኛው አጋማሽ 52ኛው ደቂቃ ላይ እዮብ ማቲዎስ ባስቆጠረባቸው ግብ አንድ አቻ ለመሆን ተገደው ነበር። ይባስ ብሎ በሁለተኛው አጋማሽ በአዳማዎች ከፍ ያለ ብልጫ የተወሰደባቸው ቢሆንም በ85ኛው ደቂቃ ሳይጠበቁ አዲሱ ፈራሚያቸው አማኑኤል ተሾመ ከቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ ተጠቅሞ ንጋቱ ገብረሥላሴ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ቡድኑን እጅግ ወሳኝ ድል እንዲያሳካ አስችሏል።

ተስፋ አስቆራጭ በሚባል የውጤት ቁልቁለት ውስጥ የነበረው ጅማ አባ ጅፋር በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም እየተመራ ቀስ በቀስ ነጥቡን እያሻሻለ የሚገኝ ሲሆን ቀጥተኛ የወራጅ ቀጠና ተፎካካሪው አዳማ ከተማን ማሸነፉን ተከትሎ ነጥቡን አስር በማድረስ ከወራጅ ቀጠና የመውጣት ተስፋውን አለምልሟል።

አባ ጅፋሮች በቀጣዩ ቅዳሜ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች የተሸነፉትን ወልቂጤ ከተማዎች የሚገጥሙ ይሆናል።

👉 ኢትዮጵያ ቡና የተፈተነበት ጨዋታ

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በድህረ ጨዋታ አስተያየታቸውን እንዳመኑት ኢትዮጵያ ቡና ከወልቂጤ ከተማ ብርቱ ፈተና ገጥሞትም ቢሆን አስፈላጊዋን ሦስት ነጥብ ይዞ መውጣት ችለዋል።

ከቀናት በፊት መሪው ፋሲል ከነማ ሌላኛውን የዋንጫ ተፎካካሪውን ቅዱስ ጊዮርጊስን መርታቱን ተከትሎ ከመሪው ጋር ያለውን ልዩነት አስጠብቆ ለመቀጠል ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ማሳካት የግድ ይላቸው የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ምስጋና ለአቡበከር ናስር ይግባና ወልቂጤን 2-1 በመርታት ልዩነታቸውን አስጠብቀው መቀጠል ችለዋል።

በጨዋታው ኢትዮጵያ ቡናዎች የቀኝ መስመር ተከላካያቸውን ኃይሌ ገብረተንሳይ እና የመሀል ተከላካያቸውን ምንተስኖት ከበደን በጉዳት ከማጣታቸው በስተቀር በተቸገሩበት ጨዋታ በአስገራሚው አጥቂያቸው ሁለት ግቦች ታግዘው ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው መውጣታቸው ለደጋፊዎቻቸው እጅግ አስደሳች የጨዋታ ቀን ነበር።

ቡድኑ እንደ ወላይታ ድቻ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ሀዋሳ ከተማ ካሉ ቡድኖች ጋር ባደረገው ጨዋታ ተጋጣሚዎቹ ይዘውት የገቡትን በጥብቅ መከላከል አቀራረብ ለመስበር ተቸግሮ ነጥቦች እንደጣለ ከዚህ ቀደም የተስተዋለ ሲሆን በአንፃራዊነት ክፍት ጨዋታ ከሚተግብሩ እና ከራሳቸው የጨዋታ ዘይቤ ጋር ከሚቀራረቡ ቡድኖች ጋር ባደረጓቸው ጨዋታዎች የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ መርታት ችለዋል። በዚህ ሳምንት ደግሞ በተመሳሳይ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ጥረት ከሚያደርገው ወልቂጤ ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ በተለይ በመጀመርያው አጋማሽ በሙከራም ሆነ በእንቅስቃሴ ረገድ ቢፈተኑም የአቡበከር ጎሎች ወሳኟን ሦስት ነጥብ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።

በቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት ቅዳሜ ላይ መሪውን ፋሲል ከነማን ከተከታዩ ኢትዮጵያ ቡና የሚያገናኘው ጨዋታ ከወዲሁ ውጤቱ በሰንጠረዡ ላይ ከሚኖረው ትርጉም አንፃር በጉጉት እየተጠበቀ ይገኛል።

👉ጥረታቸውን በውጤት ማጀብ የተሳናቸው ሠራተኞቹ

በሊጉ በመጨረሻ ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ሦስት ሽንፈት ያስተናገዱት ወልቂጤ ከተማዎች ከውጤት መግለጫው ባሻገር ሜዳ ላይ በሦስቱም ጨዋታዎች ላይ ያሳዩት እንቅስቃሴ ከአመርቂም በላይ ነበር። ነገር ግን በቀኑ መጨረሻ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ሳይሆን ወሳኙ መመዘኛ ውጤት ነውና ቡድኑ አስከፊ የውጤቱ ጉዞ ላይ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ቡና 2-1 በተሸነፉበት በ14ኛው የጨዋታ ሳምንት እንኳን ቡድኑ በሁለቱ መስመሮች እንዲሁም መሀል ለመሀል መነሻቸውን ባደረጉ የማጥቃት ሒደቶች እጅግ ተደጋጋሚ የማግባት አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችልም ከወገብ በላይ በሚገኙ ተጫዋቾቹ ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ግብ ማስቆጠር ሳይችል ቀርቷል።

በተመሳሳይ በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ ክብረወሰን ካላቸው ክለቦች ተርታ ይመደብ የነበረው ቡድኑ ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች ግን ግለሰባዊ ስህተቶች መበራከታቸውን ተከትሎ ቡድኑ በቀላሉ ግቦችን እያስተናገደ ይገኛል።

በጥቅሉ ባለፉት ሦስት ዘጠና ደቂቃዎች ወልቂጤ ከግማሽ በሚበልጡት የጨዋታ ክፍለ ጊዜዎች ከተጋጣሚያቸው ተሽለው መንቀሳቀስ ቢችሉም በተወሰኑ የጨዋታ ቅፅበቶች ቡድኑ ከጨዋታው ቅኝት ሲወጣ በሚያስተናግዳቸው ግቦች የጨዋታ ዕለት ሙሉ ጥረቱን አሳልፎ በመስጠት ላይ ይገኛል።

👉ባህር ዳር ከተማ በመቀመጫ ከተማው ወደ ድል ተመልሷል

ላለፉት አራት ጨዋታዎች ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ተቸግሮ የነበረው ባህር ዳር ከተማ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ሲዳማ ቡናን ከመመራት ተነስቶ 2-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል።

በመጀመሪያው አጋማሽ በፍፁም ቅጣት ምት እየተመሩ ወደ መልበሻ ቤት ያመሩት ባህር ዳር ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ባስቆጠሯቸው ግቦች ሲዳማ ቡናን ሲያሸንፉ ፍፁም ዓለሙ እና ወሰኑ ዓሊ የግቦቹ ባለቤቶች ነበሩ።

በተከታታይ ነጥብ መጣላቸው እና በሜዳቸው ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ በደካማ እንቅስቃሴ ነጥብ በመጋራታቸው ጫናዎች በርትቶባቸው የነበሩት ባህር ዳር ከተማዎች በዚህኛው ጨዋታ መሉ ሦስት ነጥብ ለማሳካት በተሻለ ተነሳሽነት መጫወት የቻሉ ሲሆን በተለይ ሁለተኛው ጎል ሲቆጠር የነበራቸው የደስታ አገላለፅ ውጤቱ ከነበረባቸው ጫና ለመላቀቅ ምን ያህል አስፈላጊያቸው እንደነበር ማሳያ ነበር።

እንደእዚህኛው ሳምንት ሁሉ ባህር ዳር ከተማዎች በቀጣዩም ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር ላይ ሀዲያ ሆሳዕናን የሚገጥሙ ይሆናል። ይህ ጨዋታ የሦስት ነጥብ ተበላልጠው አራተኛ እና አምስተኛ ላይ የተቀመጡትን ቡድኖች የሚያገናኝ ከመሆኑ አንፃር ወሳኝ መርሐ ግብር ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ