“የተሰጠንን ታክቲክ በአግባቡ በመተግበራችን አሸንፈን ወጥተናል” እንየው ካሣሁን

ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያደረገውን ጨዋታ በድል በመወጣት የነጥብ ልዩነቱን አስፍቷል። በቀኝ መስመር ተከላካይነት ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው እንየው ካሣሁንም በውጤቱ እና ሌሎች ጉዳዮች ዙርያ ቆይታ አድርጓል።

በዛሬው ዕለት በብዙ እግርኳሳዊ መለኪያ ተጠባቂ የነበረው የረፋዱ የፋሲል ከነማ እና የኢትዮጵያ ቡናን ጨዋታ ዐፄዎቹ በሙጂብ ቃሲም ብቸኛ ጎል በማሸነፍ ወደ ዋንጫው የሚያደርጉትን ግስጋሴ አጠናክረው ቀጥለዋል። ባለፈው ዓመት ቡድኑን ተቀላቅሎ ጥሩ ጊዜን ከቡድኑ ጋር እያሳለፈ የሚገኘው የቀኝ መስመር ተከላካዩ እንየው ካሣሁን ከዛሬው ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ስለ ዛሬው ጨዋታ እና በቀጣይ ስለሚያስበው ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

” የዛሬው ጨዋታ ውጥረት ነበረው። ቡናዎች ቢያሸንፉ ኖር ከኛ ጋር የነበራቸው የነጥብ ልዩነት ይጠብ ነበር። ለኛም በጣም አስፈላጊና ትልቅ ነጥብ ነበር። ለዋንጫ የሚደረግ ፉክክር እንደመሆኑ ጥሩ ፉክክር ነበር የታየበት። እኛም የተሰጠንን ታክቲካክ በአግባቡ በመተግበራችን አሸንፈን ወጥተናል። የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፋችን ወደ ዋንጫ ለምናደርገው ጉዞ በጣም በጣም የሚጠቅም ነው። ምክንያቱም ተከታያችንን በስምንት ነጥብ ነው የራቅነው። ዛሬ ብንሸነፍ ኖሮ ይጠብ የነበረ መሆኑ ማሸነፋችን ወሳኝ ነው።

” መጀመርያ አካባቢ ተጠባባቂ ነበርኩ። አሁን ወደ መጀመርያ አሰላለፍ በመግባት ቡድኑን እያገለገልኩ ነው። አሁን በምፈልገው ጥሩ አቋም ላይ ነው ያለሁት። አሰልጣኞቹ የሚሰጡኝ ሚና የበለጠ ጥሩ እንድጫወት ረድቶኛል። ጥሩ የውድድር ዓመት፤ የተሻለም ጊዜ እያሳለፍኩ ነው።

” በብሔራዊ ቡድን ምርጫ ዙርያ ወጣት ቡድን ተጫውቻለሁ፤ ዋናው ቡድን ነው መጫወት ያልቻልኩት። የአሰልጣኙን ሀሳብ አከብራለው። ባስፈለግኩኝ ሰዓት እጠራለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። እኔም ሀገሬን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ።

” ፋሲል ዘንድሮ እቅዱ አንድና አንድ ያለ ምንም ጥርጥር ዋንጫውን ማንሳት ነው። በቡድናችን ላይ ያለው መንፈስ ሁሌም ጥሩ ነው። የቀሩትን ሁሉንም ጨዋታዎች የማሸነፍ ስነልቦና ነው ያለን። ዋንጫ ማንሳት እና ማንሳት ብቻ ነው አላማችን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ