በፋሲል ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ዙርያ የዲሲፕሊን ውሳኔ ተላልፏል

በውዝግብ ታጅቦ በተጠናቀቀው የፋሲል ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ላይ የታዩ የዲሲፕሊን ግድፈቶችን የመረመረው የአወዳዳሪው አካል ውሳኔዎች አሳልፏል።

ከአራት ቀናት በፊት የተደረገው የ14ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተጠባቂ ጨዋታ ፋሲል ከነማን ከቅዱስ ጊዮርጊስ አገናኝቶ ነበር። ጨዋታውንም የሊጉ መሪዎች ፋሲል ከነማዎች ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በጭማሪው ደቂቃ ባስቆጠሩት የፍፁም ቅጣት ምት አሸናፊ ሆነዋል። በጊዜውም “የተሰጠብን የፍፁም ቅጣት ምት አግባብነት የለውም” በሚል ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች እና በክለቡ ውስጥ በተለያዩ ሀላፊነት የሚሰሩ ግለሰቦች በሊጉ አወዳዳሪ አካል ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

በዚህም የአወዳዳሪው አካል ውድድሩ አንደተጠናቀቀ የቅዱስ ጊዮርጊስን ማሊያ የለበሱ ደጋፊዎች የእለቱን ዋና ዳኛ በቃላት የማይገለፅ እጅግ ፀያፍ ስድብ በተደጋጋሚ ከመሳደብ አልፈው ምራቃቸውን መትፋታቸውን በእለቱ ዋና ዳኛና የጨዋታ ታዛቢ ሪፖርት ቀርቦባቸዋል ብሏል። ከዚህም በተጨማሪ የተወሰኑ በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ የተለያዩ የስራ ድርሻ ያላቸው ግለሰቦች ዳኞችንና የውድድር መሪዎችን ከመሳደብ አልፈው ከአወዳዳሪ አካላት ጋር ለድብድብ ሲጋብዙና ፀብ የሚያነሳሳ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ እነደነበር በውድድር አመራሮች ሪፖርት ተደርጓል ብሏል። በዚህም መነሻነት የውድድር አመራርና ስነስርዓት ኮሚቴ በክለቡ ላይ የሚከተሉትን የቅጣት ውሳኔዎች ማስተላለፉ ታውቋል።

1.የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የሚያደርጋቸውን ቀጣይ 3 /ሶስት/ ጨዋታዎች ካለደጋፊ እንዲያካሂድ፤

2.በፋሲል ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ላይ በደጋፊነት ተመዝግበው ውድድሩን እንዲመለከቱ የተፈቀደላችው 10/አስር/ ደጋፊዎች በዚህ የውድድር ዘመን ሁሉንም ጨዋታዎች ወደ ስታድየም በመግባት እንዳይመለከቱ ታግደዋል፤

3.በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ዉስጥ የተለያዩ የስራ ድርሻ ያላቸው ሰራተኞች አቶ ካሳሁን ደርበው /የሚድያ ባለሞያ/ እና አቶ ተስፋዬ ምንዳዬ /የሰው ሃብት አስተዳደር/ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ በሚያደርጋቸው ቀጣይ ተከታታይ የ5 ሳምንት ውድድሮች ላይ ወደ ስታድየም በመግባት ጨዋታዎችን
እንዳይመለከቱ ታግደዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ