ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የመሳይ ተመስገን ግሩም ጎል ለሀዋሳ ሦስት ነጥብ አስገኝታለች

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የአስራ አራተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን አራተኛ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ በመሳይ ተመስገን አስገራሚ የቅጣት ምት ጎል ጌዲኦ ዲላን 1-0 አሸንፏል፡፡

ከረፋዱ ጨዋታ በመቀጠል የቀኑ ሁለተኛ መርሐ-ግብር በሀዋሳ ከተማ እና ጌዲኦ ዲላ መካከል 10፡00 ሲል ተጀምሯል፡፡ አስቀድሞ የተጠበቀውን ያህል ቡድኖቹ በሜዳ ላይ እንቅሴቃሴያቸው እጅጉን ጠንካራ ፉክክርን ያሳያሉ የሚል ዕምነት የነበረ ቢሆንም ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ እስከ ፍፃሜው ሰዓት ድረስ ግን የታየው ተቃራኒው ነበር፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ በተወሰነ ረገድ ሀዋሳ ከተማዎች ተሽለው የታዩ ሲሆን ጌዲኦ ዲላዎች ለኋላ መስመራቸው በይበልጥ ሽፋን ሰጥተው ከዛም በሚገኙ ውስን ዕድሎች ወደ ፊት ለመሄድ ጥረት ማድረግ የቻሉበት ነበር፡፡ረጃጅም ኳሶችን እየተመለከትን በነበረው ጨዋታ 10ኛው ደቂቃ ላይ እጅጉን ግሩም ግብ ተመልክተናል፡፡ በግራ የጌዲኦ ዲላ የግብ ክልል አካባቢ ወደ መስመር ባደላ ቦታ በግምት ከ25 ሜትር ርቀት ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት መሳይ ተመስገን አክርራ በመምታት ከመረብ አሳርፋ ሀዋሳን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡

ጌዲዮ ዲላዎች ጎል ከተቆጠረባቸው በኃላ በመስመር አጨዋወት ወደ ጎል ለመጓዝ ጥረት ሲያደርጉ የነበረ ቢሆንም ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ለመድረስ የነበራቸው አካሄድ ደካማ በመሆኑ አቻ ለመሆን አልታደሉም፡፡በአንፃሩ በተሻለ ፈጣን የሽግግር የጨዋታ መንገድ ወደ አጥቂዎቹ ረድኤት እና መሳይ በመጣል ሀዋሳዎች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ሞክረዋል፡፡ መሳይ ተመስገን ከቅጣት ምት ሞክራ መስከረም መንግሥቱ የመለሰችባት እና ጨዋታው ሊጋመስ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው ረድኤት አስረሳኸኝ ያለቀለትን አጋጣሚ በሚያስቆጭ ሁኔታ የሳተችበት መንገድ ሀዋሳዎች ያደረጓቸው ሌሎች ጉልህ ሙከራዎች ናቸው፡፡

ጌዲኦ ዲላዎች ፍፁም መሻሻሎችን ባሳዩበት ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ጊዜ በርካታ ዕድሎችን ለመጠቀም ባላቸውን ኃይል ለመጠቀም የታተሩበት ሲሆን በአንፃሩ ከሰባ አምስተኛው ደቂቃ በኋላ ሀዋሳ ከተማዎች የኋላ መስመራቸውን በመድፈን ያስቆጠሩትን አንድ ጎል ለማስጠበቅ እጅጉን ጠንካራ ፍልሚያ አድርገዋል፡፡ አምበሏ ሥመኝ ምህረት 59ኛው ደቂቃ በግብ ክልል ውስጥ ከቡድን ጓደኞቿ ያገኘችውን ኳስ በቀጥታ መትታ የሀዋሳ ግብ ጠባቂ ገነት ኤርሚያስ አውጥታባታለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጌዲኦ ዲላዎች በመንደሪን ክንድይሁን የቅጣት ምት ሙከራን በሁለት አጋጣሚ አድርገዋል፡፡ በተለይ 71ኛው ደቂቃ መንደሪን ከመሀል ሜዳ ክፍሉ በተወሰነ መልኩ ወደ ጎን ዘንበል ባለ ቦታ የተገኘን ቅጣት ምት መትታ ቅድስት ዘለቀ በግንባር ከጎሉ ጠርዝ ያወጣችባት አጋጣሚ የምትጠቀስ ጠንካራ ሙከራ ነበረች፡፡

በአመዛኙ ጌዲኦ ዲላዎች ብልጫን ወስደው የነበረ ቢሆንም ሀዋሳ ከተማዎች ጥቅጥቅ ባለ መከላከል ወሳኝ ሦስት ነጥብን ይዘው ወጥተዋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሀዋሳ ቅድስት ዘለቀ የጨዋታው ምርጥ ተብላ ተመርጣለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ