ሪፖርት | ሰበታ ከተማ በድል የባህር ዳር ቆይታውን አጠናቋል

የአስራ አምስተኛ ሳምንት የሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ በሰበታ እና ሀዋሳ መካከል ተካሂዶ ሰበታ በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩ ጎሎች 2-1 በማሸነፍ የባህር ዳር ቆይታውን ያለ ሽንፈት አጠናቋል።

ሰበታ ከተማ ከድሬዳዋ አቻ ከተለያየው ስብስብ ሁለት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም ዳንኤል ኃይሉ እና ያሬድ ሀሰንን በአብዱልሀፊዝ ቶፊቅ እና ቃልኪዳን ተተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ያለፈው ሳምንት አራፊ የነበሩት ሀዋሳዎች በበኩላቸው ከአንደኛ ዙር የመጨረሻ ጨዋታቸው ሦስት ተጫዋቾችን በመለወጥ ፀጋአብ ዮሐንስ፣ ጋብርኤል አህመድ እና ወንድምአገኝ ኃይሉ በዘነበ ከድር፣ አለልኝ አዘነ እና ዮሐንስ ሰጌቦ ተክተዋል።

ከትናንት በስቲያ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት ኢንስትራክተር አንተነህ እሸቴ የህሊና ፀሎት በማድረግ በተጀመረው ጨዋታ የተጠበቀው የቡድኖቹ የጨዋታ አቀራረብ በመጀመርያው አጋማሽ የተስተዋለ ሲሆን ሰበታዎች እንደተለመደው ኳስ በመቆጣጠር የበላይነቱን ሲይዙ ሀዋሳዎች ኳሱን ለተጋጣሚ በመተው በሚፈጠሩ ክፍተቶች እድል ለመፍጠር ጥረዋል።
ጥቂት የግብ ዕድሎች በተፈጠሩበት በዚህ አጋማሽ በ7ኛው ደቂቃ ለጎል የቀረበ ሙከራ አድርገዋል። ከግራ መስመር ዮሐንስ ሰገቦ ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ ብሩክ በየነ ተንጠራርቶ ቢሞክረውም ምንተስኖት አሎ በጥሩ ቅልጥፍና ጎል ወደ ውጪ አውጥቶበታል።

በሰበታ ከተማ በኩል በተደጋጋሚ ወደ ሀዋሳ የጎል ክልል መድረስ ችለው የነበረ ቢሆንም ወደ ጠንካራ ሙከራነት የተቀየሩት ግን ከሁለትጀመብለጥ አልቻሉም። በዘጠነኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን የተላከው ኳስ በተከላካዮች ሲመለስ ከሳጥኑ ጠርዝ ያገኘው መስዑድ ወደ ጎል ሞክሮ ሜንሳህ አድኖበታል። በ28ኛው ደቂቃም በተመሳሳይ ከግራ መስመር የተነሳውን ኳስ ቡልቻ ሹራ ሞክሮ በተከላካይ ተጨርፎ አቅጣጫ ቢቀይርም ግብ ጠባቂው ከጎልነት አድኖታል።

ሁለተኛው አጋማሽ በጎልም ሆነ እንቅስቃሴ ረገድ ከመጀመርያው በእጅጉ የተለየ ነበር። ገና አጋማሹ እንደተጀመረ ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ያመሩት ሀዋሳዎች ከጥሩ ቅብብል በኋላ ኃይለሚካኤል አደፍርስ ያሻገረውን ፍፁም ገብረማርያም በጥሩ አጨራረስ ሰበታን ቀዳሚ አድርጓል።

ከጎሉ በኋላ ሀዋሳዎች አቻ ለመሆን ከማዕዘን ምት ለማስቆጠር ጥሩ የሚባል አጋጣሚ አግኝተው መስፍን ሳይጠቀምበት ሲቀር ለተጨማሪ ጎል ጥረታቸውን የቀጠሉት ሰበታዎች ዛሬ ተዳክሞ የታየው ምኞት ደበበን ስህተቶች በመጠቀም ሁለት ተከታታይ እድል አግኝተዋል። የመጀመርያውን ፍፁም መትቶ ሜንሳህ በቀላሉ ሲይዝበት ሁለተኛውን በ55ኛው ደቂቃ ቃልኪዳን በጥሩ ሁኔታ አመቻችቶለት መስዑድ መሐመድ ወደ ግብነት በመለወጥ መሪነቱን ማስፋት ችሏል።

በተከታታይ ለተቆጠሩባቸው ጎሎች ምላሽ በፍጥነት ለመስጠት ጥረት ያደረጉት ሙሉጌታ ምህረት የተጫዋች እና አደራደር ለውጥ በማድረግ ጫና መፍጠር የቻለሉ ሲሆን ብዙም ሳይቆዩ በ61ኛው ደቂቃ ላውረንስ ላርቴ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ መስፍን ታፈሰ በግንባሩ ገጭቶ ሀዋሳን ወደ ጨዋታው የመለሰች ጎል ማስቆጠር ችሏል።

በጎሉ ይበልጥ የተነሳሱት ሀዋሳዎች ተደጋጋሚ የጎል አጋጣሚዎች ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ የሰበታ የኋላ ክፍል በተለይ ጨዋታው ለውሀ እረፍት እስኪቋረጥ ድረስ መረጋጋት ተስኖት ታይቷል። አለልኝ አዘነ ከጎሉ አንድ ደቂቃ በኋላ ይህንኑ አለመረጋጋት ተጠቅሞ የመታው ኳስ ለጥቂት ሲወጣበት ከቅጣት ምትም ኢላማውን ያልጠበቀ ጥሩ ሙከራ አድርጓል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃ ሲቀረው አቻ ለመሆን ጥረታቸውን ቀጥለው በ88ኛው ደቂቃ ወርቃማ ዕድል ቢያገኙም ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ከጎሉ ፊት በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ብሩክ በየነ ወደ ላይ ሰዷታል። በጭማሪው ደቂቃም በተመሳሳይ ከመስመር የተሻማውን ኳስ መስፍን በግንባር ገጭቶ ቢያስቆጥርም ኳሱን ለማግኘት ግብ ጠባቂው ምንተስኖት ላይ ጥፋት ሰርቷል በሚል በአጨቃጫቂ ሁኔታ ተሽሮ ጨዋታው በሰበታ አሸናፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ