ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ኤሌክትሪክ ከአቃቂ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የአስራ አራተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ አቃቂ ቃሊቲ 1ለ1 ተለያይተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በፊት በመደረጉ ሰላሳ ደቂቃን ዘግይቶ ነበር ሊጀመር የቻለው፡፡ ብዙም ሳቢ ባልነበረው እና ብልጭ ብሎ ከሚጠፉ ወጥነት ካልነበራቸው አጋጣሚዎች ውጪ ጨዋታው የተለየ ነገርን አስመልክቶናል ብሎ መናገር ከባድ ነው፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ በተወሰነ መልኩ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በግራ አቅጣጫ ባደላ የአጨዋወት መንገድ ለመጫወት የጣሩበት ሲሆን ተጋጣሚው አቃቂ በአንፃሩ ኳስን በመቀባበል በሚገኙ ጥቂት ዕድሎች ለማጥቃት ታትረዋል፡፡

በኮሪደር በኩል ወደ አጥቂ ክፍላቸው በማሻገር ግብ ለማስቆጠር የሞከሩት ኤሌክትሪኮች ገና በጊዜ ነበር አሸናፊ ያደረጋቸውን ጎል ያገኙት፡፡ በግራ አቅጣጫ በጥሩ የኳስ ፍሰት ወደ አቃቂ ግብ ክልል 10ኛው ደቂቃ ላይ መድረስ የቻሉት የአሰልጣኝ መሠረት ማኔ ልጆች በመጨረሻም ዮርዳኖስ ምዑዝ የግል ጥረቷን ተጠቅማ ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረችው ሣራ ነብሶ ሰጥታት አጥቂዋ ወደ ጎልነት በቀላሉ ለውጣው ክለቧን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡

ኤሌኬትሪኮች ጎል ካስቆጠሩ በኃላ ተጨማሪ ማስቆጠር የሚችሉበትን ዕድል አግኝተው ነበር፡፡ሣራ ነብሶ ከርቀት ሞክራ ግብ ጠባቂዋ ስርጉት የመለሰችባት እና 33ኛው ደቂቃ ላይ ራሷ ሣራ ከመሀል ሜዳ ከግብ ክልል ትይዩ የተገኘን ኳስ በቀጥታ መታ የግቡ ቋሚ ብረት የመለሰባት ሌላው ተጠቃሽ ሙከራ ነበረነች፡፡

ኳስን ሲይዙ እግራቸው ላይ ከሚያደርጉት ቅብብል አንፃር ማራኪ ሆኖ ይታይባቸው የነበሩት አቃቂዎች አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች ቁጥብ ሆነው መሀል ሜዳው ላይ ተገድበው ውለዋል፡፡ ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመሩ አራት ደቂቃ ሲቀራቸው ከመስመር የተሻገረን ኳስ ዮርዳኖስ በርኸ በግንባር የመታቻት እና ግብ ጠባቂዋ ትዕግስት አበራ ያዳነችባት በአጋማሹ አቃቂዎች ያገኟት የጠራችዋ ሙከራ ነች፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ አቃቂዎች በሚገባ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ከመጀመሪያው አጋማሽ ስህተቶቻቸው ተሻሽለው ሲገቡ በአንፃሩ ኤሌክትሪኮች ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ጥቃት ለመሰንዘር ቢዳዱም ስኬማታ ሊሆን ግን አልቻለም፡፡ 59ኛው ደቂቃ ላይ የኤሌክትሪክ የተከላካይ መስመር በሰሩት የመናበብ ስህተት አስናቀች ትቤሶ በረጅሙ ስታሳልፍ በአቃቂ በኩል ጥሩ የሜዳ ላይ ቆይታ የነበራት ቤዛዊት ንጉሤ በድንቅ አጨራረስ ጎል አስቆጥራ ክለቧን አቻ አድርጋለች፡፡

በቀሩት ደቂቃዎች ሁለቱም ክለቦች አሸናፊ ለመሆን ጥረት ማድረግ ቢችሉም ብዙም ይህ ነው የሚባል ሙከራን ሳያስመለክተን 1ለ1 በሆነ ውጤት ተደምድሟል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ቤዛዊት ንጉሤ የጨዋታው ምርጥ ተብላ ተሸልማለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ