በ15ኛ ሳምንት የመጀመርያ ቀን ውሎ የከሰዓት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተገናኝተው ያለ ጎል ተለያይተዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በፋሲል ከነማ ከተሸነፉበት ስብስብ አቤል ያለውን በሮቢን ንግላንዴ በመተካት ወደ ሜዳ ሲገቡ ድሬዎች በበኩላቸው ከሰበታ ከተማ ጋር አቻ ከተለያዩበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ዘነበ ከበደን በቅርቡ በፈረመው ዐወት ገብረሚካኤል ተክተው ለጨዋታው ቀርበዋል።
ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት ኢንስትራክተር አንተነህ እሸቴ እና የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች መሐመድ አህመድ የህሊና ፀሎት በማድረግ የተጀመረው ጨዋታ የመጀመርያ አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ በኳስ ቁጥጥር፣ ድሬዳዋ ደግሞ በርካታ የጎል ዕድል በመፍጠር ተሽለው ታይተዋል።
ከቅዱስ ጊዮርጊሶች ቅብብል የሚያቋርጧቸውን ኳሶች በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የጎል ክልል ሲደርሱ የነበሩት ድሬዎች እንደፈፀሟቸዝ ጥቃቶች በዚህ አጋማሽ ጎል ሳያስቆጥሩ መውጣታቸው የሚያስቆጫቸው ነበር። በዘጠነኛው ደቂቃ ደስታ ደሙ ሸፍኖ ኳሱን ወደ ውጪ ለማስወጣት ጥረት ቢያደርግም ሙኅዲን ታግሎ ኳሱን በማስቀረቱ የፈጠረውን አደጋ አስቻለው በግሩም ሸርተቴ ያወጣበት እድል የመጀመርያው ጥሩ አጋጣሚ የነበረ ሲሆን ኬሙይኔ ወደ ሳጥን የጣለው ኳስ ሙህዲን ከመድረሱ በፊት ባህሩ ነጋሽ ቀደሞ በመውጣት ያዳነውም የሚጠቀስ ነበር። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሲል ደግሞ አስቻለው ከግራ የሳጥኑ ክፍል ያገኘውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ወደ ጎል የመታውን ኳስ ባህሩ በግሩም ሁኔታ ጨርፎት አግዳሚውን ለትሞ ወጥቷል።
በዚህ አጋማሽ ኳስ ከማንሸራሸር ባለፈ የሚጠቀስ የጎል ዕድል መፍጠር ያልቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አማኑኤል ከግራ መስመር መትቶ ፍሬው በቀላሉ ከያዘበት ሙከራ ውጪ ምንም መፍጠር ሳይችሉ ወደ እረፍት አምርተዋል።
እንደ መጀመርያው አጋማሽ በቀጠለው የሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጊዮርጊሶች የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ለማሻሻል ቢጥሩም አሁንም ሙከራዎች በማድረግ የተሻሉ የነበሩት ኳሱን ለተጋጣሚ በመተው በመልሶ ማጥቃት ወደፊት ሲሄዱ የነበሩት ድሬዳዋዎች ነበሩ።
በ55ኛው ደቂቃ ናንጄቦ ከቀኝ መስመር እየገፋ ወደ ሳጥን በመግባት የመታው ኳስ አቅጣጫ ቢቀይርም ባህሩ በእግሩ ያወጣበት እና አስቻለው ግርማ ከመጀመርያው አጋማሽ ጋር በሚመሳሰል መልኩ የጎሉ አግዳሚ የገጨበት ሙከራዎች በድሬ በኩል መሪ ለመሆን በእጅጉ የተቃረቡባቸው ነበሩ።
የጨዋታው ደቂቃ በገፋ ቁጥር ድሬዎች ወደ ጎላቸው ተጠግተው መጫወትን የመረጡ ሲሆን ለፈረሰኞቹ ተጫዋቾች የጎል እድል የመፍጠርያ ክፍተት በመንፈግ ረገድ ተሳክቶላቸው ውለዋል። በዚህም በ68ኛው ደቂቃ ናትናኤል፣ አዲስ እና ጌታነህ ተቀባብለው በመጨረሻ ናትናኤል መትቶ ኢላማውን ካልጠበቀው ሙከራ ውጪ ተጨማሪ አደጋ ሳይፈጠርባቸው ቀርቷል።
በጭማሪ ደቂቃ ላይ ድሬዎች ሦስት ነጥቦች ይዘው ሊወጡባቸው የሚችሉ እድሎችን በሚያስቆጭ መልኩ አምክነዋል። አስቻለው ከርቀት አክርሮ የመታውን ዛሬ ጥሩ የተንቀሳቀሰው ባህሩ ነጋሽ ሲይዝበት ከአንድ ደቂቃ በኋላ በድጋሚ አስቻለው ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል የመታውን ኳስ አስቻለው ታመነ ተደርቦ አውጥቶበት ጨዋታው ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ