መሐመድ አህመድ “ቱርክ” ማን ነው?

ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች መሐመድ አህመድን ህይወትን የተመለከተ አጭር መሰናዶ እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ወንጂ ካፈራቻቸው ስመጥር ተጫዋቾች አንዱ የሆነው መሐመድ ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ለእግርኳስ ካለው ፍቅር የተነሳ ከታዳጊነቱ ጀምሮ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫውቷል። በ1961 የቅዱስ ጊዮርጊስ ወሳኝ ተጫዋቾች ሸዋንግዛው አጎናፍር እና ፍስሀ ወልደአማኑኤል ለትምህርት ወደ አሜሪካ ሲያቀኑ እነርሱን በመተካት ነበር ፈረሰኞችን ማገልገል የጀመረው። ከአስር ዓመት በላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ማገልገል መቻሉንም ታሪክ ያስረዳል።

ሰባት ቁጥር ለባሽ እና የመስመር አጥቂ እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ታሪካዊ ተጫዋች በርካታ ስኬቶችን ከቡድኑ ጋር ማሳካት ችሏል። ከሁሉም በላይ በጥይት በተመታበት ማግስት ዳኘው ከተሰኘ ክለብ ላይ በነበረ ጨዋታ ላይ ተሰልፎ ተጫውቶ ሁለት ጎሎችን እንዳስቆጠረ ይነገራል።

መሐመድ በአንድ ወቅት ከመንግሥቱ ወርቁ ጋር በመልክ ከመመሳሰሉ ጋር ተያይዞ መንግሥቱ ያገኙ መስሏቸው እርሱን በጥይት እግሩ መተውታል። እግሩ ውስጥ የገባችውን ጥይት ሳያስወጣም ለሰባት ዓመት መጫወቱ የተለየ ተጫዋች ሲያደርገው እስከ ህይወት ፍፃሜውም ድረስ እግሩ ውስጥ የገባችው ጥይት እንዳልወጣ ይነገራል።

“ቱርክ” በሚል ቅፅል ስሙ ይበልጥ የሚታወቀው መሐመድ በአብሮ አደጉ ተስፋዬ ጥላሁን አማካኝነት ስያሜው እንደወጣለት ይነገራል። የወቅቱ የቡድኑ አሰልጣኝ የነበሩት ጋሽ ይድነቃቸው ተሰማ መሐመድ ለልምምድ ማርፈዱን አስተውለው “ምን ሆኖ ነው ያረፈደው?” ብለው ሲጠይቁ እንደ አጋጣሚ የቱርክ ፕሬዝዳንት አዲስ አበባ መጥተው የነበረ በመሆኑ ተሰፋዬ ጥላሁን የሀገሩን መሪ ሊቀበል ሄዷል በማለት በተናገረው “ቱርክ” የሚለው ቅፅል ስም በዛው እንደቀረ ታሪኩ ያስረዳል።

በኢህአፓ ዘመን ሦስት አብሮ አደግ ጓደኞቹ የተገደሉበት መሐመድ “እኔም የዚህ እጣ ቀማሽ እንዳልሆን” በማለት ከሀገሩ በመውጣት በሳውዲ አረብያ ረጅም ዓመት በስደት ኖሮ በቅርብ ዓመታት ወደ ሀገሩ በመመለስ ኑሮውን በሀገሩ አድርጎ ቆይቷል።

የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ (ኮሜርስ) ምሩቁ በቤተሰብ ህይወቱ ባለትዳር እና የልጆች አባት ሲሆን በርከት ያሉ የልጅ ልጆች አይቷል። በገጠመው የጤና እክል ህክምና ሲከታተል ቆይቶ በትናንትናው ዕለት ሌሊት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። የቀብር ስነስርዓቱም በዛሬው ዕለት ወዳጅ ዘመድ በተገኘበት ኮልፌ በሚገኘው የሙስሊም የመቃብር ስፍራ በክብር ተፈፅሟል።


© ሶከር ኢትዮጵያ