U-20 | አዳማ፣ መድን እና ወልቂጤ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የምድብ ለ ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ተደርገው አዳማ ከተማ፣ ኢትዮጵያ መድን እንዲሁም ወልቂጤ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን በተመሳሳይ 2ለ1 አሸንፈዋል፡፡

2፡00 ላይ ምድቡን ከፊት ሆነው እየመሩ የሚገኙት ሀዲያ ሆሳዕና እና አዳማ ከተማን ያገናኘ ነበር፡፡ ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር ከድንቅ የጨዋታ እንቅስቃሴ ጋር መመልከት የቻልንበት ሲሆን በተለይ አዳማ ከተማዎች የበላይነት ነበራቸው፡፡ ኳስን መሠረት ባደረገ የመሐል ሜዳ እንቅስቃሴያቸው በማራኪ ቅብብል ወደ ልማደኛው አጥቂ ቢኒያም አይተን በማሻገር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል፡፡ በአንፃሩ ረጃጅም ኳሶችን ከተለያዩ የሜዳ አቅጣጫዎች ወደ ግብ ክልል በመላክ ሀድያ ሆሳዕናዎች ጎልን ለማስቆጠር የወሰዱት አማራጭ የጨዋታ መንገድ ነበር፡፡

12ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ የኳስ ቅብብል ከቀኝ መስመር የመጣችን ኳስ ሊጉን በግብ አስቆጣሪነት የሚመራው ቢኒያም አይተን አስቆጥሮ አዳማን መሪ አድርጓል፡፡ ጎል ሊቆጠርባቸው ግድ የሆነው ሀድያ ሆሳዕና ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት የሰመረው ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ ነበር፡፡ የአዳማ ከተማ ተከላካዮች የሰሩትን የሳጥን ውስጥ ስህተት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ደስታ ዋሚሾ በቀላሉ አስቆጥሮ ክለቡን 1ለ1 አድርጓል፡፡

አዳማ ከተማዎች ከአቻነት ጎሉ በኋላ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሰንዝረዋል፡፡ በተለይ 38ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ አማካዩ በላይ ጌታቸው አክርሮ መቶ ግብ ጠባቂ የመለሰበት ሙከራ አስቆጪ ነበር፡፡ ሀድያዎች በበኩላቸው መደበኛው ደቂቃ ሊጠናቀቅ ጥቂት እንደቀሩት በደስታ ዋሚሾ አማካኝነት ያለቀለትን ዕድል አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ አዳማ ከተማዎች ኳሱን በሚገባ ተቆጣጥረው በቅብብል ወደ ፊት በመሄድ የተሳካ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የተስተዋሉ ሲሆን በአንፃሩ ሀድያ ሆሳዕናዎች እንደ ቀዳሚው አጋማሽ ሁሉ ረጃጅም የሚሻገሩ ኳሶች ላይ ትኩረታቸው አድርገው ታይተዋል፡፡ ቢኒያም አይተን ከግራ በኩል የመጣለትን ኳስ አግኝቶ ወደ ጎል ከመታ እና የግቡ ቋሚ ከመለሰበት ሁለት ደቂቃ እንደተቆጠረ 60ኛው ደቂቃ ላይ ያማረ የቅብብል ፍሰትን ሲያሳዩን የነበሩን አዳማ ከተማዎች በአላሚን ከድር ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር አሸናፊ ሆነዋል፡፡

ከሰዓት 8፡00 የቀኑ ሁለተኛ መርሀ ግብር በኢትዮጵያ መድን እና ሀላባ ከተማ መሀል የተደረገ ነበር፡፡ መድኖች ብልጫን ወስደው በታዩበት የመጀመሪያው አጋማሽ በመልሶ ማጥቃት የበላይ መሆን የቻሉበት ሲሆን በአንፃሩ ኳስን ለመያዝ ሀላባዎች ሙከራ ቢያደርጉም የመጨረሻ የአጥቂ ክፍላቸው የውሳኔ አሰጣጥ ደካማ መሆኑ የኃላ ኃላ ዋጋ ያስከፈላቸው ሆኗል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ 10ኛው ደቂቃ ፀጋ ከድር የመድንን ተከላካዮች ስህተት ተጠቅሞ በመልሶ ማጥቃት ከቀኝ በኩል ያገኘውን ኳስ ወደ ግብነት ለውጦ ሀላባዎች ቀዳሚ አድርጎ ነበር፡፡ ይሁንና የመከላከል አደረጃጀታቸው ደካማ የነበረው የሀላባ የተከላካይ ክፍል 34ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ተቆጥሮበት ወደ አቻ ውጤት ተሸጋግረዋል፡፡ ያሬድ ካሳዬ ለመድን የግል ጥረቱን በሚገባ ያሳየ ጎል አስቆጥሮ ቡድኑን ወደ ጨዋታ መልሷል፡፡

አሁንም ጥቃት በመሰንዘሩ የተዋጣላቸው የነበሩት መድኖች ሁለተኛ ግባቸውን 38ኛው ደቂቃ ላይ አግኝተዋል፡፡ ከመስመር አሸብር ደረጄ ነፃ አቋቋም ለነበረው አሸናፊ ተስፋዬ ሰጥቶት አጥቂው ያገኛትን ኳስ በአግባቡ በመጠቀም ክለቡን ከተመሪነት ወደ መሪነት አሻግሯል፡፡

ሁለቱ ክለቦች ከመልበሻ ክፍል ሲመለሱ ሀላባ ከተማዎች መጀመሪያ ላይ የታየባቸውን ክፍተት በሚገባ ደፍነው ቀርበዋል፡፡ በአንፃሩ በተወሰነ ረገድ ከቀዳሚው አጋማሽ መድኖች ቀዝቀዝ ያሉ መስለው ቢታዩም ረጃጅም ተሻጋሪ ኳሶቻቸው በቁመት ለማይታሙት አጥቂዎቻቸው ምቾትን የፈጠሩ ሆነው ታይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በኳስ ቁጥጥር እና በሙከራ ረገድ ሀላባ ከተማዎች ፍፁም የበላይ ሆነው ቢቆዩም የኢትዮጵያ መድኑ ግብ ጠባቂ ማጆ ቾኦ ጥሩ ሆኖ መቅረቡ ሀላባን ዕድለኛ እንዳይሆን ዳርጎታል፡፡

በተደጋጋሚ ሀላባ ያገኙትን አጋጣሚ ወደ ጎልነት እንዳይለውጡ ከግብ ክልሉ ጭምር በመውጣት ሲያመክናቸው ያስተዋልን መሆኑ መድኖችን ለውጤታማነት ያበቃ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ጨዋታውም በዚህኛው አጋማሽ ጎል ሳያስመለክተን 2ለ1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡

የዕለቱ ሦስተኛ እና የመጨረሻ የአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታ በወልቂጤ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ መካከል የተከናወነ ነበር፡፡ ተመጣጣኝ ፉክክርን ባየንበት እና እጅግ አስገራሚ እንቅስቃሴዎችን ማስተዋል የቻልንበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ያስመለከተን ባይሆን ብርቱ ፉክክርን አሳይቶናል፡፡

ከእረፍት መልስ ጎሎችን የተመለከትንበት ነበር፡፡ 71ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው መሐመድ ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ጎል አስቆጥሮ ክለቡን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ነገር ግን በመስመር አጨዋወት አደገኛ የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች በዮሴፍ አሰፋ እና ተቀይሮ በገባው መጂድ ዲጋ በጭማሪ ደቂቃ ግሩም ጎሎች አከታትሎ በማስቆጠር ጨዋታውን 2ለ1 አሸንፈው ወጥተዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ