በ15ኛው ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እጅግ ተጠባቂ በነበረው ፍልሚያ ፋሲል ከነማ ከአራት ጨዋታ በኋላ ከግብ የታረቀው ሙጂብ ቃሲም ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ኢትዮጵያ ቡና ላይ ወሳኝ ድል አስመዝግቧል።
አሠልጣኝ ካሳዬ አራጌ ወልቂጤ ከተማን ተቸግሮም ቢሆን ከረታው ስብስብ ውስጥ ሦስት ለውጦችን ሲያደርጉ በዚህም ኃይሌ ገብረትንሳይ ፣ ምንተስኖት ከበደ እና እያሱ ታምሩን አስወጥተው በምትካቸው አስራት ቱንጆ ፣ ወንድሜነህ ደረጄ እና ዊሊያም ሰለሞን ተክተዋል። በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሚመሩት ፋሲል ከነማዎች ከቀናት በፊት ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲያሸንፉ የተጠቀሙበትም ስብስብ ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ጨዋታውን አድርገዋል።
ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በእስካሁኑ የሊግ ጉዞ 19 ግቦችን በማስቆጠር ሊጉን በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየመራ ለሚገኘው አቡበከር ናስር በጫማ እና ኳስ ቅርፅ የተሰራ ዋንጫ በአሰልጣኝ ካሳዬ እና የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ተበርክቶለታል።
ጨዋታው ገና ከጅምሩ ፋሲል ከነማዎች ኢትዮጵያ ቡና ኳስን እንዳይመሰርት በሜዳው የላይኛው ክፍል ከፍ ያለ ጫናን በማሳደር ሲጀምሩ በዚህም በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት ሦስት ግማሽ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር።
የጨዋታው የመጀመሪያም ሙከራ በ4ኛው ደቂቃ በፋሲል በኩል የተገኘ ነበር። ከሳጥኑ በቅርብ ርቀት ወደ ግራ ካደላ አቋቋም ያገኙትን ቅጣት ምት ሱራፌል ዳኛቸው በቀጥታ ሲመታ የግቡ አግዳሚን ለትማ ወደ ውጭ ወጥታበታለች።
የጨዋታው ደቂቃዎች እየገፉ ሲሄዱ ፋሲሎች በተወሰነ መልኩ ወደ ቡና ሳጥን ገፍተው ጫና ከመፍጠር መቆጠባቸው አማራጭ የኳስ ምስረታ መንገድ ለመጠቀም የማይደፍሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በተወሰነ መልኩ ወደ ጨዋታው እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ የሚገቡበትን ዕድል የፈጠረ ይመስላል። ለወትሮም ሂደቱ እንከን የማያጣው የኢትዮጵያ ቡና ምስረታ በሚፈለገው ስኬት ባይሆንም ኳሶች የመጀመር ዕድልን በተወሰነ መልኩ ቢያገኙም መሀል ሜዳ ላይ በቀላሉ የቁጥር ብልጫ እየተወሰደባቸው ሲቋረጡ ተመልክተናል።
ፋሲል ከነማዎች የበላይ በነበሩት የመጀመሪያ አጋማሽ በ12ኛው ደቂቃ በረከት ደስታ ከራሱ ሜዳ አጋማሽ የተላከለትን ሰንጣቂ ኳስ ተጠቅሞ ወደ ቡና ሳጥን ደርሶ የሞከረው እና አቤል ማሞ በቀላሉ ያዳነበት እንዲሁም ራሱ በረከት ሽመክት ጉግሳ ከቀኝ መስመር ያሻገረለት ኳስ እንደመጣ የሞከረውና ለጥቂት በቋሚው ያለፈበት ኳስ አስቆጭ ሙከራዎች ነበሩ።
ነገር ግን በ22ኛው ደቂቃ የፋሲሎች ጥረት ፍሬ አፍርቷል። አቤል ማሞ በኢትዮጵያ ቡና ኳስ ምስረታ ላይ በጫና ውስጥ ለቡድን አጋሮቹ ለማቀበል የሞከረው ተንጠልጣይ ኳስ በሽመክት ጉግሳ ከተቋረጠች በኋላ ሙጂብ ከሱራፌል የደረሰውን ኳስ ቀለል ባለአጨራረስ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ይህችም ግብ ሙጂብን ለ360 የጨዋታ ደቂቃዎች ከዘለቀውን የግብ ድርቅ ያላቀቀች ነበረች።
ከግቧ መቆጠር በኋላም በነበረው የጨዋታ ሂደት ፋሲሎች የተሻሉ ነበሩ። በተመሳሳይ በጨዋታው ዕድለኛ ያልነበረው በረከት ደስታ በ29ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ የመታው ኳስ አቤል ማሞ ሲያድንበት ኢትዮጵያ ቡና ይህ ነው የሚባል የግብ አጋጣሚ ለመፍጠር ተቸግሮ ታይቷል። በ34ኛው ደቂቃ የኢትዮጵያ ቡና የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ሚናን የሚወጣው ታፈሰ ሰለሞን በጉዳት በፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል።
ከዕረፍት መልስ አስደናቂ የመጀመሪያ አጋማሽ ያሳለፉት ፋሲል ከነማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ጫና ለመፍጠር ይሞክሩበት የነበረውን መንገድ ማስቀጠል ተስኗቸው ሲስተዋሉ ኢትዮጵያ ቡናዎች ግን ከመጀመሪያው አንፃር የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉበት አጋማሽ ነበር።
ኢትዮጵያ ቡና በሜዳው የመጀመሪያ 80 ሜትር ከመጀመሪያው በተሻለ ኳሶችን ማሳደግ ቢችሉም በመጨረሻው 20 ሜትር ግን የነበራቸው ደካማ ውሳኔ አሰጣጥ የተሻሉ በነበሩበት አጋማሽ እንኳን አንድ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። ቡናዎች ተፅዕኖ ፈጣሪ አጥቂያቸው አቡበከር ናስር ምንም ማድረግ ባልቻለበት ጨዋታ ብልጫ ቢወስድባቸው እንኳ ፋሲል ከነማዎች ሦስት ጥሩ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።
በ51ኛው ደቂቃ ከድር ኩሊባሊ በረጅሙ ከተከላካዮች ጀርባ የጣጣለትን ኳስ ሱራፌል ዳኛቸው በጣም ተረጋግቶ የሞከረውና አቤል ማሞ በሚገርም መልኩ ያዳነበት ኳስ እንዲሁም በ78ኛው ደቂቃ በሬድዋን ናስር ስህተት የተገኘውን ኳስ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ናትናኤል ወ/ጊዮርጊስ ከተመሳሳይ ስፍራ ሞክሮ አግዳሚ ከመለሰበት ሙከራ ውጪ በ83ኛው ደቂቃ አምሳሉ ጥላሁን ከቅጣት ምት ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችሏል።
ጨዋታው በፋሲል ከነማ 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ፋሲል ከነማዎች ነጥባቸውን ወደ 35 በማሳደግ ከተከታያቸው ኢትዮጵያ ቡና በስምንት ነጥብ ልቀው ሊጉን መምራታቸውን ቀጥለዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ