​ሪፖርት | ወልቂጤ ከሦስት ሽንፈት በኋላ ወደ ድል ተመልሷል

በውጤት እጦት የሰነበቱት ሠራተኞቹ  ጅማ አባ ጅፋርን ከኋላ ተነስተው 2-1 ማሸነፍ ችለዋል።

ጅማ አባ ጅፋር አዳማን ከረታበት ጨዋታ የአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ላይ የሚገኘው ወንድምአገኝ ማርቆስን በአዲሱ ፈራሚ ሥዩም ተስፋዬ ሲተካ ወልቂጤ ከተማ ደግሞ በኢትዮጵያ ቡና 2-1 ከተረታው ቡድን ውስጥ አሜ መሐመድን በአህመድ ሁሴን ለውጧል።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ ቢሆኑም ከተከላካይ መስመር ጀርባ የመግባት ምልክትን ያሳዩት ጅማ አባ ጅፋሮች 4ኛው ደቂቃ ላይ ቀንቷቸዋል። ከማዕዘን ምት የተነሳ እና በተከላካዮች የተመለሰውን ኳስ ኤልያስ አታሮ አመቻችቶለት ከተከላካዮች እይታ ውጪ የነበረው ተመስገን ደረሰ ግብ አስቆጥሯል። ተጫዋቹ በቀድሞው ክለቡ ላይ በማግባቱ ደስታውን ከመግለፅም ተቆጥቧል። የኋላ ክፍላቸው መዘናጋት ዛሬም በቀላሉ ግብ እንዲያስተናግዱ ያስገደዳቸው ወልቂጤዎች ቀሪዎቹን ደቂቃዎች በሙሉ አቻ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ አሳልፈዋል። ሆኖም ሙከራዎቻቸው በአብዱልከሪም ኑሪ ብቃት እና በግቡ አግዳሚ ከውጣት ርቀው ቆይተዋል።

ከወልቂጤ የግብ አጋጣሚዎች ውስጥ 7ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ወርቁ ከማዕዘን አሻምቶት ቶማስ ስምረቱ በግንባር ሞክሮ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ቀዳሚ ሲሆን 21ኛው ደቂቃ ላይም ረመዳን የሱፍ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ሄኖክ አየለ ከቅርብ ርቀት ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል። ከዚህ ውጪ በግብ ጠባቂው የዳኑት የአብዱልከሪም ወርቁ ፣ ሀብታሙ ሸዋለም እና ያሬድ ታደሰ የርቀት ሙከራዎች ተጠቃሽ ሲሆኑ ወደ ዕረፍት ከማምረታቸው በፊትም የበኃይሉ ተሻገር ቅጣት ምት በአቡበከር ኑሪ እና በአግዳሚው ትብብር የዳነ ነበር።

እንደመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ሁሉ ዛሬም ግብ ለማግኘት ዕድለኛ ያልሆኑት ወልቂጤዎች አብዛኛውን ጊዜያቸውን በጅማ ሜዳ ላይ ቢያሳልፉም ለሌላ ከባድ መልሶ ማጥቃት የተጋለጡበት አጋጣሚ አልነበረም። ከዕረፍት በፊት አቻ ላለመሆን በጥንቃቄ የተከላከሉት ጅማዎች በቶሎ ወልቂጤ ሜዳ ላይ በመድረሱ ቢቀዛቀዙም እየመሩ ለማረፍ ግን ችለዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ በሙከራዎች የታጀበ እና ድንቅ እንቅስቃሴ የታየበት ሆኖ ጀምሯል። በጅማ በኩል 54ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥሮ ከጨዋታ ውጪ የተባለበት ሱራፌል ዐወል ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ ሊመለስበት ችሏል። ሆኖም በድንገት ከባድ ብልጫ የተወሰደበት ወልቂጤ ከተማ በቀጣይ ደቂቃዎች ከግብ ጋር ታርቋል። 63ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተነሳውን ኳስ ቶማስ ስምረቱ በመቀስ ምት ሞክሮ አቡበከር አድኖበት አጠገቡ የነበረው ተቀይሮ የገባው አሜ መሀመድ ወልቂጤን አቻ አድርጓል። ቶማስ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ከማዕዘን ምት በግንባሩ ሞክሮም አቡበከር አድኖበታል። ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ግብ ጠባቂው ለዚህ ማዕዘን ምት ምክንያት የነበረውን የአብዱልከሪም ወርቁን ጠንካራ ሙከራም ማውጣት ችሎ ነበር።

የተወሰደባቸውን ብልጫ ቀልብሰው ተደጋጋሚ ሙከራዎች እና ግብ ያስመዘገቡት ወልቂጤዎች 70ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ችለዋል። የአብዱልከሪም ወርቁን የቀኝ መስመር ተሻጋሪ ኳስ አህመድ ሁሴን መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል። የዓመቱን የመጀመሪያ ጎል ያስቆጠረው ቁመተ መለሎው አጥቂ በእንባ ታጅቦ ደስታውን ገልጿል። 78ኛው ደቂቃ ላይም ከአህመድ በተነሳ ኳስ አሜ መሀመድ ሌላ ግብ ለማከል ቢቃረብም አቡበከር አውጥቶበታል። ጅማ አባ ጅፋሮች በተለይም ከቆሙ ኳሶች መነሻነት ሙከራዎችን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም ጥረታቸው ሳይሰምር ለሽንፈት ተዳርገዋል።

በውጤቱ ወልቂጤ ከተማ ነጥቡን 19 አድርሶ ወደ ስድስተኛ ደረጃ ከፍ ሲል ጅማ አባ ጅፋር በነበረበት የ12ኛ ደረጃ ላይ ቀርቷል።

ያጋሩ