​የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 1-2 ወልቂጤ ከተማ

ከከሰዓቱ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከአሰልጣኞች ጋር ያረገው ቆይታ ይህንን ይመስላል።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ጅማ አባ ጅፋር

ስለጨዋታው

የዛሬው ጨዋታ ለሁለታችንም ወሳኝ ነበር። ዞሮ ዞሮ መጀመሪያ የመምራቱን ዕድል አግኝተን ነበር። ከዛ በኋላ እነሱ ባልተረጋጉበት ወቅት ላይ መድገም የምንችልባቸው ብዙ ዕድሎች ነበሩ ፤ ያን መጠቀም አልቻልንም። በሁለተኛው አጋማሽ በእነሱ በኩል ቀይረው ያስገቧቸው ፈጣን የመስመር ተጨዋቾቻቸው ውጤት ቀያሪ ሆነዋል። በአንፃሩ በእኛ በኩል የስብስብ ጥራት እና ጥበት ስላለ ትንሽ ተቸግረናል። የተጎዱ ተጨዋቾችን ነው ወደ ሜዳ ያስገባነው። ዞሮ ዞሮ የመጀመሪያ አጋማሽ እኛ የተሻልን ነበርን ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ደግሞ እነሱ የተሻሉ ነበሩ። ጥሩ ፉክክር ታይቶበታል ብዬ አስባለሁ።

ስለአቡበከር ኑሪ ጥሩ ውሎ

አቡበከር እንግዲህ ወጣት ልጅ ነው። ለጅማ አባ ጅፋር ብቻ ሳይሆን ለብሔራዊ ቡድን እና ለውጪ ዕድል የሚደርስ ግብ ጠባቂ ነው። በጣም ጥቃቅን ስህተቶች ካልሆነ በቀር በዚህ ውስን ልምዱ እያሳየ ያለው ብቃት በጣም ጥሩ ነው። በእግር ሲጫወት ጥሩ ነው ፣ የዓየር ላይ ኳስ የማዳን ብቃቱ ጥሩ ነው ፣ ከተከላካዩ ጋር ለመጫወት የሚሞክረው ነገርም ጥሩ ነው ። ለወደፊቱ ለብሔራዉ ቡድን ጥሩ ተተኪ ተጨዋች ነው ብዬ አስባለሁ።

ስለቀጣይ ጨዋታ

ቀጣይ ጨዋታችን ከፋሲል ጋር ነው።  ፋሲል ሊጉን እየመራ ነው ያለው። ዞሮ ዞሮ እኛ ለማንኛውም ቡድን የራሳችንን ዝግጅት ነው የምናደርገው። ከፋሲል ጋርም አሸንፈን ሦስት ነጥብ ይዘን ለመውጣት እንዘጋጃለን።

አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ወልቂጤ ከተማ

ስለጨዋታው

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ነው ግብ ያስተናገድነው። ከነበረብን ጫና አንፃር ልጆቻችን ላይ ቶሎ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የተቸገርንበት ሁኔታ ነው የነበረው። ሆኖም ግን ልጆቹ ያንን ጫና ተቋቁመው ወደ ራሳችን አጨዋወት መምጣት ችለው ነበር። ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች በማዳኑ የእነሱን ግብ ጠባቂ ሳላደንቅ አላልፍም ፤ ጥሩ ጥሩ ኳሶች ነው ያወጣው። ከመጀመሪያው አጋማሽ ጎል ይዘን አለመውጣታችን ይበልጥ ጫና ውስጥ እንድንገባ አድርጎናል። ሆኖም ግን ልጆቹ ውጤቱን ቀልብሰው መውጣታቸው ምን ያህል የአዕምሮ ጥንካሬ እንደነበራቸው የሚያሳይ ነው። 

ስለ አሜ መሀመድ እና አህመድ ሀሴን ወደ ግብ አስቆጣሪነት መመለስ

ይህ እጅግ መልካም ነገር ነው ብለን እናስባለን። በእርግጥ ጎሎቹን ያገኘንበት መንገድ መጀመሪያ እንዳቀድነው እና ይዘነው እንደገባነው እንቅስቃሴ ባይሆንም አህመድ ወደ ጎል ማግባት መምጣቱ ለእርሱም ትልቅ መነሳሳት ይፈጥርለታል። እንደቡድንም ውጤት ይዘን እንድንወጣ የራሱ ድርሻ አበርክቷል። የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ይገባን ነበር ፤ አሸንፈናል።

ማስተዋሻነቱን በሞት ላጧቸው አያታቸው መታሰቢያ ያውሉ እንደሆን

እንደ ጥሩ መታሰቢያ የሚወሰድ ከሆነ ቢሆን ደስ ይለኛል።