​ቅድመ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ አዳማ ከተማ

የ15ኛው ሳምንት የመጨረሻ ቀን መክፈቻ ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን እንዲህ አንስተናል።

በሁለት የተለያየ መንፈስ ላይ የሚገኙት ወላይታ ድቻ እና አዳማ ከተማ ነገ ረፋድ ላይ ይገናኛሉ። ካለፉት አምስት ጨዋታዎች አራቱን በድል የተወጡት ወላይታ ድቻዎች የወራጅ ቀጠናውን ነገር እየረሱ ከመሀል ወደ ላይ ከፍ ለማለት ጥረት ላይ ናቸው። በተቃራኒው አራተኛ ተከታታይ ሽንፈት ላስተናገዱት አዳማዎች ደግሞ ጨዋታው ከሊጉ ግርጌ ለመላቀቅ በሚደረግ ጥረት ውስጥ የሚከወን ነው። 

ከአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ጋር ከፍ እያሉ የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች መረባቸውን ለሦስት ጨዋታዎች ሳያስደፍሩ ለነገው ፍልሚያ ደርሰዋል። በጠንካራ የመከላከል መሰረት ላይ ራሱን ያገኘው ቡድኑ ፊት ላይም በየጨዋታው ግብ የሚያስገኝለት አጥቂ ባይኔረውም በተለያዩ ተሰላፊዎቹ ግብ እያስቆጠረ ነጥቦችን መሰብሰቡን ቀጥሏል። ድቻ ለተጋጣሚዎቹ የአጨዋወት ባህሪ ምላሽ የሚሰጥ አቀራረብን ይዞ ወደ ሜዳ የሚገባበት መንገድም ያዋጣው ይመስላል። በነገው ጨዋታም ከውጤት አንፃር ራሱን ከጫና ማላቀቁ በማጥቃት ሀሳብ የተወጠነ የጨዋታ ዕቅድ ሊኖረው ቢችልም የተጋጣሙው የኳስ ቁጥጥር ላይ ያመዘነ አጨዋወት አደገኛ ወደ ሆነበት የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት እንዲያመዝን ሊያደርገው ይችላል። በደካማ ጎንነት የሚነሳበት ከክፍት ጨዋታ የግብ ዕድሎችን እያገኘ ያለመሆኑ ጉዳይም ከቆሙ ኳሶች መነሻነት በማስቆጠር ጥንካሬው እየተጠገነ መቀጠሉ ነገ ከደካማ የተከላካይ ክፍል ጋር እንደመገናኘቱ ዳግም ተጠቃሚ ሊያደርገው ይችላል።

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ እንደ አዲስ እያዋቀሩት ያሉት አዳማ ከተማ ከጅማ ጋር ያደረገው ጨዋታ ከዚህ በኋላ በምን መልኩ እንደሚጫወት ቢያመላክትም በጅማ ከመሸነፍ ግን አላተረፈውም። ካስፈረማቸው ተጨዋቾች ባህሪ አንፃርም በድኑ ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑ በእንቅስቃሴም ታይቷል። ከዚህ አንፃር በቅርብ ጨዋታዎች ጥሩ የመከላከል ቁጥር ያለው ወላይታ ድቻን በቅብብሎች ለመስበር አሁን ያለበት የቡድን ውህደት ደረጃ ፈተና ሊሆንበት እንደሚችል ይታሰባል። ከዚህ በተጨማሪም የተጨዋቾች አብሮ አለመቆየት የሚያመጣው ችግር የተንፀባረቀበት የኋላ ክፍሉ ለድቻ ለመልሶ መልሶ ማጥቃት የሚሰጠው ምላሽ የጨዋታውን ውጤት የመወሰን ዕድሉ የሰፋ ነው። ይያም ቢሆን ቡድኑ ነገም ከአዲስ ፈራሚዎቹ ውስጥ አብዛኞቹን ወደ ሜዳ ይዞ እንደሙገባ ይጠበቃል።

ወላይታ ድቻ አማካዩ በረከት ወልዴን አሁንም በቅጣት ምክንያት የሚያጣ ሲሆን አስናቀ ሞገስም በመጀመሪያው ጨዋታው ከገጠመው ጉዳት አላገገመም። ከአዲስ ፈራሚዎቹ መሀል ጋቶች ፓኖም ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆን የውጪ ዜግነት ያላቸው ፈራሚዎቹ የሥራ ፍቃድ ያላላቀ በመሆነ ነገ ግልጋሎታቸውን አያገኝም። በአዳማ በኩል የትዕግስቱ አበራ ጉዳት እና የደስታ ጌቻሞ ቅጣት ብቻ በስብስቡ ውስጥ ያለ ጉድለት መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ከዚህ ውጪ ደሳለኝ ደባሽ ከአምስት ቡጫ ካርድ ቅጣት መልስ ቡድኑን የሚያገለግል ይሆናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 11 ጊዜ ተገናኝተው እኩል አምስት አምስት ጊዜ ድል ቀንቷቸው በአንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ወላይታ ድች 13 አዳማ ከተማ ደግሞ 11 ጊዜ ኳስ እና መረብን ማገናኘት ችለዋል። 

ግምታዊ አሰላለፍ 

ወላይታ ድቻ (4-3-3)

መክብብ ደገፉ
 

አናጋው ባደግ –  አንተነህ ጉግሳ – ደጉ ደበበ – ያሬድ ዳዊት                

መሳይ አገኘሁ –  ጋቶች ፓኖም – እንድሪስ ሰዒድ 

 ፀጋዬ ብርሀኑ – ቢኒያም ፍቅሬ – ቸርነት ጉግሳ

አዳማ ከተማ (4-2-3-1)

ዳንኤል ተሾመ

ታፈሰ ሰርካ – አሚኑ ነስሩ – እዮብ ማቲዮስ – ጀሚል ያዕቆብ

ኤልያስ አህመድ – ደሳለኝ ደባሽ 

በላይ አባይነህ – ኤልያስ ማሞ – ያሬድ ብርሀኑ

አብዲሳ ጀማል