ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

ነገ 9 ሰዓት የሚደረገውን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ድል ካገኙ አምስት የጨዋታ ሳምንታት ያለፋቸው አዳማ ከተማዎች ካሉበት የወራጅ ቀጠና ለመውጣት እና የውድድር ዓመቱን ሦስተኛ ድል አግኝቶ ወደ አሸናፊነት ለመምጣት የነገውን ጨዋታ ይጠባበቃሉ። በተቃራኒው ሽንፈት ካስተናገዱ ሰባት ጨዋታዎች ያለፋቸው ባህር ዳር ከተማዎች የዓመቱ የመጀመሪያ ተከታታይ ድላቸውን ወደ ሦስት ለማሳደግ እና ከደረጃ ሠንጠረዡ አናት ላይ ካሉ ክለቦች ጋር ለመቀራረብ ድልን በማሰብ ለጨዋታው ይቀርባሉ።

በ15ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር በወላይታ ዲቻ አንድ ለምንም ተሸንፈው ለነገው ጨዋታ እየተዘጋጁ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች በአንፃራዊነት ከሌላው ጊዜ በተሻለ በድቻው ጨዋታ ለመንቀሳቀስ ሲሞክሩ ተስተውሏል። እርግጥ ቡድኑ አሁንም የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ችግር ቢኖርበትም በቅርቡ ስብስቡን የተቀላቀሉት ሁለቱ ኤልያሶች (ኤልያስ አህመድ እና ኤልያስ ማሞ) ለዚህ መፍትሄ ይዘው የመጡ ይመስላል። በተለይ ተጫዋቾቹ ባላቸው ጥሩ ቴክኒካዊ ብቃት ቡድኑ የግብ ማስቆጠሪያ አማራጮችን መሐል ለመሐል እንዲያገኝ ሲጥሩ ታይቷል። በድቻውም ጨዋታ ከእነርሱ የሚነሱ ኳሶች አደጋን የሚፈጥሩ ሲሆን ነበር። ከዚህ መነሻነት ነገም አዳማ ከተማ በተለይ ሁለቱ ኤሌያሶች ላይ የተንጠለጠለ የማጥቃት ሀሳብ ይዞ ወደ ሜዳ ሊገባ እንደሚችል ይገመታል።

በአማካይ በየጨዋታው 2.07 ጎል እያስተናገደ የመጣው የአዳማ የተከላካይ መስመር ከዚህ በኋላ በጥሩ እና አስተማማኝ ደረጃ ላይ መገኘት የግድ ይለዋል። በተለይ ቡድኑ በሊጉ መትረፍ ከፈለገ በየጨዋታው የሚያስተናግደውን የጎል ብዛት መቀነስ አለበት። በነገውም ጨዋታ ቡድኑ ፈጣኖቹን የባህርዳር የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች በአግባቡ የማይቆጣጠር ከሆነ የሚደርስበት አደጋ ከባድ ይሆናል።

በወላይታ ድቻው ጨዋታ የምላስ መንሸራተት አደጋ አጋጥሞት የነበረው ታሪክ ጌትነትን ጨምሮ የኋላሸት ፍቃዱ እና ትዕግስቱ አበራ በነገው ጨዋታ የማይኖሩ የአዳማ ተጫዋቾች ናቸው።

የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ተከታታይ ድል ሲዳማ እና ሀዲያ ላይ የተቀዳጁት ባህር ዳሮች በጥሩ የተነሳሽነት ስሜት ላይ ያሉ ይመስላሉ። ከምንም በላይ ደግሞ በሲዳማው ጨዋታ ከመመራት ተነስተው ማሸነፋቸው እንዲሁም በሀዲያው ጨዋታ በትዕግስት የተጋጣሚን የግብ ክልል ለማስከፈት የጣሩበት መንገድ በጥሩ የስነ-ልቦና ልዕልና እና የማሸነፍ ፍላጎት ላይ እንዳሉ ማሳያ ነው። እርግጥ በሀዲያው ጨዋታ ቡድኑ የማጥቂያ አማራጮቹ በርክተው ባይታይም ባላፉት ጨዋታዎች መቀዛቀዞችን ያሳየው የመስመር አጨዋወቱ በተሻለ አደገኛነቱ መቷል። በነገውም ጨዋታ ፍፁም ከሚሰነዝራቸው የመሐል መለሐል ጥቃቶች በተጨማሪ የመስመር ተከላካዮቹ እና አጥቂዎቹ የሚያደርጉት የመስመር ላይ ሩጫዎች ለቡድኑ በጎ ነገርን ይዞለት ብቅ ሊል ይችላል።

ባህር ዳር በአንፃራዊነት ከኳስ ጋር ጊዜ የሚያሳልፍ ቡድን ቢሆንም በመጨረሻው የማጥቂያ ሲሶ ላይ ያለው የኳስ ቅብብሎሽ ስኬት ግን በተደጋጋሚ የወረደ ሲሆን ተስተውሏል። በተጨማሪም ከወገብ በላይ ያሉት ተጫዋቾች የተጋጣሚ የመከላከል ወረዳ ላይ ሲደርሱ የውሳኔ አሳታጥ ችግር ይታይባቸዋል። ይህም ችግር በነገው ጨዋታ የማይቀረፍ ከሆነ ቡድኑ ግብ ለማስቆጠር የሚቸገር ይሆናል።

አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የጡንቻ ጉዳት ካስተናገደው አቤል ውዱ በስተቀር በነገው ጨዋታ የሚያጡት ተጫዋች የለም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን ከተገናኙባቸው ሦስት ጨዋታዎች ሁለቱ በባህር ዳር ከተማ አሸናፊነት ሲጠናቀቁ በአንዱ ያለግብ ተለያይተዋል። በግንኙነታቸው አዳማ ከተማ እስካሁን ግብ ያልቀናው ሲሆን ባህር ዳር ከተማ አምስት ግቦች አሉት።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-1-4-1)

ዳንኤል ተሾመ

ታፈሰ ሰርካ – አሚኑ ነስሩ – እዮብ ማቲዮስ – ጀሚል ያዕቆብ

ደሳለኝ ደባሽ

በላይ አባይነህ – ኤልያስማሞ – ኤልያስ አህመድ – ያሬድ ብርሀኑ

አብዲሳ ጀማል

ባህር ዳር ከተማ (4-2-3-1)

ሀሪሰን ሄሱ

ሚኪያስ ግርማ – ሰለሞን ወዴሳ – መናፍ ዐወል – አህመድ ረሺድ

ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ሳምሶን ጥላሁን

ወሰኑ ዓሊ – ፍፁም ዓለሙ – ግርማ ዲሳሳ

ባዬ ገዛኸኝ


© ሶከር ኢትዮጵያ