ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ምድብ ለ የመጀመሪያው ዙር ዛሬ ተጠናቋል

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የምድብ ለ የመጀመሪያው ዙር ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ተጠናቋል። መሪው አዳማ ከተማ በአዲስ አበባ ከተማ 3ለ1 ሲሸነፍ ሀላባ ከተማ ከወልቂጤ ከተማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና ከ ኢትዮጵያ መድን አቻ ተለያይተዋል፡፡

የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ የተያዘለት መደበኛ ሰዓት 3፡00 የነበረ ቢሆንም ሜዳው አስቀድሞ የተያዘለት ፕሮግራም ስለነበር እስኪጠናቀቅ ከሁለት ሰዓት ከሰላሳ በላይ ዘግይቶ ነበር የአዳማ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ መጀመር የቻለው። የሰበታ ከተማ ዋና አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ እና ረዳታቸው ይታገሱ እንዳለ በቀጣዩ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ለክለባቸው ተስፈኛ ተጫዋች ለማግኘት በማሰብ በስታዲየሙ ተገኝተው ይህን ጨዋታ ተከታትለውታል፡፡

አዲስ አበባዎች ከተሻጋሪ በሚነሱ ኳሶች ተጋጣሚ ላይ ገና ከጅምሩ ጫና ማሳደር ችለዋል፡፡ 2ኛው ደቂቃ በዚህ ሒደት የመጣለትን ኳስ በአግባቡ የተቆጣጠረው አቡበከር መሐመድ አስቆጠረ ሲባል በቀላሉ ስቷታል፡፡ ፈጣኑ አጥቂ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ምንተስኖት ዘካሪያስ በረጅሙ ያሳለፈለትን ኳስ አቡበከር መሀመድ ወደ ጎልነት ለውጧት የመዲናይቱን ተስፈኞች መሪ አድርጓል፡፡

ካለፉት ጨዋታዎቻቸው አንፃር በእንቅሴቃሴ እና በሙከራ ረገድ ቀዝቅዘው የታዩት አዳማ ከተማዎች ኳስን በመሀል ሜዳ ክፍሉ ላይ ተቆጣጥሮ በመጫወት ብልጫ ቢይዙም በመስመር አጨዋወታቸው እጅጉን የተዋጣላቸው አዲስ አበባ ከተማዎች የሚቀመሱ አልነበሩም፡፡

11ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ልክ እንደ መጀመሪያው ከመስመር የመጣለትን ኳስ አቡበከር መሐመድ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ለራሱ እና ለክለቡ የግብ መጠኑን ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል፡፡ ከሶስት ደቂቃዎች በኃላ በድጋሚ አቡበከር ግብ ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ ተብሎ ተሽሮበታል፡፡

በመስመር አጨዋወት በሁለቱም ኮሪደሮች በፈጣን ተጫዋቾቻቸው ታግዘው ከአዳማ በተሻለ ጎል ለማግኘት የጣሩት አዲስ አበባ ከተማዎች መደበኛው የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተሰጠ ጭማሪ ደቂቃ ላይ አቡበከር መሐመድ በራሱ ላይ በሳጥን ውስጥ ተጠልፎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ መቶ በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርቶ ወደ መልበሻ ክፍል በአዲስ አበባ 3ለ0 መሪነት አምርተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ አዳማ ከተማዎች የነበረባቸውን የአጨራረስ ድክመት ለመቅረፍ እንዲረዳቸው የተጫዋቾች ለውጥን አከታትለው አድርገዋል፡፡ ቅያሪያቸው ቡድኑ የጨዋታ ቅርፅ በተወሰነ መልኩ እንዲኖረው ያደረገ ቢመስልም የፊት አጥቂዎቻቸው ያገኙትን ዕድል የመጠቀም ዝንጉነት ይስተዋልባቸው ነበር፡፡ በተሻለ የተንቀሳቀሱት አዳማዎች በአላሚን ናስር ወደ አጥቂዎች በሚጣሉ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ቢታትሩም የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ቢኒያም አይተን የንቃት ችግር ሌላኛው ቡድኑን ወደ ጨዋታ ቅኝት በጊዜ እንዲገባ አላደረገም ነበር፡፡

በዚህኛውም አጋማሽ በመስመር በማጥቃት አዋጭ የሆነላቸው በምንተስኖት እና ቧይ ኩዌት ፈጣን የሽግግር ሂደት ወደ አዳማ ግብ ክልል ከመድረስ ያገዳቸው አልነበረም፡፡ አብዲ ዋበላ ከርቀት በሞከራት ጠንካራ አጋጣሚ ቀዳሚ መሆን የቻሉት አዳማ ከተማዎች በቅብብል ወደ አዲስ አበባ ግብ ክልል መድረስ ቢችሉም ወደ ጎልነት መለወጡ ላይ ትልቁ ችግራቸው ሆኖ ቀጥሏል፡፡ 89ኛው ደቂቃ ላይ ፍራኦል ጫላ ከሳጥን ውጪ አስገራሚ ጎል አስቆጥሮ አዳማን ከባዶ መሸነፍ ታድጓል፡፡ ጨዋታውም በአዲስ አበባ ከተማ 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ 7፡00 የጀመረው የወልቂጤ ከተማ እና ሀላባ ከተማ ነበር፡፡ ወልቂጤ ከተማዎችን ለማበረታታት ደጋፊዎቻቸው በስታዲየም ተገኝተው ሲያበረታቱ በታየበት መርሐግብር የጨዋታው ደቂቃ እስኪገፋ ድረስ በአንፃራዊነት የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ኳስን በመቆጣጠር እና ወደ ግብ ክልል ደርሶ ግብ ለማስቆጠር ወልቂጤ ከተማዎች ተሽለው መቅረብ የቻሉ ሲሆን ቀስ በቀስ በተለይ ከሰላሳ ደቂቃዎች መንጎድ በኃላ ግን ሀላባ ከተማዎች ያደረጉት የረጃጅም ኳስ አጠቃቀም ወደ ጨዋታ ቅኝት እንዲገቡ እንደረዳቸው መመልከት ይቻላል፡፡

ወልቂጤ ከተማዎች በአንድ ሁለት ቅብብል በመሀል ሜዳ ላይ መፍጠር ከቻሉ በኃላ ወደ መስመር ኳሶችን በመጣል ጎሎችን ለማግኘት ጥረዋል፡፡ 19ኛው ደቂቃ ላይ በግብ ክልል ውስጥ የሀላባ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ሀይደር ሽኩር አስቆጥሮ ወልቂጤ ወደ 1ለ0 መሪነት አሸጋግሯል፡፡

ጎል ካገቡ በኃላ በይበልጥ ተጨማሪ ጎል ለማግኘት በተደጋጋሚ ወልቂጤዎች ጥረት ቢያደርጉም ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ ቅኝት የገቡት ሀላባዎች አቻ ሆነዋል፡፡ 36ኛው ደቂቃ ላይ በግምት ከ30 ሜትር ርቀት ላይ ያገኙትን የቅጣት ምት ተመስገን ካሱ በቀጥታ ወደ ጎል አክርሮ ሲመታ የወልቂጤው ግብ ጠባቂ ቢኒያም አብዮት በአግባቡ መቆጣጠር ባለመቻሉ ከመረብ አርፋ 1ለ1 ሆነዋል፡፡

ተመጣጣኝ የሆነ ፉክክር የተንፀባረቀበት ከሙከራ አንፃር ወልቂጤዎች ተሽለው መቅረብ በቻሉበት የሁለተኛው አጋማሽ ሠራተኞቹ በተደጋጋሚ ለሀላባ ተከላካዮች ፈታኝ እንቅስቃሴን በማድረግ ሲረብሽ በነበረው ቴፐኒ ፍቃዱ አማካኝነት ሙከራዎችን ለማግኘት ጥረዋል፡፡ ያቤፅ አስፋው ባደረጋት ሙከራ በአጋማሹ ቀዳሚ መሆን የቻሉት ወልቂጤዎች 62ኛው ደቂቃ ዮሴፍ ብርሀኑ ከርቀት ባስቆጠራት ግሩም ግብ ወደ መሪነት መሻገር ችለዋል። ጎሉ ከተቆጠረ በኃላ የወልቂጤው ቴፐኒ ፍቃዱ ደስታውን ለመግለፅ በእጅ ምልክት ያሳየው ምስል እጅጉን አስነዋሪ በመሆኑ በፍፁም ሊደገም እንደማይገባው በዚሁ አጋጣሚ ሶከር ኢትዮጵያ ለመግለፅ ትወዳለች፡፡

ከሶስት ደቂቃዎች በኃላ በድንቅ አጨራረስ አብዱላዚዝ አብደላ ሀላባን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡ ጎል ከተቆጠረባቸው በኃላ በተደጋጋሚ የሙከራ የበላይነት ወልቂጤዎች ቢኖራቸውም ወደ ጎልነት መለወጥ ሳይችሉ ጨዋታው 2ለ2 ሊያልቅ ግድ ሆኗል፡፡

የመጨረሻው የአንደኛው ዙር ማሳረጊያ ጨዋታ በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያለው ሀዲያ ሆሳዕና እና ኢትዮጵያ መድንን የተገናኙበት ነበር፡፡ብዙም ሳቢ ያልነበረው እና ጥቂት ሙከራን በተመለከትንበት የመጀመሪያው አጋማሽ 6ኛው ደቂቃ ላይ ልማደኛው ደስታ ዋሚሾ ሀድያ ሆሳዕናን ቀዳሚ አድርጓል፡፡

ጎል ካስተናገዱ በኃላ ኢትዮጵያ መድኖች ወደ ጨዋታ ቅኝት በመመለስ ብዙ የሚባክን ግን ጥቂት ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም አቻ የሚያደርጋቸው ዕድል ለማግኘት ታትረዋል፡፡ አሸናፊ ተስፋዬ 27ኛው ደቂቃ ከግራ የግብ ክልሉ አቅጣጫ በቀጥታ የመታት ኳስ የግቡ ቋሚ ብረት የመለሰበት እና አርባ አምስቱ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ሊያመሩ ሽርፍራፊ ሰከንድ እየቀረ ጌታሁን ጎሳዬ እጅግ ያለቀለትን የግብ ዕድል ከግቡ ትይዩ አግኝቶ ወደ ላይ የሰደዳት አጋጣሚ ምናልባት ከሙከራዎች ሁሉ ላቅ ያለች ሆና መድንን አቻ የምታደርግ ነበረች፡፡

ከእረፍት መልስ በኳስ ቁጥጥሩ እና በሙከራ ረገድ ኢትዮጵያ መድኖች ብልጫ ይዘው ሲገቡ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ቀዝቀዝ ብለው ኃላ ላይ ግን በረጃጅሙ ወደ አጥቂ ክፍሉ አልፎ አልፎ በመላክ ግብ ለማግኝት ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል፡፡ ከመስመር አልያም ከመሀል ክፍሉ ከሚገኙ አጋጣሚዎች ጎል ለማስቆጠር ብልጫን ወስደው ሲታዩ የነበሩት ኢትዮጵያ መድኖች 79ነኛው ደቂቃ ላይ አቻ ሆነዋል፡፡ ዳግም ንጉሴ ላይ የሀድያ ተከላካዮች በሳጥን ውስጥ በሰሩት ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አሸናፊ ተስፋዬ ወደ ጎልነት ለውጧት 1ለ1 ሆነዋል፡፡ በቀሩት ደቂቃዎች ኢትዮጵያ መድኖች ተጨማሪ ግብ ለማከል ጥረት ባይለያቸው ከመረብ ጋር ማገናኘት ሳይችሉ 1ለ1 ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ