ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ኤሌክትሪክ በዮርዳኖስ ምዑዝ ሁለት ጎሎች ንግድ ባንክን ረቷል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ሊጉን እየመራ የሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተገናኝተው የዮርዳኖስ ምዑዝ ሁለት ድንቅ ግቦች ኤሌክትሪክን 2ለ1 አሸናፊ አድርጓል፡፡

ረፋድ 4፡00 ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ መሪነት የተጀመረው ጨዋታው ደቂቃ እስኪገፋ በአመዛኙ ቡድኖቹ አጀማመራቸው የተፈራሩ በሚመስል መልኩ አብዛኛዎቹን እንቅስቃሴዎች በመሀል ሜዳው ላይ ታጥረው የቆዩበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በሒደት ባንኮች ከሰናይት ቦጋለ እግር ስር ከሚመነጩ ኳሶች ወደ ሎዛ አበራ እና ረሂማ በተደጋጋሚ በማሾለክ ጠጣር የነበረውን የኤሌክትሪክን የግብ ክልል ለማለፍ ጥረትን አድርገዋል፡፡ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው መሀል ሜዳ ላይ ድንቅ በነበረችው ሲሳይ ገብረዋህድ እና በግራ በእፀገነት ብዙነህ አማካኝነት ከፊት ወደተሰለፈችው ዮርዳኖስ ምዑዝ በማሻገር ለንግድ ባንክ የተከላካይ ክፍል ለመረበሽ ጥረዋል።

13ኛው ደቂቃ ሎዛ አበራ ከቀኝ በኩል መሬት ለመሬት ወደ ግብ ክልል ስታሻማ ረሂማ ዘርጋው አግኝታው ወደ ላይ በሰደደችው ኳስ ወደ ኤሌክትሪኮች ግብ ክልል መጠጋትን የጀመሩት ባንኮች 26ኛው ደቂቃ ላይ ሰናይት ቦጋለ ስታሻማ ረሂማ በግንባር ገጭታ የግቡ የቀኝ ቋሚ ብረት መልሶት መሠሉ አበራ ደርሳ ባወጣችው ኳስ ጎል ለማግኘት ጥረዋል፡፡

በመጨረሻዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች የላይነት የወሰዱት ኤሌክትሪኮች 36ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አግምተዋል። ታታሪነት ይታይባት የነበረው ሲሳይ ገብረዋህድ ወደ ግራ አዘንብላ ወደ ነበረችው ዮርዳኖስ ምዑዝ በረጅሙ አሻግራ ዮርዳኖስም የንግድ ባንክ ተከላካዮችን ስህተት በመጠቀም ሁለት ጊዜ ኳሱን ገፋ ካደረገች በኃላ ወደ ጎልነት ለውጣው ኤሌክትሪክን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡

ጎል ከተቆጠረባቸው በኃላ የንግድ ባንኩ አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛወው መሀል ሜዳ ላይ ተዳክማ የታየችው ህይወት ደንጌሶን በትዕግስት ያደታ ቀይረዋል፡፡ ተጫዋቿ ተቀይራ ብትገባም የተለየ ለውጥን በሜዳ ላይ ስታመጣ መመልከት ግን አልቻልንም፡፡

ከእረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ የንግድ ባንክ የተሻለ የሙከራ ብልጫ የታየበት በአንፃሩ በስህተት የተሞላው የኃላ ክፍል ታታሪነት ለሚታይባቸው የኤሌክትሪክ ተጫዋቾች ምቾትን የፈጠረ እንደነበር በአጋማሹ ማስተዋል ችለናል። 48ኛው ደቂቃ ዓለምነሽ ገረመው ከቀኝ መስመር ስታሻማ ግብ ጠባቂዋ ትዕግስት መልሳው ከፊቷ የነበረችሁ ሎዛ አበራ በቅፅበት መታው ትዕግስት በግሩም ሁኔታ ባወጣችባት አጋጣሚ ንግድ ባንኮች ወደ ግብ በመጠጋት ቀዳሚ ሆነዋል፡፡ከሁለት ደቂቃዎች ቆይታ በኃላ ሎዛ አበራ ከረሂማ መሀል ለመሀል የመጣላትን ኳስ በቀላሉ አስቆጠረች ሲባል ትዕግስት አበራ በፍጥነት ወጥታ አድናባታለች፡፡

66ኛው ደቂቃ ላይ መልሶ ማጥቃት ሲያዋጣቸው የነበሩት ኤሌክትሪኮች ሁለተኛ ግባቸውን አግኝተዋል፡፡ ትዕግስት አበራ በግራ መስመር ለነበረችው እፀገነት ብዙነህ ሰጥታት የግራ መስመር ተከላካይዋም በቀጥታ ለዮርዳኖስ ምዑዝ በረጅሙ ልካላት አጥቂዋ የገነሜ ወርቁን ስህተት ተጠቅማ ለራሷም ሆነ ለኤሌክትሪክም ሁለተኛ ጎል አስቆጥራለች፡፡ ከዚህች ጎል በኃላ ሳራ ነብሶ ሶስተኛ ጎል የሚሆን አጋጣሚን አግኝታ ንግስቲ መዐዛ አድናባታለች፡፡

ሁለት ግብ ለማስተናገድ የተገደዱት ንግድ ባንኮች የመጨረሻዎቸቹን ሀያ ደቂቃዎች በፍፁም የማጥቃት ኃይላቸው በኤሌክትሪክ ላይ ጫና መፍጠር ችለዋል፡፡ 73ኛው ደቂቃ ላይም ሰናይት ቦጋለ ሰጥታት ሎዛ መታ ድንቅ ጊዜ ሜዳ ላይ የነበራት ትዕግስተት አበራ መልሳባታለች፡፡ ቶሎ ቶሎ ጎል አስቆጥሮ ለማንሰራራት ሲታትሩ የነበሩት ባንኮች 75ኛው ደቂቃ ግብ አግኝተዋል፡፡ እመቤት አዲሱ ወደ ጎል በቀጥታ ስቶመታ ትዕግስት በመትፋቷ አጠገቧ የነበረችው ረሂማ ዘርጋው በቀላሉ አስቆጥራዋለች፡፡

በቀሩት ደቂቃዎች ተጨማሪ ግብን ለማግኘት ንግድ ባንኮች ቢጥሩም ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው በኤሌክትሪክ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ንግድ ባንክም በዓመቱ ሁለተኛ ሽንፈቱን አስተናግዷል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ