ቢንያም በላይ ወደ ኢትዮጵያ የሚመልሰውን ዝውውር ለመፈፀም ተስማማ

በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ቢንያም በላይ በፕሪምየር ሊጉ የሚገኝ ክለብን ለመቀላቀል ተስማምቷል።

ባለ ተስጥኦው የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አማካይ ቢኒያም በላይ አሳዳጊ ክለቡ ንግድ ባንክን በ2009 ለቆ ወደ ጀርመን በማቅናት ለዳይናሞ ደርስደን ለመጫወት የሙከራ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ ወደ አልባንያ በማምራት ከስከንደርቡ ክለብ ጋር ሁለት ስኬታማ ዓመታት አሳልፏል፡፡ በአልባኒያ ቆይታው የሊጉን ዋንጫ ከቡድኑ ጋር ካነሳ በኃላ በመቀጠልም በስዊድኖቹ ክለቦች ስሪያንስካ እና ኡመያ ክለቦች በመጫወት ቆይታን አድርጓል፡፡

የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ከሳምንታት በፊት ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ የተመለሰ ሲሆን በዚህ የዝውውር መስኮት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ክለቦች እንደሚዘዋወር ሲጠበቅ ቆይቷል። በዚህም ሲዳማ ቡናን ለመቀላቀል ከስምምነት መድረሱን እና አዲስ ነገር ካልተፈጠረ በቀር ለቡድኑ ፊርማውን አኑሮ ወደ ባህር ዳር በማቅናት ቡድኑን ለመቀላቀል እንደተዘጋጀ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ከውጤት ቀውስ ለመውጣት በዝውውር መስኮቱ እየተሳተፈ የሚገኘው ክለቡ ተጨማሪ አዲስ ፈራሚዎችን እንደሚቀላቅል እና በምትኩ ከበርካታ ተጫዋቾች ጋር እንደሚለያይ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ