​ሪፖርት | ቀዝቃዛው ጨዋታ በወላይታ ድቻ አሸናፊነት ተጠናቋል

በዛሬ ረፋዱ እጅግ ደካማ ፉክክር በታየበት ጨዋታ ወላይታ ድቻ በአዲስ ፈራሚው ጋቶች ፓኖም ጎል አዳማ ከተማን 1-0 ማሸነፍ ሲችል ታሪክ ጌትነት ሜዳ ውስጥ ያስተነገደው ግጭትም የጨዋታው አስደንጋጭ ክስተት ሆኗል።

ወላይታ ድቻ ሀዲያ ሆሳዕናን ከረታበት ጨዋታ ውስጥ ጉዳት በገጠመው አስናቀ ሞገስ እና መሣይ አገኘሁ ምትክ አዲስ ፈራሚው ጋቶች ፓኖም እና ፀጋዬ ብርሀኑን ተጠቅሟል። በአዳማ በኩል በተደረጉ ለውጦች ደግሞ ከጅማው ጨዋታ አንፃር ፍሰሀ ቶማስ ፣ ብሩክ መንገሻ ፣ እዮብ ማቲያስ እና ዳንኤል ተሾመ አርፈው ኤልያስ ማሞ ፣ ያሬድ ብርሀኑ ፣ ደሳለኝ ደባሽ እና ታሪክ ጌትነት ጨዋታውን ጀምረዋል።

የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ከሙከራዎች የራቀ እና በእንቅስቃሴም የተቀዛቀዘ ነበር። የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ይዘው ጨዋታውን የጀመሩት አዳማ ከተማዎች ወደ ወላይታ ድቻ የግብ ክልል የደረሱባቸው ጥቂት አጋጣሚዎች የጨዋታ ውጪ በሆኑ አቋቋሞች እና በቁጥር በተመናመነ የተጨዋቾች የመጨረሻ ማጥቃት ተሳትፎ ከሙከራ ርቀው ቆይተዋል። ሲጀመር የተወሰደባቸውን ብልጫ በእጃቸው ማስገባት የቻሉት ወላይታ ድቻዎችም ከመልሶ ማጥቃት ባህሪያቸው ወጥተው አብዛኛውን ደቂቃ ኳስ በማንሸራሸር ነበር ያሳለፉት።

ወላይታ ድቻ በቀኝ መስመር ባደላ እንቅስቃሴ ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ሲያደርግ ቢታይም እንደተጋጣሚው ሁሉ ፊት ላይ ስል ሆኖ መቅረብ አልቻለም። 34ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ቅጣት ምት ደጉ ደበበ ከታሪክ ጌትነት ጋር ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው ያዳነበት ኳስም የተሻለው የአጋማሹ ሙከራ ነበር። ከዚህ ውጪ ድቻዎች ከቆሙ ኳሶች ለመፍጠር የሟከሯቸው ዕድሎች የአዳማን ስብስብ የሚያስጨንቁ ሆነው መታየት ችለዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው ብሶ እጅግ የተዳከመ እንቅስቃሴ እየታየበት የቀጠለ ነበር። መድረሻቸው የማይታወቁ ረጃጅም ኳሶች እና የተቆራረጡ ቅብብሎች በተደጋጋሚ እየታዩ ባለበት ሁኔታ 15 ደቂቃዎች አልፈው የአጋማሹን ቀዳሚ ሙከራዎች ተመልክተናል። በዚህም 61ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ድቻ የኋላ ክፍል በተዘናጋበት አጋጣሚ አዳማ ከተማዎች በመስመር አጥቂዎቻቸው በላይ አባይነህ እና ያሬድ ብርሀኑ አማካይነት ከሳጥን ውጪ ሁለት አደገኛ ሙከራዎችን አከታትለው አድርገው ለጥቂት ወጥተውባቸዋል።

ከዚህ በኋላ ጨዋታው እጅግ አስደንጋጭ ትዕይንትን አስተናግዷል። 64ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማዎቹ ታሪክ ጌትነት እና አሚን ነስሩ በተጋጩበት ቅፅበት ታሪክ ምላሱ ተንሸራቶ የመተንፈሻ አካሉን በመዝጋቱ አስጊ የሚባል አደጋ ገጥሞታል። ራሱን በሳተው ግብ ጠባቂ ሁኔታም ሜዳው ላይ ካሉ ተጨዋቾች ውጪ ተጠባባቂዎች እና ሌሎች የጨዋታው አካል የሆኑ ግለሰቦች ሜዳ ውስጥ በከፍተኛ ድንጋጤ ተውጥተው ታይተዋል። ዘጠኝ ደቂቃዎች ከፈጀው የመጀመሪያ ዕርዳታ በኋላም ታሪክ ጌትነት ለተጨማሪ እርዳታ ወደ ሆስፒታል አምርቷል። 

ጨዋታው ሲቀጥል መሳይ አገኘሁን ቀይረው ያስገቡት ወላይታ ድቻዎች የተሻለ የማጥቃት ኃይል ኖሯቸው በተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ላይ ሲታዩ አዳማዎች አፈግፍገው ክፍተቶችን መዝጋት ላይ ትኩረት አድርገዋል። 82ኛው ደቂቃ ላይም የመሳይ አገኘሁን የማዕዘን ምት አንተነህ ጉግሳ በግንባሩ አመቻችቶለት ጋቶች ፓኖም በግንባሩ በማስቆጠር በድቻ ማለያ የመጀመሪያ ግቡን አስመዝግቧል። በቀሩት ደቂቃዎች ጨዋታው ዳግም ተዳክሞ ቀጥሎ ጭማሪ ደቂቃ ላይ የጨዋታውን ከባድ ሙከራ ስንመለከት መሣይ አገኘው ቸርነት ጉግሳ የሰጠውን ኳስ ከቅርብ ርቀት ሞክሮ በግቡ ቋሚ ተመልሶበታል። እስከ 103ኛው ደቂቃ የዘለቀው ጨዋታም በወላይታ ድቻ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ የጦና ንቦቹ ነጥባቸውን 20 አድርሰው ወደ ስድስተኝነት ከፍ ማለት ችለዋል።