​የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 1-0 አዳማ ከተማ

ከዛሬው ቀዳሚ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ከሱፐር ስፖርት ጋር የተደረገው የአሰልጣኞች ቆይታ ይህንን ይመስል ነበር።

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው – ወላይታ ድቻ 

ስለጨዋታው

ጨዋታው የእኛን ክፍተት በተጨባጭ ያሳየ ነበር። ጥቅጥቅ ብሎ የሚከላከል ቡድን ሲያጋጥም የማስከፈት አቅምህ ትልቅ መሆን አለበት። ሰው የመቀነስ አቅምህም ትልቅ መሆን አለበት። ካልሆነ ሁሌ ከቆሙ ኳሶች ብቻ አገባለሁ ማለት ትንሽ ይከብዳል። ያ ይጎለናል ፤ ድክመታችን ያ ነበር። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ከ20ኛው ደቂቃ በኋላ ግን ኳስ ይዘን ለመንቀሳቀስ ጥረት አድርገናል። ያገባነው በእርግጥም ከማዕዘን ምት ነው። ነገር ግን ሁለተኛ ግብ ሊሆን የሚችል ኳስ አግኝተን ነበር ፤ የግቡ ቋሚ መልሶብናል። አሁን አለመግባቱ እና መግባቱ አይደለም አካሄዱ ጥሩ ነበር። እና ይሄን ነገር ማጎልበት ያስፈልጋል። 

የቡድኑ የአለመሸነፍ ሂደት እና ቀጣይ ጉዞ

ያለመሸነፍ ብቻ ሳይሆን ባለፉት አራት ጨዋታዎች ግባችንንም አላስደፈርንም። እሱም ጥሩ ነገር ነው። አሁንም ከፍ ብለናል ሥራችን እና አቅማችን እስከፈቀደልን ድረስ እስከ ምርጥ አምስትም እስከ ሦስትም ለመድረስ እንሞክራለን።

አሰልጣኝ ዘርዓይ መሉ – አዳማ ከተማ

ጨዋታው እነሱ በተዘጋጁበት መንገድ ልክ እኛም የተዘጋጀንበት ነበር። ዞሮ ዞሮ ግብ ጠባቂያችን እስኪወጣ ድረስ ያንን ተቋቁመናል። ያው ተቃራኒ ቡድን የሚጫወትበት መንገድ ባመልሶ ማጥቃት እና የቆሙ ኳሶችን በመጠቀም ነው። እንደተነጋገርነውም ይቆመ ኳስ ነው የገባብን ፤ ልጆቹ የሚችሉትን አድርገዋል። የአቅማቸውን ነው የሰጡን እና ብዙ መስተካከል ያለበት ቡድን ነው። ቡድኑ መትረፍ ካለበት ብዙ ቦታዎች ላይ ክፍተቶች አሉት። እነሱ ካልተሟሉ ከባድ ነው የሚሆነው። ግን ያሉትን ልጆች ለመጠቀም ሞክረናል ፤ ለማየት ሞክረናል። ስለዚህ በቀጣይ ብዙ ሥራዎች ያሉት ቡድን ነው ብዬ ነው የማስበው።

የታሪክ መውጣት ለሽንፈቱ ምክንያት ስለመሆኑ

አዎ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ነበር። ዛሬ እሱ ቢኖር ኖሮ እየወጣ ኳስ ያድን ስለነበር የማዕዘን ምት የሆነውም ኳስ በቀላሉ የሚድን ነበር። አንዳንዴ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ትልቅ ለውጥ ይዘው ነው የሚመጡት። እና የእሱ ጉዳት ለሽንፈቱ ምክንያት ነው ብዬ ነው የማስበው።