የአዳማው ግብጠባቂው ታሪክ ጌትነት የተፈጠረበትን አስደንጋጭ ጉዳት ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይደርስ የታደገው በላይ ዓባይነህ ስተፈጠረው ሁኔታ ይናገራል።
በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ እስከዛሬ በተካሄዱ አስራ አምስት ሳምንት ጉዞ ውስጥ እንደዛሬው አስደንጋጭ የተጫዋች ጉዳት አልተከሰተም። በወላይታ ድቻ እና በአዳማ ከተማ በዛሬው ዕለት በተካሄደው ጨዋታ 64ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማው ግብጠባቂ ታሪክ ጌትነት እና የራሱ የቡድን አባል ከአሚን ነስሩ ጋር በተጋጩበት ቅፅበት ታሪክ ምላሱ የመተንፈሻ አካሉን በመዝጋቱ ሜዳ ውስጥ አሳዛኝ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ድርጊቱ በተፈፀመበት ቦታ በቅርብ ርቀት የነበረው የአዳማው የመስመር አጥቂ በላይ ዓባይነህ በፍጥነት በመድረስ የታሪክ ሁኔታ ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይደርስ በእጁ አፉን ለመክፈት ሲፈለቅቅ ሌላኛው የቡድን አጋሩ ደሳለኝ ደባሽ ምላሱን በማውጣት ህይወቱን ታድገውታል። ይህ ሁኔታ ሲፈጠር ተጨዋቾችም ሆኑ በተጠባባቂ ወንበር የነበሩትን ጨምሮ ሌሎች የጨዋታው አካል የሆኑ ግለሰቦች በሙሉ ሜዳ ውስጥ በከፍተኛ ጭንቀት ተውጠው ሲያለቅሱ ለመታዘብ ችለናል።
በሰዓቱ የተፈጠረውን ሁኔታ አስመልክቶ በፍጥነት በመድረስ ከቡድን አጋሩ ደሳለኝ ደባሽ ጋር በመሆን ህይወቱን የታደገው በላይ ዓባይነህ ስለተፈጠረው ሁኔታ ለሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቷል።
” እጅግ የሚያሳዝን ሁኔታ ነው። እንዳጋጣሚ ታሪክ ተመቶ ዞር ስል ከንፈሩ ላይ ፈሳሽ ነገር እየፈሰሰ አየሁ። በቃ ደንግጬ ምላሱን ውጦ ነው ብዬ ሩጬ ወደ እርሱ ሄድኩ። ወድያው እጄን ከትቼ ምላሱን ለማውጣት ጥረት አደረኩ። እንደ አጋጣሚ ሙሉ ለሙሉ ምላሱን አልዋጠም ነበር። ደሳለኝ እጁን በመክተት ምላሱን እንዳይውጥ አድርጎት ተጫዋቾች እየጮሁ ተጣሩና የህክምና ባለሙያዎች መጥተው ተረባርበን ሊተርፍ ችሏል።
“እርሱን ለማዳን በማደርገው ጥረት እጄ ትንሽ ቆስሏል። ይህ ለኔ ምንም አይደለም ከእኔ እጅ የእርሱ ህይወት መትረፍ ይበልጣል።
” ከዚህ ቀደም ልምዱ የለኝም። ያው ተጫዋቾች እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥማቸው ሜዳ ውስጥ በምን መልኩ እንደሚድኑ ብዙ ጊዜ የማየቱም የመስማቱም ዕድል ነበረኝ። ከዛ የተነሳ ነው እንዲህ ያለ ግጭት ሲፈጠር ይህን ላደርግ የቻልኩት።
” ፈጣሪ ረድቶን ይህን አስጨናቂ ጊዜ አልፈናል። ከመሐል አንድ ሰው ማጣት በጣም የሚከብድ ነገር ነው። አጠገብህ ያለ ሰው እንዲህ ሆኖ መመልከት በጣም ያማል። ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን ህይወቱ በመትረፉ።”
ለተጨማሪ እርዳታ ወደ ሆስፒታል ያመራው ታሪኬ በአሁኑ ሰዓት በሙሉ ጤንነት እንደሚገኝ ለማረጋገጥ ችለናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ