ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መከላከያ ወደ ድል ተመልሷል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አስራ አምስተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ መከላከያ ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኃላ አርባምንጭን 3ለ1 በመርታት ወደ ድል ተመልሷል፡፡

የሚባክኑ ኳሶች በርክተው በታዩበት እና ተመጣጣኝ የሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ያስተዋልንበት የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የመስመር አጨዋወት ላይ አመዝኖ ተመልክተናል። በተለይ አርባምንጮች በግራ በኩል ከተሰለፈችው ርብቃ ጣሰው እና መሀል ሜዳ ላይ ካሉ ተጫዋቾች ወደ አጥቂ መሠረት ወርቆነህ በመጣል ጎሎችን ለማግኘት ጥረዋል፡፡ ለዚህም አጨዋወታቸው ማሳያ መሠረት ማቲዮስ ከቀኝ በኩል አሻምታ መሠረት ወርቅነህ ግልፅ የግብ ማግባት ዕድልን በ10ኛው ደቂቃ ያመከነችበት መንገድ አስቆጪ ነበር፡፡ 

ከተሻጋሪ ኳስ ግብ ለማግኘት መጣራቸውን የቀጠሉት አርባምንጮች የመከላከያን የተከላካይ ስህተት ተጠቅመው ጎል አስቆጥረዋል፡፡ 32ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ በኩል በረጅሙ ወደ ጎል የተሻገረውን ኳስ መሠረት ወርቅነህ በግንባር ጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረችሁ ለርብቃ ጣሰው ሰጥታት የግራ መስመር ተከላካዩዋ በቀላሉ ወደ ጎልነት ለውጣው አርባምንጭን መሪ አድርጋለች፡፡

ጎል ካስቆጠሩ በኃላ ጨዋታው ያለቀ የመሰላቸው አርባምንጮች ፈዘው በዋሉት መከላከያዎች በሒደት ብልጫ ተወስዶባቸዋል፡፡ በተለይ በመስመር አጨዋወት ከመዲና ዐወል እና ሥራ ይርዳው እንዲሁም በመሳይ ተመስገን እና ሴናፍ ድንቅ ቅንጅት ወደ አርባምንጭ የግብ ክልል መድረስ ችለዋል፡፡ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶም መደበኛው አጋማሽ ተጠናቆ በተሰጠ ጭማሪ ደቂቃ ከግራ በኩል ቤተልሄም በቀለ አሻምታ በአርባምንጮች ተከላካዮች በግባር ሲመለስ መሳይ ተመስገን ጋር ደርሶ አክርራ ስትመታው የአርባምንጯ ግብ ጠባቂ ድንቡሽ አባ ኳሱን ለመቆጣጠር ባደረገችው ጥረት በተፈጠረ ስህተት ኳስ ከመስመር አልፏል በሚል በረዳት ዳኛዋ ይልፋሸዋ አየለ አማካኝነት ውሳኔ ግብ ሆኖ ፀድቆ መከላከያዎች አቻ ሆነው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ መከላከያዎች በሚገባ ወደ ጨዋታ ቅኝት ገብተው የታየበት እና አርባምንጮች ተረጋግቶ ከመጫወት ይልቅ አቻ ሆኖ ለመጨረስ ያሰቡ በሚመስል መልኩ ኳስን በረጃጅሙ ከግብ ክልላቸው ማውጣትን ምርጫቸው አድርገው የቀረቡበት ነበር፡፡ 49ኛው ደቂቃ የተገኘውን የማዕዘን ምት ሥራ ይርዳው ስታሻማ ሴናፍ ዋቁማ በአግባቡ በመቆጣጠር ለመዲና ዐወል አቀብላት ተጫዋቿም ወደ ጎል ለውጣው መከላከያን ከተመሪነት ወደ መሪነት አሸጋግራለች፡፡ 53ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ መዲና ዐወል ወደ ጎል አክርራ ስትመታ በሳጥን ውስጥ ተከላካይዋ ድርሻዬ መንዛ በእጅ በመንካቷ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ሴናፍ ዋቀማ ወደ ጎልነት ለውጣው የክለቧን የጎል መጠን ከፍ አድርጋለች፡፡

አጀማመራቸው ጥሩ ቢሆንም የኃላ ኃላ ለመከላከያ እጅ ለመስጠት የተገደዱት አርባምንጮች ጎሎችን ካስተናገዱ በኃላ አሰልጣኙ ጌታሁን ሲያሳይ የነበረው አዝናኝ ስሜታዊ ባህሪ ፈገግ የሚያሰኝ ነበር፡፡

መከላከያዎች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር በመዲና እና ሴናፍ ያለቀላቸውን ዕድል አግኝተው መጠቀም ሳይችሉ ቀርተው ጨዋታው 3ለ1 ተጠናቋል፡፡



© ሶከር ኢትዮጵያ