Anterior Cruciate Ligament (ACL) መጎዳት በእግር ኳስ

Anterior Cruciate Ligament አልያም ACL በእግር ኳስ ጨዋታ ወቅት ጉዳት ከሚያጋጥማቸው ጅማቶች መካከል አንዱ ነው። ተጫዋቾች ከሜዳ ለረጅም ወራት እንዲርቁም ያስገድዳል። በዛሬው የሶከር ሜዲካል አምዳችን ስለዚህ ጅማት ይህንን ፅሁፍ አዘጋጅተናል።

በምስሉ ላይ እንደሚታየው ACL በጉልበታችን በፊተኛው በኩል የሚገኝ ጅማት ሲሆን ከአጥንቱ ክፍል የlater condyle በስተግራ ተነስቶ የtibial spine በስተቀኝ ላይ ያርፋል።

የACL ተግባር ከፊትለፊት ከሚመጡ ግጭቶች ጉልበትን መጠበቅ (stabilize) ነው። Posterior Cruciate Ligament ደግሞ የዚህን ተቃራኒ ይሰራል ማለት ነው ።

የACL ጉዳት የሚከሰተው በርካታ ቦታ ላይ የጉልበት መገጣጠሚያዎች ጉዳት ሲደርስባቸው ነው። ለምሳሌ ያህል የጉልበት ውልቃት ፣ የታችኛው Femur አጥንት ስብራት እና የTibia አጥንት Plateau ስብራት ናቸው ።

በእግር ኳስ ጨዋታ ወቅት ልማዳዊ ባልሆነ መልኩ እግር የተለያዩ ግጭቶች እና መተጣጠፎች ያጋጥሙታል ። በዚህን ወቅት ACL ላይ ጉዳት ይደርሳል። Physiological ካልሆኑ የእግር እንቅስቃሴዎች አንዱ Hyperextension ሲሆን እግርን በረጅሙ መዘርጋትን ያጠቃልላል።

የACL ጉዳት መከሰቱን ከምናውቅበት ምርመራ ዋነኛው Lachman Test ይሰኛል ። ምርመራውን የሚሰራው ሀኪም ጉልበት 30 ዲግሪ እንዲታጠፍ ካደረገ በኋላ የታችኛው የእግር ክፍል እንዲዘረጋ ለማድረግ ይሞክራል። Lachman test ከ94% እስከ 98% በሚሆን ስኬት ስለ ACL ጉዳት መኖር ይነግረናል። ከዚህም በተጓዳኝ Pivot Shift የተሰኘ ምርመራ ይደረጋል። ይህም ከLachman Test በበለጠ የACL ጉዳት መኖሩን ያሳያል።

ሀኪሙ ጉልበት ጉዳት ያጋጠመውን ተጫዋች በሚያይበት ወቅት ክፍት የሆነ ጥያቄን በመጠየቅ ግለሰቡ በራሱ ቋንቋ ጉዳቱ እንዴት እንደደረሰ እንደዚሁም የተሰማውን ስሜቶች እንዲያብራራ እድልን መስጠት ይኖርበታል። ለዚህም ” ወደዚህ ስፍራ እንድትመጣ ምክንያት የሆነህ ጉዳይ ምንድን ነው?” በማለት ጥያቄውን መጀመር ይኖርበታል።

ከጥያቄውም በኋላ የሚሰሩ አካላዊ ምርመራዎች የተለያዩ ቅደም ተከተል አላቸው።

1) Inspection ( ምልከታ)
2) Palpation ( ዳበሳ)
3) የእንቅስቃሴ እና ጥንካሬ ምርመራ
4) የጉልበት ጅማት ምርመራ
5) የጉልበት ልስልስ አጥንት ምርመራ
6) የጅማት እርጋታ ምርመራ
7) የመራመድ ሙከራ
8) የጡንቻ ድካም እና መዛባትን መመርመር እና የመሳሰሉት የምንከተላቸው የመመርመሪያ መንገዶች ናቸው።

ከአካላዊ ምርመራዎቹ በመቀጠል MRI የACL ጉዳትን ለመመርመር ወሳኙ መንገድ ነው።

የACL ጉዳት ለረጅም ወራት ከሜዳ ከማራቁም በተጨማሪ በአእምሮ ጤና ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል። የቀድሞ ብቃትን መልሶ ለማግኘትም ብዙ ልፋትን የሚጠይቅ ነው። ስለዚህ ከፍተኛ ትኩረት እና ብቁ ባለሙያዎች ያስፈልጉታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ